የ 'ፍሬንድስ' ተዋናይን የገደለውን መድኃኒት የሸጠችለት 'የካታሚን ንግሥት' ማን ናት?

የፎቶው ባለመብት, TBC
ሁሉም የተሟላላት ሰው ናት። አስተዳደጓ ቅንጡ፣ ትምህርቷም ጥሩ እንደሆነ ይነገራል። የሚከቧት ወዳጅ ዘመዶች ብዙ ናቸው።
ጃዝቪን ሳንጋ ድብቅ ምሥጢርም ነበራት። የቅርብ ጓደኞቿ ስለ ምሥጢሯ አያውቁም።
እንግሊዛዊት አሜሪካዊቷ ጃዝቪን ለሆሊውድ ሃብታም እና ዝነኞች ኮኬይን፣ ዛኔክስ፣ ሐሰተኛ አድሪል እና ካታሚን ትሸጥ ነበር።
በ 'ፍሬንድስ' ተከታታይ አስቂኝ ፊልም ላይ የተወነው ማቲው ፔሪ ሲሞት ግን ንግዷ እና አንጸባራቂው ሕይወቷ ባለበት ተገታ።
ማቲው ፔሪ እአአ በ2023 የሞተው እሷ በሸጠችለት ካታሚን መድኃኒት እንደሆነ ተገልጿል።
ጃዝቪን ሳንጋ እና ሁለት ዶክተሮችን ጨምሮ አምስት ሰዎች ከማቲው ፔሪ ሞት ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ መሆናቸውን በፍርድ ቤት አምነዋል።
ፍርድ ቤት የፊታችን የካቲት በጃዝቪን ክስ የፍርድ ውሳኔ ይሰጣል። በፌደራል ፍርድ ቤት እስከ 65 ዓመት እንድትታሰር ሊወሰን ይችላል።
የተዋናዩን ሞት ተከትሎ የተከፈተው የወንጀል ምርመራ በሎስ አንጀለስ የተዘረጋውን የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ሰንሰለት አጋልጧል።
የአሜሪካ የመድኃኒት ቁጥጥር እና አስተዳደር ልዩ መርማሪ ቢል ቦንደር ከሎስ አንጀለስ ታይምስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጃዝቪንን የገለጹት "በከፍተኛ ደረጃ የተማረች ሰው ብትሆንም አደንዛዥ ዕፅ መሸጥን መረጠች። በምታገኘው ገንዘብም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ማንነትን ገነባች" በማለት ነበር።
ለሆሊውድ ሃብታም እና ዝነኞች "ከፍተኛ የአደንዛዥ ዕፅ አቅርቦት" ላይ ተሰማርታ እንደነበር ገልጸዋል።
ዐቃቤ ሕግ እንዳለው፤ ማቲው ፔሪ ለድባቴ በሐኪም የታዘዘለትን ካታሚን ይወስድ ነበር። ሆኖም ግን ከታዘዘለት መጠን በላይ ካታሚን ለመጠቀም በመፈለጉ ወደ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ፊቱን አዙሯል።

የፎቶው ባለመብት, Courtesy of Zanc
የፍርድ ቤት ሰነዶች እንደሚጠቁሙት፤ ተዋናዩ በበርካታ ዶክተሮች እና ዕፅ አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ነበር ጃዝቪን ከምትመራው ቡድን ጋር የተገናኘው።
ጠበቃዋ ማርክ ጌርጎስ እንዳሉት ማቲው ፔሪን በአካል እንደማታውቀው የገለጸችው ጃዝቪን ለድርጊቷ ኃላፊነት ወስዳለች።
"በጣም ነው ያዘነችው። ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ተከፍታለች" ብለዋል።
ቶኒ ማርከዝ የረዥም ጊዜ ጓደኛዋ ነው። ማቲው ከመሞቱ ከቀናት በፊት በስልክ አውርተዋል።
ቢቢሲ ካነጋገራቸው የጃዝቪን ጓደኞች አንዱ ቶኒ ነው። ጃዝቪን 'የካታሚን ንግሥት' በሚል ቅጽል ስም አነጋጋሪ ሆናለች።

ጃዝቪን እና ቶኒ እአአ ከ2010 ጀምሮ ጓደኛሞች ናቸው። ቤተሰቦቿን እንዳስተዋወቀችውም ይናገራል።
ጃዝቪን እና ቶኒ ከሎስ አንጀለስ የሙዚቃ እና መጠጥ ድግሶች አይጠፉም።
ከዚህ ቀደም ቶኒ ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ጋር በተያያዘ ተከስሶ ነበር። ጃዝቪን የቅርብ ጓደኛው ብትሆንም አደንዛዥ ዕፅ እንደምትሸጥ እንዳልነገረችው ለቢቢሲ ገልጿል።
ከወራት በፊት በሰሜን ሆሊውድ የሚገኘው ቤቷ በፖሊስ ተፈትሿል። ፖሊስ ቤቷን "የአንዛዥ ዕፅ ማከማቻ" ብሎታል።
ጃሽ ነጋንዲ ከጃዝቪን ጋር አብሮ ተምሯል። እአአ በ2001 በዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርያ ከተዋወቁ በኋላ ለ20 ዓመታት በጓደኛነት ቀጥለዋል።
"ሙዚቃ እና ዳንስ ትወዳለች። ጥሩ ጊዜ ማሳለፍም ደስ ይላታል። ሆኖም ግን አደንዛዥ ዕፅ ስለመሸጧ አንዳችም መረጃ አልነበረኝም። አውርታልኝም አታውቅም" ይላል።

ጃዝቪን ሃብታም ስለሆነች አደንዛዥ ዕፅ ከመሸጥ የሚገኘው ገንዘብ ያስፈልጋታል ብለው ጓደኞቿ አያምኑም።
"ሁሌም ገንዘብ አላት። በግል ጀት ነበር የምትንቀሳቀሰው" ይላል ቶኒ ማርከዝ።
አያቶቿ በምሥራቅ ለንደን በፋሽን ዘርፍ የታወቁ ሚሊየነሮች ናቸው። አባቷ ኒልም ሳንጋም ነጋዴ ናቸው። ከአባቷ እና ከእናቷ ዶ/ር ባልጂት ሳንጋ ቾከር ከፍተኛ መጠን ያለው ውርስ አግኝታለች።
እናቷ ሁለተኛ ባለቤታቸውን ካገቡ በኋላ በካሊፎርንያ፣ ካዛብላንካ መኖር ጀመሩ። ጃዝቪንም እዚያው አደገች።
የቤተሰቦቿ ቤት "ትልቅ" እና "ውብ" መሆኑን ቶኒ ይናገራል።
"ቤተሰቦቿ በመዋኛ ገንዳ ዳርቻ ምግብ ያበስላሉ። ሰው መንከባከብ በጣም ይወዳሉ። እኛንም እንደ ልጆቻቸው ነበር የሚያዩን።"
ጃዝቪን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ ለንደን ኖራለች። ሁለተኛ ዲግሪዋን ያገኘችው ከሁልት ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ስኩል ነው።
እአአ በ2010 ለንደም ከሚገኘው ዩኒቨርስቲ ስትመረቅ የሚያሳዩ ምሥሎች ደስተኛነቷን ያሳብቃሉ።
"ገንዘብ ለማግኘት የምትጣጣር አትመስልም ነበር" ሲሉ አብረዋት የተማሩ ሰዎች ይገልጿታል።
በዲዛይነሮች የተሠሩ አልባሳት በማድረግ ትታወቃለች። ማኅበራዊ ሕይወቷም ሞቅ ያለ ነበር። አደንዛዥ ዕፅ እንደምትሸጥ ጭምጭምታ እንኳ አልነበረም።

ሁለተኛ ዲግሪዋን አጠናቃ ወደ ሎስ አንጀለስ ተመለሰች። ከእናቷ እና ከእንጀራ አባቷ ጋር ትኖር ነበር።
እንጀራ አባቷ በካሊፎርንያ የኬኤፍሲ ቅርንጫፎችን ያስተዳድር ነበር። ለዋናው የኬኤፍሲ ኩባንያ መፈጸም ያለበትን ክፍያ ባለማድረጉ የ50 ሺህ ዶላር ክስ ቀርቦበታል።
ንግዱ መክሰሩን ካወጀ በኋላ ፍርድ ቤት የክስ ፋይሉን ዘግቷል።
በዚህ ወቅት የጃዝቪን ቤተሰብ የገንዘብ ቀውስ ገጥሞት እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ለጓደኞቿ ምንም ፍንጭም አልሰጠችም።
ጃዝቪን እንደ ወላጆቿ ስኬታማ ነጋዴ መሆን ትመኝ ነበር። ለአጭር ጊዜ የቆየ የጥፍር ማስዋቢያ ከፍታ ነበር።
በርካታ ቅርንጫፍ ያለው ሬስቶራንት ባለቤት መሆን እንደምትመኝ ለጓደኞቿ ነግራለች።
አብዛኛውን ጊዜዋን የምታሳልፈው የሙዚቃ ድግሶች በመታደም ነበር።
'ኪትንስ' በሚል ቅጽል ስም ከሚጠሩ ጓደኞቿ ጋር ታዋቂ ሰዎች የሚገኙባቸው ድግሶችን ያሰናዳሉ።
አቫሎን በሚባል ታሪካዊ ቴአትር ቤት ውስጥ ሙሉ ሌሊቱን የሚቆዩ የኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ ኮንሰርቶች ያዘጋጃሉ።
በኮንሰርቶቹ ላይ ካታሚንን ጨምሮ ሌሎች መድኃኒቶችንም ይወስዳሉ። አንዳንድ የሙዚቃ ድግሶች ለቀናት ይቀጥላሉ።
"ሐቫሱ ሐይቅ ሄደን ትልቅ ቤት እንከራያለን። እንዘንጣለን። ዲጄ ቀጥረን ሙሉ ሌሊቱን እንዝናናለን " ሲል ቶኒ ያስታውሳል።
እነዚህ ድግሶች ላይ ካታሚን መውሰድ የተለመደ ቢሆንም ያኔ ጃዝቪን 'የካታሚን ንግሥት' በሚለው መጠሪያ እንደማትታወቅ ያስታውሳል።
አደገኛ የሆኑት መድኃኒቶች ኦፒዮድ እና ፌንታኔል በሕገ ወጥ መንገድ መቅረባቸው ያሳስባቸው ስለነበር በሕጋዊ መንገድ ካታሚን ያገኙ እንደነበር ይናገራል።
ካታሚን የሚያገኙት "ከዋነኛው ምንጭ" እንደሆነም ቶኒ ጠቅሷል።
መድኃኒቱን የሚያገኙት ሜክሲኮ አዘውትረው ከሚሄዱ ሰዎች ነበር።
ካታሚን በቀዶ ሕክምና ወቅት ለማደንዘዣነት ይውላል። እንደ አደንዛዥ ዕፅ የሚጠቀሙበት ሰዎች መድኃኒቱን ከሙሰኛ ፋርማሲዎች ይሸምታሉ።
ቶኒ አሁንም ድረስ ጃዝቪን አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ እንደነበረች ማመን ይከብደዋል።
"እውነቱን ለመናገር አስደንጋጭ ነው። ለዓመታት አውቃታለሁ። ከየት እንደመጣች አውቃለሁ። ወላጆቿን አውቃለሁ። አሁንም ድረስ የተፈጠረውን ነገር ማመን ተስኖኛል።"
አሁን ላይ ሆኖ ሲያስበው ጃዝቪን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታዋቂ ከመሆን ጋር ሱስ እንደያዛት ይጠረጥራል። ከሃብታም እና ታዋቂ ሰዎች ጋር ለመቀራረብ ስትል አደንዛዥ ዕፅ ሽያጭ ውስጥ እንደገባች ያምናል።
"በቴሌቪዥን በሚታዩ ታዋቂ ሰዎች መከበብ እና መፈለግ ሱስ አስይዟታል ብዬ አምናለሁ። እንደ ሁላችንም ካታሚን መውሰድ ስለምትወድ ወደ ሽያጩ እንደገባች አስባለሁ። በስፋት መድኃኒቱን ትሸጥ እንደነበር ለመቀበል ይከብደኛል።"
እአአ በ2019 ኮዲ ማክላውሪ ለተባለ ግለሰብ ካታሚን እንደሸጠች እና ከልክ በላይ መድኃኒቱን ወስዶ እንደሞተ ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።
የኮዲ እህት ለጃዝቪን በላከችው የጽሑፍ መልዕክት መድኃኒቱ እንደገደለው ገልጻለች።
የቀድሞው የካሊፎርንያ ግዛት የወንጀል መርማሪ ማርቲን ኤስትራዳ "ጤናማ ሰው ይሄ መልዕክት ሲደርሰው ወደ ፖሊስ ይሄዳል፤ ሽያጩንም ያቆማል እንጂ ገበያውን አያስፋፋም" ይላሉ።
መርማሪው አክለውም "መድኃኒቱን መሸጥ ቀጠለች። ከዓመታት በኋላም ማቲው ፔሪ ሞተ" ብለዋል።
ጃዝቪንን ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ የሚያውቃት ሰው ለቢቢሲ እንደገለጸው፤ ዜናውን ሲሰማ ተደናግጧል።
"ለረዥም ዓመታት በየምሽቱ ድግስ ቤት እንገናኝ ነበር። ምንም መድኃኒት እንድወስድ ጠይቃኝ ግን አታውቅም" ብሏል።
ሁሉም ቦታ ስትሄድ ዘናጭ የሆነው አጎቷ ፖል ሲንግን እንደምትወስድ ያስታውሳል።
"ይሄ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ባህሪ አይመስልም" ይላል።
ፖል ሲንግ በጃዝቪን አብዛኞቹ ፎቶዎች ላይ ይታያል። ጥፋተኛ መሆኗን ስታምንም በፍርድ ቤት ተገኝቷል።
እአአ በ2020 የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኞች ማገገሚያ ገብታ ነበር። ለ17 ወራት ማንኛውንም አደንዛዥ ዕፅ አለመውሰዷን ጠበቃዋ ገልጸዋል።
ከጃዝቪን ጋር አብሮ ዩኒቨርስቲ የተማረው ጃሽ ነጋንዲ "ለመጨረሻ ጊዜ ሳገኛት ስለወደፊት ሕይወታችን ነው የተወያየነው" ይላል። በዛው ሰሞን ታስራ እንደነበር ለጃሽ አልነገረችውም።
ሁለቱም በ40ዎቹ ዕድሜ ክልል ስለሆኑ ስለ ሕይወታቸው በጥልቅ ያሰላስሉ እንደነበር ገልጿል።
"በዚህ ዕድሜ ላይ ሕይወትን መለስ ብሎ መቃኘት የተለመደ ነው። ከዚህ በኋላ ምን መሥራት አለብኝ? የሚለውን እናስባለን። አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ ካቆመች በኋላ የወደፊት ሕይወቷን በጉጉት ስትጠብቅ ነበር።"















