ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሊቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከእስራኤል አቻቸው ጋር መወያየታቸው ተቃውሞ አስነሳ፣ ከሥራቸውም ታገዱ
የሊቢያዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከእስራኤሉ አቻቸው ጋር የመገናኘታቸው ዜና በዋና ከተማዋ ትሪፖሊ ታቀውሞ ከቀሰቀሰ በኋላ ሚኒስትሯ ከሥራቸው ታገዱ።
የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር የካቢኔ አባላቸው ከፍቃዳቸው ውጪ ከእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ ባለሥልጣኗን ከሥራ አግደዋል።
የሊቢያዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናጀላ አል-ማንጉሽ ከእስራኤሉ አቻቸው ኤሊ ኮኽን ጋር የመገናኘታቸው ዜና ከተሰማ በኋላ በሊቢያ ተቃውሞ ተቀስቅሷል።
ሊቢያ ፍልስጤማውያንን በመደገፍ ለእስራኤል እውቅና አትሰጥም።
እስራኤል በበኩሏ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሊቢያን ጨምሮ ከአረብ አገራት ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ጥረት እያደረገች ትገኛለች።
የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊ ኮኽን ከሊቢያዋ አቻቸው ጋር ጣሊያን በሮም በነበረ ስብበሳ ላይ ካገኟቸው በኋላ የነበራቸውን ግንኙነት ታሪካዊ ሲሉ ገልጸውታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ከእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መገናኘታቸው ያስቆጣቸው የሊቢያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱል ሐሚድ ደዴባህ ግን ሚንስትሯን ከማገዳቸው በተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግባቸው ጭምር አዘዋል።
የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከማንጉሽ ጋር በነበራቸው ግንኙነት ሁለቱ አገራት መካከል ግንኙነት ለመመሥረት ስላለው ዕድል መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሮም በነበረው ውይይት ላይ እስራኤል ስለምታደርገው ሰብዓዊ እርዳታ፣ ግብርና፣ የውሃ ሃብት አስተዳደር እና በሊቢያ ያሉ የአይሁዶች ቅርስን ስለመጠበቅ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል ተብሏል።
የሊቢያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ግን ሚኒስትሯ ከእስራኤል ተወካዮች ጋር ውይይት ለማድረግ የቀረበላቸውን ጥሪ አለመቀበላቸውን እና ሁለቱ ሚንስትሮች የተገናኙት “ምንም አይነት ዝግጅት ባልተደረገበት በጣሊያን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በነበረ ይፋዊ ባልሆነ ስብሰባ ላይ ነው” ብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ለመከላከል የወጣው መግለጫ በሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባን ተከትሎ የተደረሰ ምንም አይነት ስምምነትም ሆነ መደምደሚያ አለመኖሩን ገልጿል።
የሊቢያዋ ሚኒስትር ከእስራኤሉ አቻቸው ጋር የመገናኘታቸው ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ በትሪፖሊ እና በሌሎች የሊቢያ ከተሞች ተቃውሞ ተቀስቅሷል።
በዚህም ሳቢያ መንገዶች ተዘግተዋል፣ ጎማ ተቃጥሏል እንዲሁም ተቃዋሚዎች የፍልስጤም ባንዲራን ይዘው አደባባይ ወጥተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያለው እና ሦስት የሊቢያ ግዛቶችን እያስተዳደረ ያለው መንግሥት ከእስራኤል ጋር ግንኙነት መጀመር ሕጋዊ አይደለም ብሏል።
የአገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን በአገር ክህደት ከመወንጀሉም በላይ ለዛሬ ሰኞ አስቸኳይ ሰብብሰባ መጠራቱን አመልክቷል።
ሊቢያ በሞአመር ጋዳፊ ስር ስትመራ በነበረበት ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ከሊቢያ የተባረሩ ሲሆን፣ በርካታ የአይሁዳውያን ማምለኪያ ስፍራዎች ደግሞ እንዲወድሙ ተደርገዋል።
እስራኤል በቅርብ ዓመታት ከተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፣ ከባህሬን፣ ከሱዳን እና ከሞሮኮ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ ለመመሥረት መቻሏ ይታወቃል።