ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩዋንዳ ከአሜሪካ የሚባረሩ ስደተኞችን ለመቀበል ከትራምፕ ጋር ውይይት ጀመረች
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የሚያባርራቸውን ስደተኞች ለመቀበል ከአሜሪካ ጋር "የመጀመሪያ ደረጃ" ውይይት ላይ መሆኗን ሩዋንዳ አስታወቀች።
የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦሊቪየር ንዱንጊሪዬ እንዳሉት ከዚህ ቀደም ሩዋንዳ ከዩናይትድ ኪንግደም የሚባበበሩ ስደተኞችን ለመቀበል ውይይት ስታደርስ ስለነበር አሁን ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ውይይት እንግዳ ነገር አይደለም።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ማርኮ ሩቢዮ ባለፈው ወር ባደረጉት ንግግር አሜሪካ "በጣም መጥፎ የሆኑ ሰዎችን" የምታቆይበት አገራት እየፈለገች መሆኗን ተናግረው ነበር።
ዩናይትድ ኪንግደም ወደ ሩዋንዳ ስደተኞችን ለመላክ ያደረገችው ሙከራ በፍርድ ቤት ጥያቄ ስለተነሳበት የሰር ኪር ስታርመር ሌበር ፓርቲ ምርጫ ካሸነፈ በኋላ ዕቅዱ ሳይሳካ ቀርቷል።
የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦሊቪየር ንዱንጊሪዬ በቴሌቪዥን ቀርበው እንዳሉት መንግሥታቸው "በመላው ዓለም ችግር ለሚገጥማቸው ስደተኞች ሁለተኛ ዕድል መስጠት" ይፈልጋል።
ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ውይይት የመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንደሆነ እና ውጤቱን ለመተንበይ እንደማይቻል አክለዋል።
ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ቃል እንደገቡት፣ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአሜሪካ ማባረርን ዋነኛ የአስተዳደራቸው ትኩረት አድርገውታል።
ከወራት በፊት ኤል ሳልቫዶር አሜሪካውያን ዜጎችን ጨምሮ ከአሜሪካ የሚባረሩ ወንጀለኞችን በግዙፍ እስር ቤት ለማቆየት ጥያቄ አቅርባ ነበር።
የኤል ሳልቫዶር ፕሬዝደንት ናይብ ቡኬሌ እንዳሉት ለዚህ አገልግሎት አገራቸው የሚከፈላት ይሆናል።
ፓናማ እና ኮስታ ሪካም ከአሜሪካ የተባረሩ ስደተኞችን ተቀብለዋል።
ባለፈው ሳምንት ስማቸው ያልተጠቀሰ የሩዋንዳ ባለሥልጣን ከአሜሪካ የሚባረሩ ስደተኞችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከአንድ ወር በፊት ኢራቃዊ ስደተኛን መቀበላቸው ይታወሳል።
እኚሁ ባለሥልጣን ከአሜሪካ ጋር ውይይት የተጀመረው ትራምፕ ሥልጣን መያዛቸውን ተከትሎ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሩዋንዳ በሰብአዊ መብት አያያዝ ትችት ይሰነዘርባታል። ወደ ሩዋንዳ የሚወሰዱ ስደተኞች ወደመጡበት አገር በግዳጅ እንደሚመለሱ እና ለእንግልት እንደሚዳረጉም የመብት ተሟጋቾች ሲናገሩ ቆይተዋል።
ሩዋንዳ ግን ለስደተኞች ደኅንነቷ የተጠበቀ አገር መሆኗን በተደጋጋሚ ትገልጻለች።