ጋና ገዳይ እና ከኢቦላ ጋር ተመሳሳይ በሆነው ቫይረስ ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አደረገች

ጋና በፍጥነት እና በቀላሉ ተላላፊ በሆነው ገዳይ ቫይረስ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አደረገች።

ማርበርግ የተባለው ይህ ቫይረስ ኢቦላን ከሚያመጣው ቫይረስ ጋር ተቀራራቢ ነው።

ሁለቱም ታካሚዎች በደቡባዊ አሻንቲ ግዛት ሕክምና ሲሰጣቸው ቆይቶ ሕይወታቸው አልፏል ተብሏል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የተወሰደው የታማሚዎቹ ናሙና በዚህ ገዳይ ቫይረስ መያዛቸውን ያሳየ ሲሆን፤ ሴኔጋል ያለ ቤተ ሙከራም ይህንኑ አረጋግጧል።

የአገሪቱ የጤና ባለሥልጣናት በቫይረሱ ተይዘው ሕይወታቸው ካለፉት ሰዎች ጋር ንክኪ ነበራቸው ተብለው የተጠረጠሩ 98 ሰዎች በላይቶ ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።

ማርበርግ ቫይረስ የሚያስከትለውን ሕመም የሚፈውስ መድኃኒት አልተገኘም። ብዙ ውሃ መጠጣት እና የሚታዩ ምልክቶችን ማከም የታካሚውን የመዳን ዕድል እንደሚያሻሽለው የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ቫይረሱ ወደ ሰዎች የሚተላለፈው ከሌሊት ወፎች ነው። በሰዎች መካከል ደግሞ ከሰውነት ከሚወጣ ፈሳሽ ጋር በሚኖር ንክኪ አማካኝነት በቀላሉ ይተላለፋል።

በዚህ ገዳይ በሆነው ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ከባድ የራስ ምታት፣ ትኩሳት፣ የጡንቻ ሕመም፣ ደም ማስመለስ እና የደም መፍሰስን ምልክት ይታይባቸዋል።

ሰዎች የሌሊት ወፎች ሊገኙባቸው ከሚችሉ ዋሻዎች እንዲርቁ እና ሥጋ ሲመገቡ በደንብ እንዲያበስሉ ባለሥልጣናት እያስጠነቀቁ ነው።

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ ይህ ቫይረስ አፍሪካ ውስጥ ቀደም ሲል በአንጎላ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በኡጋንዳ በተለያየ ደረጃ ተከስቶ ነበር።

የመጀመሪያው የማርበርግ ወረርሽኝ እአአ በ1967 ጀርመን ውስጥ የተከሰተ ሲሆን ሰባት ሰዎችም ሕይወታቸውን አጥተዋል።

እአአ በ2005 በቫይረሱ ምክንያት ከ200 በላይ ሰዎች አንጎላ ውስጥ ሕይወታቸው አልፏል። ይህም በዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት እጅግ የከፋው ነው ተብሎ ተመዝግቧል።