ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ያስመረቀችው ግዙፍ የመዝናኛ ስፍራ ለውጭ ቱሪስቶች እንደማይፈቀድ አሳወቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰሜን ኮሪያ ከሁለት ሳምንት በፊት በይፋ ያስመረቀችው ግዙፉ ዘመናዊ የባሕር ዳርቻ የመዝናኛ ስፍራ ለውጭ ዜጎች እንደማይፈቀድ አስታወቀች።
የአገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ቱሪስቶችን ለመሳብ አላቸው በተባለው ፍላጎት መሠረት የተገነባው ዎንሳን ካልማ የተባለው የባሕር ዳርቻ የቱሪስቶች የመዝናኛ ስፍራ ሲከፈት ሰሜን ኮሪያ በሯን ለመክፈት ያላት ፍላጎትን ማሳያ ተደርጎ ተወስዶ ነበር።
የመዝናኛው ስፍራ ከመከፈቱ በፊት ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ቱሪስቶች መስህብ እንደሆነ ሲተዋወቅ ቆይቷል። ነገር ግን በዚህ ሳምንት የአገሪቱ ቱሪዝም መሥሪያ ቤት ድረ ገጽ የውጭ ዜጎች ወደ መዝናኛ ስፍራው መሄድ "ለጊዜው" እንደማይፈቀድላቸው አስታውቋል።
ባለፈው ሳምንት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በመዝናኛዋ ከተማ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር በተገናኙበት ጊዜ የመጀመሪያዎቹ የሩሲያ ቱሪስቶች ለጉብኘት ወደ ስፍራው ደርሰው ነበር።
የፈረንሳይ ዜና ወኪል እንደዘገበው ላቭሮቭ በባሕር ዳርቻው ላይ የተገነባውን የመዝናኛ ስፍራ "ጥሩ የቱሪስቶች መስህብ ነው" በማለት በሩሲያውን ተወዳጅ እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸው ነበር።
አንድ ሩሲያዊ አስጎብኚም ለሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን በሚቀጥሉት ወራት በርካታ ቱሪስቶችን ወደ መዝናኛው ለማምጣት ዕቅድ እንዳለ አመልክቶ ነበር።
የመዝናኛ ቦታው የሚገኝባት ዎንሳን በሰሜን ኮሪያ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ የምትገኝ ሲሆን፣ የአገሪቱ የሚሳዔል ማዕከላት እና የባሕር ትራንስፖርት ተቋም ያለባት ናት። በተጨማሪም የአገሪቱ መሪ ኪም የወጣትነት ጊዜያቸውን ያሳለፉባት እንዲሁም የአገሪቱ ባለሥልጣናት የእረፍት ጊዜ መኖሪያ ቤቶች ይገኙባታል።
አዲሱ የባሕር ዳርቻ የመዝናኛ ስፍራ 4 ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍን ሲሆን፤ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች፣ የገበያ ማዕከላት እና የውሃ ላይ መዝናኛ ቦታዎች አሉት።
የሰሜን ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት 20 ሺህ ሰዎችን የማስተናገድ አቅምም አለው።
በአውሮፓውያኑ 2018 ግንባታው የተጀመረው ይህ የመዝናኛ ስፍራ በሂደቱ የግንባታ ሠራተኞች አያያዝን አሳሳቢ መሆኑን የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ሲተቹ ነበር። በዚህም ግዙፉን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ሠራተኞች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለረጅም ሰዓታት በዝቅተኛ ክፍያ እንዲሠሩ ተደርገዋል ብለዋል።
የመዝናኛ ስፍራው ግንባታ ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ሲጠናቀቅ የሩሲያ አምባሳደሮች ከአገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና ከቤተሰባቸው ጋር በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ነበር።
ሰሜን ኮሪያ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በሯን ለቱሪስቶች ዝግ አድርጋ ለዓመታት ከቆየች በኋላ ባለፈው ዓመት ሩሲያውያን ቱሪስቶች ለጉብኝት እንዲገቡ እንደፈቀደች ይታወሳል።
በየካቲት ወር ደግሞ አገሪቱ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ከሌሎች የምዕራብ አገራት የመጡ ቱሪስቶችን መቀበል ጀምራ ነበር። ነገር ግን ከሳምንታት በኋላ ምክንያቷን ሳትገልጽ በድንገት ቱሪስቶች እንዳይገቡ አግዳለች።















