አወዛጋቢው የሙሴቪኒ ልጅ ፕሬዝዳንት እሆናለሁ ሲሉ ቃል ገቡ

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ልጅ የአባታቸውን የስልጣን መንበር ለመረከብ ያላቸውን ፍላጎት ገለፁ።

ጄነራል ሙሆዚ ካያኔሩጋባ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ እናታቸውን ፕሬዝዳንት በመሆን እንደሚክሷት በመግለጽ ጽፈዋል።

ኡጋንዳን ለረዥም ዓመታት ያስተዳደሩት ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ልጅ፣ የአባታቸው ሥልጣን ወራሽ ናቸው የሚለውን ጥርጣሬ የሚያረጋግጥ መልዕክት ማስፈራቸው ብዙዎችን አስደንቋል።

ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ እኤአ ከ1986 አንስቶ በስልጣን ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ልጃቸው ጄነራል ሙሆዚ የስልጣናቸው ወራሽ ናቸው የሚለው አሉባልታ ለረዥም ጊዜ ሲወራ ቆይቷል።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ጄነራል ሙሆዚ በትዊተር ገጻቸው ላይ ሰዎች ፕሬዝዳንት መሆን እንዳለባቸው ያስቡ አንደሆን ጠይቀው ነበር።

በድጋሚ በዚህ ወር ደግሞ “ለኡጋንዳ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ከአባቴ በኋላ በማንኛውም ምርጫ በዝረራ አሸንፋችኋለሁ። ኡጋንዳውያን እናንተን ከሚወዱት በላይ እኔን ይወዱኛል” ሲlu ጽፈዋል።

የ48 ዓመቱ ጄኔራል በትዊተር ላይ በሚለጥፏቸው መልዕክቶች መነጋገርያ ከመሆን ታቅበው አያውቁም።

በጥቅምት ወር መጀመርያ ላይ ኬንያን ለመውረር ዝተው፣ አገራቸው ኡጋንዳ በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ ከአገሪቱ ጋር ያላትን ጠንካራ ትስስር እንድታረጋግጥ አስገድደዋል።

ከዚህ በኋላም አወዛጋቢው የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ልጅ ሌፍተናንት ጄኔራል ሙሆዚ ካይኒሩጋባ ከአገሪቱ የምድር ጦር ኃይል አዛዥነት ሥልጣናቸው ተነስተዋል።

ከዚህ በኋላም አባታቸው ፕሬዝዳነት ሙሴቪኒ በመንግሥት ጉዳዮች ዳግም ትዊት እንደማያደርግ የገለፁ ቢሆንም ወድያውኑ “ማንም ምንም ነገር ከማድረግ አያግደኝም” ሲሉ ጄኔራሉ ትዊተር ጽፈዋል።

ጄኔራሉ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን የተመለከተ በተለይ ደግሞ ከትግራይ ጋር የተያያዙ አስተያየቶችን ሲሰጡ ነበር።

የኢትዮጵያው የእርስ በእርስ ጦርነት አንድ ዓመት በደፈነበት ጥቅምት 2014 ዓ.ም. ላይ የትግራይ ኃይሎችን ደግፈው ትዊት አድርገው ነበር።

“የትግራይ መከላከያ ኃይሎች . . . የቆማችሁበትን ዓላማ እደግፋለሁ። የትግራይ እህቶቻችንን የደፈሩ እና ወንድሞቻችንን የገደሉ መቀጣት አለባቸው” ሲሉ ጽፈው ነበር።

የጄኔራል ሙሆዚ ትዊት ተከትሎ የኡጋንዳ መንግሥት አስተያየቱ የጄኔራሉ እንጂ የጦሩን አቋም አይወክልም የሚል ማስተባበያን ሰጥቶ ነበር።

በተጨማሪም ጄኔራሉ ከአገራቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ከጥቂት ወራት በፊት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋርም ተገናኝተው ነበር።

መስከረም 22/2015 ዓ.ም. በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሳፈሩት ጽሑፍ፤ “ትግራይ ሁሌም በልቤ አለች! ትግራይን እንድወድ እና እንድከላከል ከፈጣሪዬ ከእየሱስ ክርስቶስ የመጣ ትዕዛዝ ነው” ብለዋል።

በተመሳሳይ ዕለት ከሰዓታት በኋላ ደግሞ ጄኔራሉ ኢትዮጵያን በተመለከተ ባሰፈሩት ሌላኛው ጽሑፍ፤ “ዳግማዊ ሚኒሊክ አያታችን ናቸው። ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ አካል ናት። እንድትወድም አንፈቅድም። ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንወዳለን!” ሲሉ ጽፈዋል።