በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ወንድማቸውን የገደሉት እህትማማቾች በእስራት ተቀጡ

የፎቶው ባለመብት, West Arsi Zone Police
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን አዳባ ወረዳ አዳባ ከተማ ውስጥ ወንድማቸውን የገደሉ ሁለት እህትማማቾች እስራት ተፈረደባቸው።
ፍርደኞቹ ተሚማ ከማል እና አራቤ ከማለ የተባሉ እህትማማቾች ሲሆኑ፣ ከወንድማቸው ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ግድያውን መፈጸማቸው ተገልጿል።
ጉዳዩን የተመለከተው ችሎት የቀረቡለትን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን መሠረት አድርጎ በሁለቱ ተከሳሾች ላይ የ18 ዓመት ጽኑ እስራት በይኗል።
በፍርድ ቤት ጥፈተኛ ሆነው የተፈረደባቸው ተሚማ እና አራቤ ወንጀሉን ቀደም ሲል የተፈጠረን ግጭት ምክንያት አድርገው በቂም በቀል ወንድማቸው ላይ መስከረም 14/2016 ዓ.ም. የግድያ ወንጀሉን እንደፈጸሙ ፖሊስ ለቢቢሲ ተናግሯል።
“ሁለቱ ወንጀለኞች በግል ጸብ ምክንያት ወንድማቸውን ለመግደል አቅደው የግል ተበዳይ በተኛበት ጭንቅላቱ ላይ በተደጋጋሚ በዱላ ደብድበው መግደላቸው ተረጋግጦባቸዋል” ሲሉ የምዕራብ አርሲ ዞን ፖሊስ ባልደረባ የሆኑት ምክትል ኢንስፔክተር አሕመድ ጣቃሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በመካከለቸው አለመግባባት ነበረ። በዚህ ምክንያት እህቶቹ ቂም በቀል ቋጥረው ነበር። ወንድማቸውን ለመግደል አቅደው በዕለቱ ምሽት 2 ሰዓት አካባቢ በመኖሪያ ቤቱ በተኛበት ወንጀሉን ፈጽመውበታል” ብለዋል የፖሊስ ባልደረባው።
እህትማማቾቹ ወንጀሉን ከፈጸሙ በኋላ በፖሊስ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል።
ዐቃቤ ሕግም ወንጀል ከተፈጸመበት ስፍራ የተገኘውን ማስረጃ እና የአስክሬን ምርመራ ውጤት በመያዝ በአገሪቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 32/1 (ሀ) እንዲሁም አንቀጽ 539/1 (ሀ) በሁለቱ ሴቶች ላይ ክስ መሠርቷል።
በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በዋለው ችሎት የቀረበለትን የሰው እና የሰነድ ማስረጃ መርምሮ የፍርድ ውሳኔ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ጥቅምት 09/2016 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ተሚማ ከማል እና አራቤ ከማል እያንዳንዳቸው በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል።
የፖሊስ አባሉ ምክትል ኢንስፔክተር አሕመድ ጣቃሳ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ውሳኔ ለሌሎች አስተማሪ መሆኑን ጠቅሰው በቤተሰብ መካከል አለመግባባት ሲፈጠረ አለመግባባቱን በንግግር ለመፍታት ቅድሚያ መሰጠት አለበት በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።












