‘የሥራ ሕይወቴን አበላሽተዋል’ ያላቸውን ሦስት ግለሰቦች የገደለው ፍርድ ቤት ቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፈረንሳይ ‘የሥራ ሕይወቴን አበላሽተዋል’ በሚል ቂም ሦስት የሰው አስተዳደር ኃላፊዎች የሆኑ ሴቶችን የገደለው ግለሰብ ፍርድ ቤት ቀረበ።
የ48 ዓመቱ ገብሪኤል ፎርቲን በቁጥጥር ሥር የዋለው እአአ 2021 በደቡባዊት የፈረንሳይ ውስጥ በምትገኘው ቫለንስ ከተማ ነበር።
ግለሰቡ በቂም በቀል ተነሳስቶ ከረዥም ዓመታት በፊት ከሥራው ያሰናበቱትን ወይም ሥራ እንዳያገኝ ምክንያት ናቸው ያላቸውን የሰው ሃብት አስተዳደር ኃላፊዎችን በጥይት ገድሏል የሚል ክስ ቀርቦበታል።
‘ኤች አር (የሰው ሃብት አስተዳደር ኃላፊ) ገዳይ’ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ግለሰብ ከገደላቸው ሦስት ሴቶች በተጨማሪ ሌላ አራተኛ ሰው ለመግደል ሙከራ አድርጓል።
በቁጥጥር ሥር ሲውል ሥራ አጥ የነበረው መሃንዲስ፣ ከመርማሪዎች ጋር አልተባበርም በማለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሊሰጥ ፍቃደኛ አይደለም ተብሏል።
የመጀመሪያው ግድያ የተፈጸመው 2021 መጀመሪያ ወር ላይ ሲሆን፣ ኤስቴሌ ሉስ የተባለችውን ግለሰብ ጭንቅላቷን በጥይት መትቶ ነበር የገለደው።
በዚያው ተመሳሳይ ምሽት 50 ኪሎ ሜትሮችን ተጉዞ ሁለተኛዋን ግለሰብ ለመግደል የፒዛ አድራሽ ምስሎ የሰው ሃብት አስተዳደር ኃላፊን በመኖሪያ ቤቱ ቢመታም ይህ ግለሰብ ከሞት ተርፏል።
እነዚህ ሁለት ግለሰቦች ላይ ወንጀል ከፈጸመ በኋላ ወደ ፈረንሳይ ደቡባዊ ክፍል 500 ኪሎ ሜትር ተጉዞ የሥራ ቅጥር ወደሚካሄድበት ማዕከል በመግባት ፓትሪሺያ የተባለች ሴትን በጥይት መትቶ ገድሏል።
እንዲሁም በደቂቃዎች ልዩነት አራተኛዋን ግለሰብ በጥይት መትቶ ገድሏል።
ግለሰቡ የሰው ሃብት አስተዳደር ኃላፊዎችን ዒላማ ያደረገው የቅጥር የሙከራ ጊዜው ውጤታማ ሳይሆን ቀርቶ ከሥራ ስላባረሩት፣ እንዲሁም ከሥራ ቅጥር ማዕከል ያገኝ የነበረው ጥቅማ ጥቅም በማብቃቱ ነው ተብሏል።
በግለሰቡ ዒላማ ከተደረጉት አራት ግለሰቦች ሁለቱ ከ14 ዓመታት በፊት ከሌላ ኩባንያ እንዲባረር ምክንያት እንደነበሩ ጭምር ተነግሯል።
ፖሊስ በወንጀሉ የተጠረጠረውን ግለሰብ ላፕቶፕ ከሁለት ዓመታት በላይ ሲመረምር ቆይቶ ገብርኤል ፎርቲን የሥራ ኃላፊዎቹ ላይ ቂም ከመቋጠር አልፎ መውጫ መግቢያቸውን ሲከታተል ስለመቆየቱ ከበቂ በላይ ማስረጃ አግኝቻለሁ ብሏል።
ዛሬ ማክሰኞ በፈረንሳይዋ ቫሌንስ ከተማ በሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረበው ገብርኤል ፎርቲን በሦስት ሰዎች ግድያ እና በአንድ የግድያ ሙከራ ክስ ቀርቦበታል።












