ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በምስራቅ ወለጋ አምስት ሰዎች በ'ጽንፈኛ ታጣቂዎች' መገደላቸው ተነገረ
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ “ጽንፈኛ የአማራ ታጣቂዎች” ፈጽመውታል በተባለ ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።
አርብ መስከረም 4/2015 ዓ.ም. በሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ከተገደሉት አምስት ሰዎች በተጨማሪ ቢያንስ አራት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ቢቢሲ ከአካባቢው ባለስልጣን እና የሆስፒታል ምንጮች ሰምቷል።
የምስራቅ ወለጋ ዞን የአስተዳደር እና ጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ለሜሳ ዴሬሳ ጥቃቱ በጊዳ አያና ወረዳ አንዶዴ ዲቾ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ በሰላማዊ ሰዎች ላይ መፈጸሙን ተናግረዋል።
“የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ፣ ተሳፋሪዎችን ጭኖ ከአንገር ጉቴ ወደ ጊዳ አያና እየተጓዘ ሳለ ነው ጥቃቱ የተፈጸመው” ብለዋል።
ኮሎኔል ለሜሳ ይህን ጥቃት የፈጸሙት በክልሉ ውስጥ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ “ጽንፈኛ የአማራ ታጣቂዎች” ናቸው ብለዋል።
“በዚህ አካባቢ ታጥቀው እየተንቀሳቀሱ የአካባቢውን ሰላም የሚያውኩ ጽንፈኛ ታጣቂዎች አሉ። እነዚህ ጽንፈኞች የሕዝብ ማመላለሻ መኪና መንገድ ላይ አስቁመው ችግር ፈጥረዋል” ብለዋል።
ምንም እንኳ ኃላፊው ይህንን ቢሉም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ጥቃቱን ያደረሱት የመከላከያ አባላት ናቸው ብሏል።
ፓርቲው ግድያው በተፈፀመበት ዕለት ባወጣው መግለጫ እንዳለው የመከላከያ ሠራዊት አባላት በጉዞ ላይ የነበሩ ሠላማዊ ዜጎች ላይ በመተኮስ ጥቃት አድርሰዋል።
አክሎም “ፋኖ የሚል ስምን እንደ ጭምብል ተጠቅመው በብልጽግና ፓርቲ የሚመራ የአገር መከላከያ ኃይል. . . የፈጸመውን የጅምላ ግድያ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አጥብቆ ይቃወማል” ብሏል።
የጸጥታ ኃላፊው እና ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሆስፒታል ምንጭ የሟቾች ቁጥር 5 ነው ይበሉ እንጂ፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በዚህ ጥቃት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 31 መሆኑን የሚገልጹ በርካቶች ናቸው።
ኮሎኔል ለሜሳ “የሞቱት አምስት ናቸው። አራት ደግሞ በሆስፒታል ይገኛሉ” ብለዋል።
በዚህ ጥቃት ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና በተወሰዱበት የጊዳ አያና ሆስፒታል ሠራተኛ እንዲሁ የሟቾችን ቁጥርን በተመለከተ ከዞኑ ኃላፊ ጋር ተመሳሳይ ቁጥር ሰጥተዋል።
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የጤና ባለሙያ “መጀመሪያ ላይ አምስት ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ እኛ መጡ። ለእነርሱ አስቸኳይ ሕክምና ካደረግን በኋላ የአራት ሰዎች አስክሬን መጣ” ያሉ ሲሆን ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ጊዳ አያና ሆስፒታል ከመጡት መካከል የአንዱ ሕይወቱ ማለፉን እኚህ የጤና ባለሙያ ተናግረዋል።
ሐኪሙ በአሁኑ ወቅት በሆስፒታላቸው ሕክምና እያገኙ ያሉት አራት ሰዎች መሆናቸውን እና ከእነዚህ መካከል ሦስቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።
የጤና ባለሙያው ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሕይወታቸው ያለፈውም ሆኑ ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎች በሙሉ ወንዶች መሆናቸውን እና ሁሉም ተጎጂዎች በጥይት የተመቱ መሆናቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ሦስቱ ከባድ ጉዳት ደርሶባቾዋል። ለተሻለ ሕክምና ወደ ሌላ የጤና ተቋም መንገዱ ሰላም ስላልሆነ መላክ አይቻልም። ከደረሰባቸው ከፍተኛ ጉዳት አንጻር በእኛ አቅም ማከም አንችልም። የደም እጥረትም አለብን” ብለዋል።
ጥቃት አድራሾቹ እነማን ናቸው?
የምስራቅ ወለጋ ዞን የአስተዳደር እና ጸጥታ ኃላፊ ኮሎኔል ለሜሳ እንደሚሉት ጥቃቱ በተፈመጸበት እና በሌሎች አካባቢዎችም 'ጽንፈኛ የአማራ ታጣቂዎች' በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ እና ማፈናቀል እያደረሱ ነው ይላሉ።
ኃላፊው ከእነዚህ ኃይሎች በተጨማሪ መንግሥት ሸኔ የሚለው እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን በአካባቢው ሰላም ለማምጣት እና የልማት ስራዎችን ለማከናወን የሚደረገውን እያወኩ ነው ይላሉ።
ኃላፊው እንደሚሉት ትናንት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የከፈቱት ታጣቂዎች ከአማራ ክልል የተሻገሩ ሳይሆኑ በዞኑ ነዋሪ የሆኑ ታጣቂዎች ናቸው ይላሉ።
“ተሻግሮ የመጣ ጠላት የለም። በረሃማ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች አሉ። እነርሱ ውስጥ በአነስተኛ ቁጥር ተደራጅተው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አሉ” ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ መስከረም 3/2016 ዓ.ም. ትናንት ጥቃቱ ባጋጠመበት አካባቢ የሕዝብ ማመላለሽ ተሸከርካሪዎችን ዒላማ ያደረገ ዘረፋ ሲከናወን እንደነበር አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።
“እኔ ራሱ ተዘርፌያለሁ። ታጣቂዎቹ ንብረት ሲዘርፉ ነበር። እኔን ወደ ጫካ ወስደውኝ በኪሴ የነበረውን ገንዘብ እና ሞባይል ስልክ ወሰዱብኝ” ሲሉ ለቢቢሲ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
እኚህ ነዋሪ እንደሚሉት ታጣቂዎቹ ከሁለት የሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች ላይ ተሳፍረው ከነበሩ ሰዎች ላይ ዘረፋ ፈጽመዋል።