አሜሪካ የኢራን ጦርነት ግቦቿን አሳክታለች?

የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱበት የመጀመሪያው ሳምንት አንስቶ የዋሽንግተኑ ወታደራዊ መሥሪያ ቤት ፔንታገን የጦርነቱን ሂደት በተመለከተ የተለያዩ ትርክቶችን ሲያቀርብ ሰንብቷል።

የዓለማችንን ግዙፍ ወታደራዊ ኃይል የሚመሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጡበት አኳኋን ወደ ሥልጣን ሳይመጡ በፊት ፎክስ ኒውስ ላይ ትንተና ከሚያቀርቡበት መንገድ የተለየ አይደለም።

የአሜሪካን በጦርነቱ ለማሳከት የወጠነቻቸውን ግቦች ከገለጹበት የመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ እስከ ሰጡት ማብራሪያ ድረስ ገለጻዎቻቸው የአሜሪካን ወታደራዊ የበላይነት የሚያሳዩ ነበሩ።

ስለ ጦርነቱን ሂደት እና አሜሪካን ስላስከፈለውን ዋጋ እውነቱን ለመረዳት ጥልቅ ምርመራ ማድረግ ይጠይቃል። ከአሁኑ ፈተና እያስተናገደ ያለው ተኩስ አቁም ተግባራዊ እየሆነ ባለበት በዚህ ጊዜ አሜሪካ ምን አሳካች? ዋጋውስ ምን ነበር?

ብዙም ፈቀቅ ያላለው የኒውክሌር ጉዳይ

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጦርነቱ የያዙት ዋነኛ ግብ ኢራን ኒውክሌር መሣሪያ ለማምረት የሚያስችል አቅም እንዳይኖራት ማድረግ ነው። ኢራን ከጅምሩም ይህንን ዓይነቱን መሣሪያ የመታጠቅ ዕቅድ እንደሌላት ስትገልጽ ቆይታለች።

ይህ ግብ ለረጅም ዓመታት አሜሪካ መሩ ዲፕሎማሲ እንዲሳካ ጥረት ሲደረግበት የነበረ ነው። በአውሮፓውያኑ 2015 በቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ መሪነት ከኢራን ጋር ዓለም አቀፍ የኒውክሌር ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።

ቀጥሎ ሥልጣኑን የተረከቡት ትራምፕ ግን ደካማ ስምምነት ነው የሚል እምነት ነበራቸው። በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ስምምነቱን በመጣስ ለውሉ እየተገዛች በነበረችው ኢራን ላይ በድጋሚ ማዕቀብ ጥለዋል። ይህ እርምጃቸውም አሜሪካ ከስምምነቱ እንድትወጣ አድርጓል።

በዚህ ውሳኔያቸው ከዲፕሎማሲ ይልቅ ኃይልን የመረጡት ትራምፕ፤ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው መገባደጃ ላይ ደግሞ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አዛዥ ጄነራል ቃሲም ሱሌይማኒን ገድለዋል።

እነዚህ እርምጃዎቻቸው ከቴህራን ጋር የሚደረገውን ግንኙነት በዲፕሎማሲያዊ ጥረት እና በወታደራዊ ኃይል መካከል እንዲዋልል ምክንያት ሆኗል። የአሁኑ ጦርነት እንዲነሳ ያደረገውም ይህ ዓይነቱ አካሄድ ነው።

ከ40 ቀናት ጦርነት በኋላ በደንብ ያልጠነከረው ተኩስ አቁም መተግበር ቢጀምርም፤ እስካሁን ድረስ ትራምፕ በኒውክሌር ጉዳይ ጉልህ ውጤት እንዳገኙ የሚያመለክት ማስረጃ የለም።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ በተካሄደው የ12 ቀናት ጦርነት ወቅት በኢስፋሃን፣ ፎርዶው እና ናታንዝ ውስጥ በሚገኙ የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ አሜሪካ በፈጸመቻቸው ድብደባዎች የኢራን የኒውክሌር አቅም መውደሙን ትራምፕ ተናግረው ነበር።

ከዘንድሮው የአምስት ሳምንታት ጦርነት በኋላም፤ አሁንም ኢራን ፍርስራሽ ሥር በጋዝ ሲሊንደሮች እንደተቀመጠ የሚገመት የጦር መሣሪያ ደረጃ ላይ ለመድረስ ትንሽ የቀረው የዩራኒየም ክምችት አላት።

በጦርነት ሦስተኛ ሳምንት ላይ የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ድርጅት ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ፤ የኢራንን የኒውክሌር ፍላጎት ሊገታ የሚችል ወታደራዊ አማራጭ ሊኖር እንደማይችል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ "ጠልቀው ተቀበሩትን ሁሉንም የኒውክሌር ግብዓቶች ቆፍሮ ለማውጣት እና ለማስወገድ ከኢራን ጋር" እንደምትሠራ ገልጸዋል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ቴህራን በዚህ ጉዳይ በእምቢተኝነቷ ቀጥላለች።

በቀጣይ ቀናትም ይኸው ጉዳይ በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ የሚደረገው የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር አንዱ ዋነኛ ነጥብ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ከቀድሞውም የበለጠ ተጠራጣሪ አመራር የያዘቸው ኢራን፤ በድጋሚ በአሜሪካ ጥቃት እንዳይፈጸምባት ለመከላከል ስትል የኒውክሌር አቅሟን ለማጎልበት ያላት ፍላጎት ሊጨምር እንጂ ሊቀንስ አይችልም የሚል መከራከሪያ የሚያነሱ አሉ።

የኢራንን የመሣሪያ ክምችት ማዳከም

ትራምፕ ከማር ኣ ላጎ መኖሪያቸው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ጦርነቱ መጀመሩን ሲያውጁ ካስቀመጧቸው ግቦች አንዱ በኢራን የአገዛዝ ለውጥ ማምጣት የሚለው ነው።

በወቅቱ አሜሪካ እና እስራኤል የሚፈጽሙት ድብደባ ሲያቆም ኢራናውያን መንግሥታቸውን እንዲቆጣጠሩ ጥሪ አቅርበው ነበር።

ከቀናት በኋላ ደግሞ አገዛዙ "ያለቅድመ ሁኔታ እጅ እንዲሰጥ" ጠይቀዋል፤ ሊሆን አልቻለም እንጂ። እስራኤል ጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ አመራሮችን ብትገድልም የቀድሞው መሪ ልጅ ሞጅታባ ኻሜኒ ተተኪ ሆነው ተመርጠዋል።

ትራምፕ፤ አዲሱ አመራር ከቀድሞው አንጻር "አክራሪነቱ የቀነሰ እንዲሁም እጅግ ብልህ" እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

የአሜሪካ ኃይሎች ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ከአገራቸው አፍነው በመውሰድ በኒው ዮርክ እስር ቤት ያስገቡበት እንዲሁም የአገሪቱ አመራር ለዋሽንግተን ፍላጎት ታዛዥ ያደረጉበትን የቬንዙዌላ ጥቃት ኢራን ላይ እንደሚደግሙት ተስፋ አድርገው ነበር። ይህ ዓይነቱ ነገር ኢራን ውስጥ ስለመሆኑ እስካሁን አንድም ማስረጃ የለም።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤ አሜሪካ የኢራንን የሚሳዔል፣ የማስወንጨፊያ፣ የድሮን፣ የመሣሪያ ማምረቻ እና የባሕር ኃይል አቅሞች "መደምሰሳቸውን" ይናገራሉ።

ስለ ኢራን ሚሳዔል እና ድሮን ክምችት የተሰጠው ገለጻ ግን ሾልኮ በወጣ የስለላ መረጃ የተነሳ አጠራጣሪ ሆኗል።

የስለላ መረጃው እንደሚያመለክተው ኢራን ከጦርነቱ በፊት ከነበራት የመሣሪያ ክምች ውስጥ ግማሽ ያህሉን እንደያች ናት። ቢቢሲ እነዚህ ሁለቱንም መከራከሪያዎች በራሱ አላረጋገጠም።

ይህም ሆነ ያ ግን፤ የትራምፕ አስተዳደር በጦርነቱ መጀመሪያ አስቀምጦት የነበረውን ግብ በሂደት ቀይሯል። አሜሪካ እና እስራኤል የያዙት የአገዛዝ ለውጥም ተግባራዊ መሆን አልቻለም።

የጦርነቱ ዋጋ

በዚህ ጦርነት 13 የአሜሪካ ወታደሮች ተገድለው በመቶዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቶማሃውክ ሚሳዔሎችን ጨምሮ በርካታ ተተኳሾች በከፍተኛ ፍጥነት ጥቅም ላይ እንደዋሉ ተነግሯል። የጦርነቱ አንድ ቀን ወጪ በቀን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነም ይገመታል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ለንጽጽር የማይቀርበው በአገራቸው ወታደራዊ ክህሎት እና የቴክኖሎጂ የበላይነት የአየር ጥቃቱ ከታቀደለት ጊዜ በፊት እንዲጠናቀቀ እንዲሁም ኢራን እጅ እንድትሰጥ ማስገደዱን ይናገራሉ።

አገር ውስጥ ደግሞ ጦርነቱ ትራምፕን ፖለቲካዊ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። የሕዝብ አስተያየት ዳሰሳዎች እንደሚያመለክቱት ጦርነቱን የሚደግፉ አሜሪካውያን ቁጥር አነስተኛ ነው።

ትራምፕ በኮንግረስ ያላቸው ድጋፍ በፓርቲ አጋርነት የተከፈለ ነው። አብረዋቸው የቆሙት ሪፐብሊካኖች ናቸው።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ እንዲያውም ትራምፕ ኢራንን ሙሉ ሥልጣኔ እንደሚያወድሙ መዛታቸውን ተከትሎ አንዳንድ የፓርቲ አጋሮቻቸው በግልጽ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እንደ የፖድካስት አቅራቢ እና ጋዜጠኛው ታከር ካርልሰን ያሉ የ'ማጋ' እንቅስቃሴ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አቋማቸው ከትራምፕ ጋር የተቃረነ ሆኗል።

ትራምፕ እሁድ ዕለት የኢራንን መሠረተ ልማቶችን እንደሚያወድሙ በመዛት ሁኔታውን ካባባሱት በኋላ ከዚህ ቀደም ደጋፊያቸው ከነበረችው እና ኋላ ላይ ግን ከተለየቻቸው ማርጆሪ ቴይለር ግሪንም ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

የቀድሞዋ የኮንግረስ አባል "ይህ አሜሪካን ዳግም ታላቅ ማድረግ አይደለም፤ ይህ ክፋት ነው" ብላለች። እነዚህ ስንጥቃቶች የትራምፕ እንቅስቃሴ ካጋጠመው ስብራት እያገገመ መሆኑን አያመለክቱም።

ዴሞክራቶችም እየጨመረ የመጡት የትራምፕ ጫፍ የረገጡ ዛቻዎች እንዲሁም አገራት ላይ የሚሰነዝሯቸው ስድቦች በእኩል መጠን አበሳጭቷቸዋል።

ጦርነቱ የመጀመሪያ ቀን በሚናብ ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ ለተፈጸመው እና 110 ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 168 ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት የተፈጸመው በአሜሪካ ሚሳዔል ስለመሆኑ እና አለመሆኑ የትራምፕ አስተዳደር ምላሽ እንዲሰጥ አሳስበዋል።

ሕጻናት ተማሪዎች የተገደሉበት ይህ ጥቃት የተፈጸመው በአሜሪካ መሆኑ ከተረጋገጠ በመካከለኛው ምሥራቅ በአሜሪካ ጥቃት ከደረሱ እጅግ የከፉ የሲቪል ጉዳቶች አንዱ ይሆናል።

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታገን) ለስድስት ሳምንታት ያህል ጉዳዩን እየመረመረ መሆኑን ሲገልጽ ቢቆይም እስካሁን ምንም መረጃ አላወጣም።

በዚህ ሳምንት በርካታ ሕግ አውጪዎች የትራምፕ ካቢኔ አባላት በሥልጣን ላይ ያለ ፕሬዝዳንት እንዲነሳ የሚያደርገውን ሕግ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

አስተዳደሩ በበኩሉ የትራምፕ ዛቻ ኢራን እንድታፈገፍግ ማድረጉን ይናገራል። የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሪታሪዋ ካሮሊን ሌቪት "የፕሬዝዳንት ትራምፕን የአሜሪካን ጥቅም በስኬት የማስከበር እና ሰላምን የማምጣት ብቃት በጭራሽ እንዳትጠራጠሩ" ሲሉ ተደምጠዋል።

በመጪው ኅዳር የሚደረገው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ አሜሪካውያን ስለ ትራምፕ ያላቸውን ትክክለኛ አቋም ያሳይ ይሆናል።

በሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ምክንያት የተፈጠረው ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ጫና ከአሁኑ አሜሪካውያንን ለከፍተኛ የናፍጣ እና የቤንዚን ዋጋ ጭማሪ እንዲጋለጡ አድርጓል።

ይህ የነዳጅ ጭማሪ በሸቀጦች ዋጋ ላይ እጁን ሲያሳርፍ ቀድሞውንም ቢሆን በቀጣዩ ዓመት በሚደረገው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ለትራምፕ ፓርቲ ስጋት እንደሚሆን የተገመተው የኑሮ ውድነት እንዲንር ያደርጋል።

ጦርነቱ የሪፐብሊካኖችን የተወካዮች ምክር ቤት እና ምናልባትም በሴኔት ውስጥ ያላቸውን የበላይነት ሊያሳጣ ይችላል። ለሪፐብሊካን ፓርቲ ይህ ሁኔታ እጅግ ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ነው።

ጦርነቱ እየቀጠለ ሲሄድ ትራምፕ እየጨመረ ለመጣው የኢኮኖሚ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ተገድደዋል። ጦርነቱን ሲከፍቱ የወጠኑት ዓላማ ቀርቶ ግባቸው የሆርሙዝ ወሽመጥን ማስከፈት ሆኗል።

ፈተና ውስጥ የገቡት የአሜሪካን አጋሮች

ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ተቆጣጠረችበት ወቅት ትራምፕ የሚሰጡትን ምላሽ በተመለከተ ሀሳባቸውን በተደጋጋሚ ቀያይረዋል።

አጋር አገራት ወሽመጡን ለማስከፈት እንዲያግዙ ሲጠይቁ ከቆዩ በኋላ አሜሪካ እርዳታ እንደማትፈልግ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ቆይተው ደግሞ በጦርነቱ የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላቸው የገለጹትን የረጅም ጊዜ አጋሮቻቸውን "ፈሪዎች" ሲሉ ዘልፈዋል።

ትራምፕ ግሪንላንድን ለመቆጣጠር በሳዩት ፍላጎት የተነሳ ቀድሞውኑ እየተሰነጠቀ የነበረው የኔቶ አንድነት በኢራን ጦርነት ምክንያት ተባብሷል።

ፕሬዝዳንቱ ጦርነቱ ውስጥ ከመሳተፍ በታቀበው የኔቶ ጥምረት ላይ የሚሰነዝሩትን ጥቃት እንደ አዲስ ጀምረዋል። የኔቶ ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩተ በዋይት ሐውስ ከትራምፕ ጋር ያደረጉት ንግግር "እጅግ ግልጽ" እንደነበር ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንቱ አሜሪካ ያላት እጅግ ግዙፍ ወታደራዊ የበላይነት፤ የአገሪቱን ልዕለ ኃያልነት ለረጅም ጊዜ አሰጠብቆ ይቀጥላል የሚል ዕምነት ሊኖራቸው ይችላል።

የአውሮፓ አገራት ግን ገና ከአሁኑ ራሳቸውን ከማይገመት እና የማይታመን ጠባቂ ለማራቅ አማራጮችን መመልከት ጀምረዋል።

ይህ ሁኔታ ቻይና ኢኮኖሚያዊ እና ስትራቴጂካዊ ጥቅም እንድታገኝ ሊያደርግ ይችላል። ትራምፕ በዋሽንግተን ቅሬታ እንዲነሳባቸው ያደረገው አንዱ ምክንያትም ይኸው ጉዳይ ነው።

የዚህ ጦርነት ትክክለኛ ዋጋ ገና አልተቆጠረም። መተግበር የጀመረው የተኩስ አቁም ወይም ሊካሄድ የታቀደው ድርድር የሚከሽፉ ከሆነ አሜሪካ የምትከፍለው ዋጋ ከዚህም ሊያሻቅብ ይችላል።