ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የአልጀርሱን ስምምነት እንዲያከብሩ ጥሪ እየተደረገ ያለው ለምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ በመጣበት ወቅት የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የአልጀርስ ስምምነት የተፈረመበትን 25ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ሁለቱ አገራት ሉዓላዊነታቸውን እና የግዛት አንድነታቸውን እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የአልጀርሱ ስምምነት የተፈረመበትን 25ኛ ዓመት አስመልክተው ባወጡት መግለጫ ላይ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለስምምነቱ ያላቸውን ተገዢነት እንዲያድሱ ጠይቀዋል።
የአውሮፓ ኅብረት እና አባል አገራቱ በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት ባወጡት መግለጫ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከ25 ዓመታት በፊት ለተፈራረሙት የአልጀርስ ስምምነት እና የዓለማቀፉ የድንበር ኮሚሽን በካርታ ላይ ለወሠነው የሁለቱ አገራት ድንበር ሙሉ ድጋፍ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ኅብረቱ የአልጀርስ ስምምነት የተፈረመበትን 25ኛ ዓመት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ሁለቱ አገራት "ሉዓላዊነትን፣ ነጻነትን" እና የግዛት አንድነትን" እንዲያከብሩ ጠይቋል።
ካናዳ፣ ጃፓን፣ ኖርዌይ፣ ቱርክ እና ዩናይትድ ኪንግደም በጋራ ባወጡት መግለጫ እንዲሁ ለአልጀርስ ስምምነት እና ለድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ያላቸውን "ዘላቂ ድጋፍ" አረጋግጠዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቃል አቀባያቸው በኩል አርብ ዕለት ባወጡት መግለጫ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለአልጀርስ ስምምነት ያላቸውን ተገዢነት ዳግም እንዲያረጋግጡ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ "ለዘላቂ ሰላም" እና አንዳቸው የሌላውን "ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት" ለማክበር ለተፈራረሙት የአልጀርስ ስምምነት እንደገና ቁርጠኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ጥሪ አቅርበዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረት በነገሰበት በዚህ ወቅት ጉቴሬዝ "መልካም ጉርብትና ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ማጠናከር" እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
የአልጀርሱን ስምምነት ጉቴሬዝ "ወሳኝ ማዕቀፍ" በማለት ሲጠሩት፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሐሙድ አሊ ዩሱፍ በበኩላቸው "ታሪካዊ" ብለውታል።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በድንበር ይገባኛል ምክንያት ሚያዝ 28/1990 ዓ.ም. ወደ ጦርነት ከገቡ በኋላ በአልጀርስ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ጦርነቱ እንዲያበቃ አድርጓል።
ይህ የከፋ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመትን ያስከተለው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የድንበር ጦርነት እንዲያበቃ ያደረገው ስምምነት የተፈረመው ታኅሣሥ 3/1993 ዓ.ም. በአልጄሪያ ዋና ከተማ አልጀርስ ነው።
ሁለቱን አገራት ወደ እርቅ እና መግባባት ያመጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ይህ ስምምነት የተፈረመው በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና በኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ነበር።
ጦርነቱ በተካሄደባቸው ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሁለቱም ወገን ለሞት እና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል።
ከዚያ ቀጥሎ ባሉት አስርት ዓመታት ምንም ዓይነት የተኩስ ድምጽ ባይሰማም የሁለቱ አገራት ጦር በድንበር አካባቢ ተፋጥጦ ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የሁለቱ አገራት ግንኙነት መሻሻል አሳይቶ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሁለቱ አገራት መካከል ሰላም እንዲወርድ ላደረጉት አስተዋጽኦም የኖቤል የሰላም ሽልማትን አሸንፈዋል።
ሁለቱ አገራት ለሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት በጋራ ጦራቸውን አሰልፈው ከተዋጉ በኋላ የፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረምን ተከትሎ ግንኙነታቸው ዳግም ሻክሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የባሕር በር ለኢትዮጵያ "የኅልውና ጉዳይ ነው" ማለታቸውን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል የቃላት ጦርነት የተጀመረ ሲሆን፣ በየጊዜው በሚያወጧቸው መግለጫዎችም መለሳለስ አይታይባቸውም።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር በመግለጫቸው ላይ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለስምምነቱ ያላቸውን ተገዢነት "እንዲያድሱ" ጥሪ አቅርበዋል።
ለዘላቂ ሰላም እና ለመልካም ጉርብትና ሁለቱም አገራት ውይይትን እንዲያስቀድሙም ሊቀመንበሩ በመግለጫቸው ላይ ጠይቀዋል።
የአውሮፓ ኅብረት በበኩሉ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ማናቸውንም "ውጥረቶች ወይም ውዝግቦች በሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ" መንገዶች እንዲፈቱ ጥሪ አድርጓል።
ኅብረቱ ይህም ለቀጠናው መረጋጋት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር በበኩላቸው የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባሕር መረጋጋት እንዲሁም የሕዝቦቹ ደኅንነት የሚመሠረተው መተማማን በመገንባት፣ ትብብርን በማጠናከር እንዲሁም የቀጠናውን እና የጋራ ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ግጭቶችን በመከላከል ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኢትዮጵያንም ሆነ ኤርትራን እንዲሁም ሰፊውን ቀጠና ወደ ሰላም፣ ልማት እና ድንበር ተሻጋሪ ትብብር እንዲመጣ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ሊቀመንበሩ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
"የአፍሪካ ኅብረት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጋር ወደፊት በሰላም፣ በአጋርነት እና በጋራ ዕጣ ፈንታ ላይ ለሚሠሩት ሥራዎች ከጎናቸው ነው" ሲል መግለጫው ገልጿል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የባሕር በር ማግኘትን አስመልክቶ በሚሰጡት አስተያየት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን አለመግባባት ይፋ እያወጣው ነው።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግሥታት እና ዓለማቀፍ አጋሮቹ ያወጧቸው እነዚህ መግለጫዎች ለ25 ዓመታት ያህል በሁለቱ አገራት መካከል ጦርነትን ያስቆመውን የአልጀርስ ስምምነት ተጥሶ ዳግም ጦርነት ያገረሻል የሚል ስጋት ያደረባቸው ይመስላል።















