እንግሊዝ የእርቃን ምስልን ያጋሩ አሊያም የፈጠሩ ሰዎችን በሁለት ዓመት እሥር ልትቀጣ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሰዎችን ልቅ ምስሎችን ሳያስፈቅዱ ማጋራትም ሆነ መፍጠር እንግሊዝ እና ዌልስ ውስጥ ለእሥር የሚዳርግ ድርጊት ሊሆን ነው።
ኦንላይን ሴፍቲ ቢል የተሰኘው ረቂቅ ልቅ ምስልን የሚያጋሩ ሰዎች የስድስት ወራት እሥር ሊገጥማቸው አንደሚችል አመልክቷል።
በተለይ ደግሞ በበቀል የሰዎችን እርቃን ምስል ማጋራት፤ ካልሆነም ደግሞ ዲፕፌክ የተባለውን ቴክኖሎጂን ምስላቸውን መፍጠር በሕግ ያስቀጣል።
ጥፋተኞች ይህ ድርጊታቸው ለጭንቀት፣ መዋረድ እና ለሌሎች ጉዳቶች የሚያስከትል ከሆነ ቅጣቱ ወደ ሁለት ዓመት ከፍ ይላል።
ከዚህ አልፎ መሰል ድርጊቶችን የሚፈፅሙ ሰዎች ስማቸው ወሲባዊ ጥቃት ያደረሱ ሰዎች መዝገብ ላይ ይሰፍራል።
የበቀል የወሲብ ፊልም (ሪቬንጅ ፖርን) ማለት የሰዎችን ልቅ ምስል ያለፈቃዳቸው ማጋራት ነው።
ዲፕፌክ ፖርን ደግሞ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የሰዎችን ምስል ወስዶ ፎቶ አሊያም ቪድዮ መሥራት ማለት ነው።
‘ሪቬንጅ ፖርን’ በፈረንጆቹ 2015 ወንጀል ነው ተብሎ ቢመዘገብም ከሳሾች ይህ ድርጊት ውርደት አሊያም ጭንቀት አስከትሎብናል የሚለውን ማስረገጥ አለባቸው።
ጆርጂያ ሐሪሰን በመባል የምትታወቀው ታዋቂ እንግሊዛዊት የቀድሞ ፍቅረኛ የነበረው ስቴፈን ቤር በዚህ ዓመት የግለሰቧን ልቅ ምስል ያለፈቃዷ በማጋራቱ ለእሥር መዳረጉ ይታወሳል።
ላቭ አይላንድ በተሰኘው የቴሌቪዥን ፕሮግራም የምታተወቀው ሐሪሰን ሕጉ ትክክለኛ ነው ትላለች።
ኦንላይን ሴፍቲ ቢል የተሰኘው ረቂቅ ባለንበት የሰኔ ወር ለአገሪቱ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀርቦ ድምፅ ይሰጥበታል።
ዲፕፌክ የተሰኘው ቴክኖሎጂ በቅርቡ ወደ በይነ መረብ ቢመጣም በሰፊው እየተሰራጨ ነው።
ይህ ቴክኖሎጂ የሰዎችን ምስል በመጠቀም ያልሆኑትን እንደሆኑ፣ የሆኑትን እንዳልሆኑ አድርጎ መፍጠር የሚያስችል ነው።
አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው ዕድሜያቸው ከ18 አስከ 34 ከሆኑ ሰባት ሴቶች መካከል አንዷ ምስልን የማጋራት ማስጠንቀቂያ ይደርሳታል።
በተመሳሳይ ዕድሜ ውስጥ ካሉ ዘጠኝ ወንዶች መካከል አንዱ ማስጠንቀቂያ ይደርሰዋል።
ከአውሮፓውያኑ ሚያዚያ 2015 እስከ ታኅሣሥ 2021 ባለው ጊዜ ከ28 ሺህ በላይ ሰዎች ወሲባዊ ይዘት ያለው ልቅ ምስላቸው ያለፈቃዳቸው መለቀቁን ለፖሊስ አመልክተዋል።












