ቢዮንሴ ለሙዚቃዎቿ ‘ቪድዮ’ መሥራት ያቆመችው ለምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, Bryce Anderson/GQ/PA Wire
ክሬዚ ኢን ላቭ በተሰኘው የሙዚቃ ክሊፕ ማስቲካ ስታፈነዳ፤ ሆልድ አፕ በተሰኘው ሥራዋ ደግሞ መኪና በዱላ ስትሰባብር ትታያለች።
እኒህ ትዕይንቶች በፖፕ የሙዚቃ ክሊፕ አድናቂዎች ዘንድ ሁሌም ሲዘከሩ ይኖራሉ።
ቢዮንሴ በሙዚቃ ቪድዮ ማይክል ጃክሰን እና ማዶና በ1980ዎቹ ያገኙት ትልቅ ስም ተጎናፅፋለች የሚሉ ብዙዎች ናቸው።
አሜሪካዊቷ ሙዚቀኛ ሌመኔድ በተሰኘው ሥራዋ ጥቁር ሴቶችን ያወደሰችበት እና የሴቶችን ኃይል የገለፀችበት መንገድ አድናቆት ተችሮታል።
ነገር ግን ድንገት ነው ቢዮንሴ ለሙዚቃዎቿ ‘ቪድዮ’ መሥራት ያቆመችው።
ሬኔሳንስ እና ካውቦይ ካርተር የተሰኙት ያለፉት ሁለት አልበሞቿ የቪድዮ ድርቅ ያጠቃቸው ናቸው።
ቢዮንሴ ጂኪው ከተሰኘው ጋዜጣ ጋር ባደረገችው ቃለ-ምልልስ ለምን ቪድዮ መሥራት እንዳቆመች ተናግራለች። “ቪድዮዎቼ የድምፅ እና የሙዚቃውን ጥራት እንዲሸፍኑብኝ አልፈልግም” ብላለች።
“ሁሉም ነገር እንድናየው ተደርጎ በሚቀርብበት በዚህ ሰዓት ሰዎች ድምፁ ላይ እንዲያተኩሩ እሻለሁ” ትላለች ኮከቧ።
በቅርቡ ያሳተመቻቸው አልበሞች ጥቁር ድምፃዊያን ብዙም የማይሳተፉባቸው እንደ ሀውስ፣ ዲስኮ እና ካንትሪ [ሀገረሰብ] የሙዚቃ ዘውግ ላይ ያተኮሩ ናቸው። እኒህ ሥራዎች ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ ነው የምፈልገው ስትል ታስረዳለች።
“ሙዚቃው በታሪክ እና በሙዚቃ መሣሪያ የተሞላ ነው። ይህን ለማጣጣም፣ ለማጥናት እና ለመረዳት ወራት ሊወስድ ይችላል።”
ቢዮንሴ ሬነሳንስ የተሰኘ አልበሟን ከለቀቀች በኋላ በበርካታ ሀገራት እየተዘዋወረች የሙዚቃ ኮንሰርት አሳይታለች። እኒህ ኮንሰርቶች በሺዎች የሚቆጠሩ አድናቂዎቿ የታደሙባቸው ነበሩ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብዙውን ጊዜ ዘለግ ያሉ ቃለ-ምልልሶች በመስጠት የማትታወቀው ቢዮንሴ ለመጨረሻ ጊዜ ረዘም ያለ ጊዜ ወስዳ ስለሥራዎቿ ያወራችው በአውሮፓውያኑ 2017 ከእህቷ ሶላንጅ ጋር ሆና ባደረገችው ቃለ-ምልልስ ላይ ነበር።
ቢዮንሴ አዲሱን የዊስኪ ‘ብራንዷን’ ለማስተዋወቅ በሚል ነው ከጂኪው ጋር ቆይታ ያደረገችው።
የሙዚቃ ኮከቧ ከአውሮፓውያኑ 2013-14 ጀምሮ ነው ቃለ-መጠይቅ ከመስጠት ይልቅ ረዘም ያሉ ፅሑፎችን ለመፅሔቶች መላክ አሊያም ማኅበራዊ ሚድያ ላይ መፃፍ የጀመረችው።
አሁን ጂኪው ከተሰኘው መፅሔት ጋር ያደረገችው ቃለ-ምልልስ ስለግል ሕይወቷ ብዙም አያነሳም።
ነገር ግን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ‘ተርኪ’ ከተባለው እንስሳ በቀር ስጋ መብላት ማቆሟን የተናገረች ሲሆን ሰው ሰራሽ አስተውሎት [ኤአይ] እየፈጠረ ስላለው ስጋትም ስሜቷን አጋርታለች።
በቅርቡ በኤአይ የተሠራ ሙዚቃ አድምጣ “በጣም የኔን ድምፅ ይመስላል እና በጣም ፈራሁኝ” ስትል የተሰማትን አጋርታለች።
የግል ሕይወቷን ከተቀረው ዓለም በመሸሸግ የተካነችው ቢዮንሴ ስለቤተሰብ ሕይወቷ መገናኛ ብዙኃን ብዙ መረጃ እንዲኖራቸው እንደማትፈልግ ገልፃለች።
የመጨረሻ አልበሟን በሀገረሰብ የሙዚቃ ዘውግ የሠራችው ቢዮንሴ ‘ካንትሪ ሚዪዚክ አዋርድ’ ለተሰኘው ሽልማት ሳትታጭ ቀርታለች።
ነገር ግን በዚህ አልበሟ በአሜሪካ የሀገረሰብ ሙዚቃ ሰንጠረዥ ቁጥር አንድ በመሆን የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት መሆን ችላ ነበር። አልፎም ቴክሳስ ሆልደ’ም የተሰኘው ሙዚቃ ለሁለት ሳምንታት የደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ ቆይቷል።
ሲንግል ሌዲስ፣ ፎርሜሽን፣ ካውንትዳውን፣ ክሬዚ ኢን ላቭ እና ጌት ሚ ቦዲድ ቢዮንስ እውቅና ካተረፈችባቸው የሙዚቃ ቪድዮዎች መካከል ይጠቀሳሉ።












