የደቡብ አፍሪካ ገዢ ፓርቲ የጋራ ብሔራዊ መንግሥት ለመመስረት ጥሪ አቀረበ

 የኤኤንሲ ቃለ አቀባይ ማህሌንጊ ብሄንጉ ሞትሲሪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ባለፈው ሳምንት በተደረገው ታሪካዊ ምርጫ አብላጫ ድምጽ በፓርላማ ያጣው የደቡብ አፍሪካ ገዢ ፓርቲ የአፍሪካ ናሺናል ኮንግረስ (ኤኤንሲ) የጋራ ብሔራዊ መንግሥት የመመስረት ሃሳብ አቀረበ።

ለሁሉም ፓርቲዎች ጥሪ ማድረጉን ያስታወቀው ፓርቲው ነገር ግን ድርድሮች እየተካሄዱ ነው ብሏል።

“የምርጫው ውጤቶች ደቡብ አፍሪካውያን ሁሉም ፓርቲዎች እንዲተባበሩ ይፈልጋሉ” ሲሉ የኤኤንሲ ቃለ አቀባይ ማህሌንጊ ብሄንጉ ሞትሲሪ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በምርጫው ኤኤንሲ 40 በመቶ ድምጽ ሲያገኝ በመከተልም ዲሞክራቲክ አሊያንስ 22 በመቶ ድምጽ ማግኘት ችሏል̄።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ፓርቲ ኡምኮንቶ ዊሲዝዌ (ኤምኬ) 15 በመቶ እና ሥር ነቀል ለውጥ በአገሪቱ ሊመጣ ይገባል የሚለው የጁሊየስ ማሌማ ኢኤፍኤፍ 9 በመቶ በማግኘት ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የዘረኛው አፓርታይድ ስርዓት ማክተም ተከትሎ በትግሉ ወደ ስልጣን በአውሮፓውያኑ 1994 ወደ ስልጣን የመጣው ኤኤንሲ አገሪቷን በበላይነት ሲመራ ቆይቷል።

ከነጻነት በኋላ በተደረገው ምርጫ ኔልሰን ማንዴላን ወደ ስልጣን ያመጣው ዲሞክራሲያዊ ምርጫን ተከትሎም ለሶስት አስርት ዓመታት አገሪቷን የመራው ኤኤንሲ በፓርላማ ያለው አብላጫ ድምጽ ሲያጣ የመጀመሪያው ነው።

በደቡብ አፍሪካ የፖለቲካ ስርዓት መሰረት ፓርቲዎች መንግሥት ለመመስረት ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።

ቃለ አቀባይዋ ማህሌንጊ ብሄንጊ እንዳሉት ፓርቲያቸው ከዲኤ፣ ከኢኤፍኤፍ እና ከሌሎች ትናንሽ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

ለዙማ ፓርቲ ኤምኬ ጥሪ ቢያደርጉም አዎንታዊ ምላሽ እንዳልተገኘ ገልጸዋል።

የኤኤንሲ ቃለ አቀባይ አክለውም ፓርላማው ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከመሰብሰቡ በፊትም ለዚህ እልባት ማበጀት ይፈልጋል ብለዋል።

የመጀመሪያው ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ለሚመሰረተው መንግሥት ፕሬዚዳንት መምረጥ ነው። የምርጫው ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ በደቡብ አፍሪካ ምን አይነት የጥምር መንግሥት ሊመስረት ይችላል የሚሉ ጉዳዮች መነጋገሪያ መሆናቸው ቀጥሏል። ኤኤንሲ የጋራ ብሄራዊ መንግሥት ለመመስረት ሃሳብ ማቅረቡ ከገባበት አጣብቂኝ ውስጥ ያወጣዋል ተብሏል።

አናሳ ነጮችን ይወክላል ከሚባለው ከዲኤ ጋር ጥምረት መፍጠሩ በርካታ የፓርቲውን አባላት ሊያስቆጣ እንደሚችል ይገመታል።

የቀኝ ፖለቲካ የሚያራምደው ዲሞክራቲክ አሊያንስ በከፍተኛ ሁኔታ የሕዝብን የልማት ተቋማት ወደ ግል የማዛወር (ፕራይቬታይዜሽን) በመደገፍ እንዲሁም ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወገድም የሚጠቅሱ ፖሊሲዎች አሉት።

ለኤኤንሲ በዘረኛው አፓርታይድ ዘመን ሰውነትን የተነፈጉ እንዲሁም በምጣኔ ኃብት የተገለሉ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን የማብቃት ስራው “መደራደር የማይችልበት” ፖሊሲው ነው። ሌላኛው በቅርቡ በህግነት የጸደቀውን የብሔራዊ የጤና መድህን ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ነው።

ዲኤ የጤና መድህንንም ሆነ የኤኤንሲን ጥቁሮችን የማብቃት ፖሊሲውን ይቃወማል።

አርማ