የአውሮፓ ኅብረት አሜሪካ 15 በመቶ ታሪፍ እንድትጥል ተስማማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም ግዙፍ የኢኮኖሚ አጋሮች የሆኑት አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ለወራት የቆየውን ፍትጊያቸውን በመቋጨት የንግድ ስምምነት ማዕቀፍ ላይ ደረሱ።
በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና በአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን መካከል በስኮትላንድ ከተደረጉ ድርድሮች በኋላ፤ ወደ ዋሽንግተን በሚገቡ በሁሉም የአውሮፓ ኅብረት ሸቀጦች ላይ የ 15 በመቶ ታሪፍ እንዲጣል ተስማምተዋል።
አሁን ስምምነት ላይ የደረሱበት የታሪፍ መጠን ትራምፕ ከአርብ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ሲዝቱ ከነበረው የ30 በመቶ ቀረጥ በግማሽ ያነሰ ነው።
የኅብረቱ አባል የሆኑት የ27ቱ አገራት በአንዳንድ አሜሪካ ምርቶች ላይ የሚጥሉትን ታሪፍ ወደ ዜሮ በማውረድ ገበያዎቻቸውን ለአሜሪካ ላኪዎች ክፍት ያደርጋሉ ብለዋል።
ኮሚሽነሯ ቮን ደር ሌየንም፤ ስምምነቱ የዓለም ንግድ አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን ድርሻ ለሚይዙት ሁለቱ አጋሮች መረጋጋትን ያመጣል በማለት አድናቆታቸውን ቸረዋል።
ትራምፕ የዓለም ኢኮኖሚን በድጋሚ ለመሰደር እና አሜሪካ ያለባትን የንግድ ጉድለት ለመቀነስ በሚል በዋና ዋና የአሜሪካ የንግድ አጋሮች ላይ ቀረጥ ሲጥሉ ቆይተዋል።
ፕሬዝዳንቱ፤ ከአውሮፓ ኅብረት በተጨማሪ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከጃፓን፣ ከኢንዶኔዥያ፣ ከፊሊፒንስ እና ከቬትናም ጋር የታሪፍ ስምምነቶችን መፈጸም ችለዋል።
ይህም ቢሆን ግን "በ90 ቀናት ውስጥ 90 ስምምነቶችን" ለመፈጸም ያስቀመጡት ግብ አልተሳካም።
እሁድ ዕለት የተደረገው ስምምነት ይፋ የተደረገው ትራምፕ እና ቮን ደር ሌየን በደቡብ ኤየርሻየር በሚገኘው በቱርንቤሪ የጎልፍ ሜዳ ላይ በግል ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው።
በስኮትላንድ የአምስት ቀናት ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ትራምፕ ካደረጉት አጭር ስብሰባ በኋላ፤ "ስምምነት ላይ ደርሰናል። ለሁሉም ጥሩ ስምምነት ነው" ብለዋል።
"ይበልጥ እንድንቀራረብ ያደርገናል" ሲሉም አክለዋል።
ቮን ደር ሌየን በበኩላቸው "ከከባድ ድርድሮች" በኋላ የተደረሰ "ትልቅ ስምምነት" ነው ሲሉ አወድሰዋል።
እንደ ትራምፕ ገለጻ፤ የአውሮፓ ኅብረት የአሜሪካ ወታደራዊ መሳሪያዎች ላይ የሚያፈስሰውን ጨምሮ በዋሽንግተን የሚኖረውን ኢንቨስትመንት በ 600 ቢሊዮን ዶላር ያሳድጋል። ኅብረቱ፤ ተጨማሪ 750 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ በኢነርጂ ዘርፍ ላይ እንደሚያፈስስም ተናግረዋል።
የአውሮፓ ኅብረት፤ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት በአሜሪካ የተፈጥሮ ጋዝ፣ ነዳጅ እና የኒውክሌር ነዳጆች ላይ የሚደርገው ኢንቨስትመንት፤ አውሮፓ በሩሲያ የኃይል ምንጮች ላይ ያላትን ጥገኛነት ለመቀነስ እንደሚረዳ ቮን ደር ሌየን ገልጸዋል።
አውሮፕላን እና የአውሮፕላን ክፍሎች፣ የተወሰኑ ኬሚካሎችን እንዲሁም አንዳንድ የግብርና ምርቶችን ጨምሮ አንዳንድ ሸቀጦች ምንም ዓይነት ታሪፍ አይጣልባቸውም። በ'ሰሚኮንዳክተሮች' ላይ እየተደረገ ያለ ሌላ ስምምነት በቅርቡ ይፋ ሊደረግ ይችላል ተብሏል።
ነገር ግን ትራምፕ በዓለም አቀፍ ደረጃ በብረት እና በአሉሚኒየም ላይ ተግባራዊ ያደረጉት የ50 በመቶ ታሪፍ ግን ባለበት እንደሚቀጥል ፕሬዝዳንቱ ብለዋል።
ቮን ደር ሌየን፤ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይህንን ስምምነት ለማሳካት ላሳዩት የግል ቁርጠኝነት እና አመራር በግል ማመስገን እፈልጋለሁ" ሲሉ ተደምጠዋል።
"ጠንካራ ተደራዳሪ ነው፣ ደግሞም ግን ስምምነትን ፈጻሚ ነው" ሲሉል አክለዋል።
ሁለቱም ወገኖች የደረሱበትን ስምምነት፤ ድል አድርገው ሊያቀርቡት ይችላሉ።
የአውሮፓ ኅብረት፤ እንደ ዩናይትድ ኪንግደም የ10 በመቶ የሆነ ዝቅተኛ ታሪፍ ባያገኝም፤ ኅብረቱ ሊጣሉበት የነበሩት የአሜሪካ ታሪፎች ከዚህም የከፉ ሊሆኑ ይችሉ ነበር።
ኅብረቱ ስምምነት የደረሰበት የታሪፍ መጠን፤ ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ከጃፓን ጋር ከተስማማችበት የ15 በመቶ ተመን ጋር ተመሳሳይ ነው።
ለአሜሪካ ደግሞ፤ ስምምነቱ 90 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚገመት የታሪፍ ገቢ በመንግሥት ካዝና ውስጥ እንደሚያስገባ ይጠበቃል።
በተጨማሪም በመቶ ቢሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር ኢንቨስትመንት ከአውሮፓ ኅብረት ወደ አሜሪካ ይመጣል።
አንድ ነገር ግልጽ ነው፤ በታሪክ ትልቁን የንግድ ስምምነት የፈረሙት ትራምፕ፤ ደስታ ላይ ናቸው።
በዚህ ስምምነት ውስጥ የአሜሪካን ጥቅም የሚያስጠብቁ ብዙ ውጤቶች ቢገኙም፣ የአውሮፓ ኅብረት ከዚህ ስምምነት ምን እንደሚያገኝ ግልጽ አይደለም።
ቮን ደር ሌየን ከዚህ ቀደም የሁለቱን አጋሮች የንግድ ግንኙነት "እንደገና ማመጣጠን" እንደሚያስፈልግ መናገራቸው ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
ቀደም ሲል፤ የአውሮፓ ኅብረት ለአሜሪካ ከሚሸጠው በላይ ከአሜሪካ ብዙ አገልግሎቶችን እንደሚገዛ በመግለጽ የንግድ ሚዛኑ አልተዛባም በማለት ሲከራከር ቆይቷል።















