ኤርትራዊው ስደተኛ ከዩኬ እንዳይባረር ያቀረበው አቤቱታ በፍርድ ቤት ተቀባይነት አገኘ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ከሁለት ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ የተጓዘው ኤርትራዊ ዩናይትድ ኪንግደም በሕገ ወጥ መንገድ መግባቱን ተከትሎ ከአገር እንዲባረር የተወሰነውን ውሳኔ በመቃወም ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት አገኘ።
በአነስተኛ ጀልባ እንግሊዝ የገባው ኤርትራዊው ዩናይትድ ኪንግደም ከፈረንሳይ ጋር ባደረገችው "አንድ ማስገባት፤ አንድ ማስውጣት" ስምምነት ከአገር የመውጣት ሂደቱ በጊዜያዊነት ታግዷል።
ፈረንሳይ እና ዩኬ በፈረሙት በዚህ ስምምነት መሠረት በጀልባ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ አንዳንድ ስደተኞች ወደ ፈረንሳይ ሲመለሱ፤ ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ ተመጣጣኝ ቁጥር ያላቸውን ጥገኛ ጠያቂዎች የደኅንነት ፍተሻ አድርጋ ትቀበላለች።
የ25 ዓመቱ ወጣት ባለፈው ሐምሌ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ በደረሱት በዚህ ስምምነት መሠረት ረቡዕ ወደ ፈረንሳይ ለመመለስ ቀጠሮ ተይዞለት ነበር።
በለንደን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበው የኤርትራዊው መዝገብ የዚህ ስምምነት የመጀመሪያው ሕጋዊ አቤቱታ ሲሆን፤ ጠበቃው የዘመናዊ ባርነት ተጎጂ ሊሆን እንደሚችል እና ለዚህም ማስረጃ ለማቅረብ ጊዜ ያስፈልገዋል ሲል ተከራክሯል።
እግዱ የአየር በረራ የተቆረጠላቸው ሌሎች ስደተኞችም ተመሳሳይ መከራከሪያ በማቅረብ ከአገር እንዳይወጡ ለማድረግ አሊያም ለማዝግየት ሊጠቀሙበት ይችላል የሚል ጥያቄን አስነስቷል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጠበቆች ኤርትራዊው ስደተኛ ፈረንሳይ ጥገኝነት መጠየቅ ይችላል ሲሉ ተከራክረዋል።
ስደተኛው ከአገር እንዳይወጣ የተጣለው ጊዜያዊ እግድ የመመለሻ በረራ የተዘጋጀላቸው ሌሎች ስደተኞች ተመሳሳይ አቤቱታ እንዲያቀርቡ እንደሚያበረታታ እና እየጨመረ የመጣውን የአነስተኛ ጀልባዎች ፍልሰት ለመከላከል በሕዝቡ ዘንድ አመኔታ ይሸረሽራል ሲሉ አክለው ተሟግተዋል።
በፍርድ ቤቱ ችሎት የአገር ውስጥ ጉዳይ ባለሥልጣናት ኤርትራዊው የባርነት ሰለባ ስለመሆኑ አቤቱታውን ውድቅ አድርገዋል።
ዳኛ ጀስቲስ ሸልደን ስደተኛው በፈረንሳይ ቤት አልባ እንደሚሆን እና ችግር ላይ እንደሚወድቅ ጠቅሶ ያቀረበውን አቤቱታ ውድቅ ቢያደርጉም፤ የሕገ ወጥ ዝውውር አቤቱታውን ተከትሎ ከአገር እንዲወጣ የሚያስገድደውን ውሳኔ በጊዜያዊነት እንደሚያግዱ ገልፀዋል።
"ከሰዎች ዝውውር አቤቱታ ጋር በተገናኘ መታየት ያለበት አሳሳቢ ጉዳይ አለ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በሕጋዊ አካሄድ ምርመራ አድርገዋል ወይስ አላደረጉም የሚለው መታየት አለበት" ብለዋል።
"ስደተኛው ከፈረንሳይ ሳይሆን በሰው አዘዋዋሪዎች እጅ ወድቆ ስለመሆኑ አሳማኝ ጥርጣሬ ከነበረ፤ ቢያንስ ለአጭር ጊዜ ከአገር እንዳይባረር እግድ መጣል ይቻላል" ሲሉም አክለዋል።
ዳኛው የኤርትራዊው የፍርድ ቤት መዝገቡ እንዲዘጋ ጠበቃው በ14 ቀናት ውስጥ ማስረጃ እንዲያቀርብ አዝዘዋል።
የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለቢቢሲ መንግሥት በስምምነቱ መሠረት የመጀመሪያዎቹ ተመላሾች በአስቸኳይ እንዲመለሱ እንደሚፈልግ እና ጊዜያዊ እግዱ ፖሊሲውን በሰፊው ለማስፈፀም እንደማይከለክል ተናግረዋል።
የተቃዋሚው ወግ አጥባቂዎች ፓርቲ መሪ የሆኑት ኪሚ ዳዲኖች "ነግረናችሁ ነበር" ሲሉ የእግዱን ዜና በተመለከተ አስተያየት ሰጥተዋል።
"አገራችንን በመሠረታዊነት በአገራቸው በመጠኑም ቢሆን እንኳ ደስተኞች ያልሆኑ የማንኛውም ስደተኞች አገር እያደረግናት ነው" ሲሉ ተችተዋል።
የሪፎርም ፓርቲ መሪ ናይጅል ፋራጅ ፖሊሲው ቢሰራ እንኳ የስደተኞችን ቁጥር በ"አንድ ማስገባት፤ አንድ ማስወጣት" ስርዓት በእንግሊዝ ቻናል የሚደረግን ፍልሰት መቀነስ አይቻልም ብለዋል።
በለንደን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀረቡ ሰነዶች የስደተኛው ስም ለሕጋዊ አካሄድ ሲባል ያልተጠቀሰ ሲሆን፤ ኤርትራዊው ከሁለት ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ በመጓዝ እ.አ.አ ሚያዚያ 2025 ጣሊያን ደርሷል።
ከወር በኋላ በቀይ መስቀል እና በሌሎች እገዛ ሲኖርበት ከነበረው ፈረንሳይ እናቱ ለአዘዋዋሪዎች በከለችለት 1,400 ዶላር የእንግሊዝ ቻናልን ተሻግሮ ዩናይትድ ኪንግደም ገብቷል።
በ2025 ዓመት ብቻ በአነስተኛ ጀልባዎች ከ30 ሺህ የሚበልጡ ስደተኞች የእንግሊዝ ቻናልን ተሻግረው ዩኬ ገብተዋል።
"የአንድ ማስገባት፤ አንድ ማስውጣት" ስምምነት ባለፈው ሐምሌ በጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር እና በፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ይፋ ተደርጓል።
በዚህ ስምምነት በአነስተኛ ጀልባዎች ተጉዘው ዩኬ የሚገቡ ስደተኞችን ፈረንሳይ መልሳ ለመውሰድ እና የጥገኝነት ጥያቄያቸውን ውድቅ ለማድረግ ተስማምተዋል።















