ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለክሪፕቶከረንሲ መገበያያ ስርዓት ባይናንስ መስራች ምህረት አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዓለማችን ትልቁ የክሪፕቶከረንሲ መገበያያ ባይናንስ መስራች ለሆነው ቻንግፔንግ ዣኦ ምህረት አደረጉ።
ዣኦ እአአ በሚያዝያ 2024 ላይ የአሜሪካን የገንዘብ ማጭበርበር ሕግን በመጣስ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የአራት ወራት እስራት ተፈርዶበት ነበር።
ባይናንስ ጥፋተኛ መሆኑን ያመነ ሲሆን የአሜሪካ መንግሥት ባደረገው ምርመራ ተጠቃሚዎች ማዕቀብን እንዲያመልጡ እገዛ ማድረጉ ስለተደረሰበት 4.3 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል ተወስኖበት ነበር።
ለዣኦ የተደረገው ምህረት የትራምፕ ቤተሰብ በኢንዱስትሪው ውስጥ መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰሳቸውን እንዲሁም ዋይት ሐውስ ክሪፕቶከረንሲን እየደገፈ መምጣቱን በመጥቀስ ክርክሮች ተነስተዋል።
የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት በባይደን አስተዳደር ስር የዣኦ ክስ የታየው "ክሪፕቶከረንሲ ላይ በተከፈተ ዘመቻ" ስር ነበር በማለት፣ ምህረት የተደረገለት በትራምፕ የግል የፋይናንስ ፍላጎት በመነሳሳት ነው ያሉ ተቺዎችን ውድቅ አድርገዋል።
"ይህ በባይደን አስተዳደር ከሚገባው በላይ ክስ የቀረበበት ነበር" በማለት ጉዳዩ "በጥልቀት ተገምግሟል" ሲሉ አብራርተዋል።
"ስለዚህ ፕሬዝዳንቱ ይህንን የባይደን አስተዳደር ኢ ፍትሃዊነት ማረም ይፈልጋሉ እና ይህን ለማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን ተጠቅመዋል።"
ባይናንስ በመስከረም 2024 የአራት ወራት የእስር ፍርዱን ለጨረሰው የቀድሞ ኃላፊው ምህረት ለማግኘት ለአንድ አመት ያህል ጥረት ሲያደርግ እንደነበር ዎል ስትሪት ጆርናል ሐሙስ ዕለት ዘግቧል።
ምህረት እነዲደረግለትየሚጠይቀው ዘመቻ የተጀመረው ዶናልድ ትራምፕ ሁለተኛውን የሥልጣን ዘመናቸውን ከመጀመራቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ነው።
ወቅት ዶናልድ ትራምፕ የራሳቸውን የክሪፕቶከረንሲ ገንዘብ ያስተዋወቁበት እና ከቀደምት አስተዳደር ይልቅ ለኢንዱስትሪው በጎ አቀራረብን እንደሚከተሉ ቃል በገቡበት ወቅት ነው።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ደንቦችን ያላሉ ሲሆን ብሔራዊ የክሪፕቶከረንሲ መጠባበቂያ ለመጀመር ፍላጎት እነዳላቸው እንዲሁም አሜሪካውያን የጡረታ ቁጠባቸውን በዲጂታል መገበያያዎች ላእ ኢንቨስት ለማድረግ ቀላል እነዲሆንላቸው ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ 2023 ዣኦ ከባይናንስ ዋና ሥራ አስፈፃሚነት የተነሱ ሲሆን ሐሙስ ዕለት በማኝበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ "ዛሬው ለተደረገልኝ ይቅርታ እና ለፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ ለፍትሃዊነት፣ ለፈጠራ እና ለፍትህ ያላትን ቁርጠኝነት ስላረጋገጡ በጣም አመስጋኝ ነኝ" ሲል ጽፏል።
ለዣኦ የተደረገው ምህረት የፋይናንስ ስራዎች ላይ እንዳይሰማራ የተጣለበትን እገዳዎች የሚያነሳ ቢሆንም ከአሜሪካ ተቆጣጣሪዎች ጋር ያለበትን ፍጥጫ ያነሳ ይሆን ወይም ባይናንስ ቀጥታ መምራት ያስችለው እንደሆን እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ባይናንስ በሰጠው መግለጫ ውሳኔውን "አስደናቂ ዜና" ሲል አሞካሽቶታል።
በኬይሜን ደሴቶች ተመዝግቦ የሚንቀሳቀሰው ባይናንስ የተለያዩ ክሪፕቶከረንሲዎችን እንዲሁም ዲጂታል ሃብቶችን ለመግዛትና ለመሸጥ ሰዎች የሚጠቀሙበት የዓለማችን ትልቁ መድረክ ነው።















