የአውሮፓ ኅብረት የሶማሊያን የግዛት አንድነት ማክበር ያስፈልጋል አለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር ጠረፍ ያስገኛል የተባለ የመግባቢያ ሠነድ መፈራረማቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት የሶማሊያን ሉዓላዊነት ማክብር አስፈላጊ ነው አለ።
የአውሮፓ ኅብረት የስምምነቱን መፈረም አስመልክቶ ባወጣው አጭር መግለጫ የፌደራል ሪፐብሊክ ኦፍ ሶማሊያ ሕገ-መንግሥት እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተሮች መሠረት የአገሪቱን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር ጠቃሚ መሆኑን ለማስታወስ እንወዳለን ብሏል።
በአውሮፓ ኅብረት ቃል አቀባይ በኩል ትናንት የወጣው መግለጫ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋገትን ለማስፈን የሶማሊያ ሉዓላዊነትን ማክበር ቁልፍ ነው ብሏል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሠነድ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. መፈራረሟ ይታወሳል።
ይህ ስምምንት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ለወደብ እና ለጦር ሰፈር ልማት የሚውል 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ እንድታገኝ የሚያስችላት ሲሆን በምላሹ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንዲሁም እንደ አገር ከአዲስ አበባ እውቅና እንደምታገኝ ተዘግቧል።
እአአ 1991 ራሷን ከሶማሊያ ገንጥላ ነጻነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ እስካሁን ደረስ ከየትኛው ሀገር እንዲሁም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋም እንደ ሀገር የሚያስቆጥራትን እውቅና አላገኘችም።
ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ኢትዮጵያ “ለሪፐብሊክ ኦፍ ሶማሊላንድ በይፋ ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ አገር ትሆናለች” ብለዋል።
የፊርማ ስነ-ስርዓቱ በተከናወነ ወቅት ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ለሶማሊላንድ ዕውቅና እንደምትሰጥ በኢትዮጵያ በኩል የተባለ ነገር ባይኖርም ትናንት ማክሰኞ ታኅሣሥ 23/2016 ዓ.ም. ራስ ገዟ ሶማሊላንድ እንደ ሀገር የሚያስቆጥራትን “ዓለማ አቀፋዊ ዕውቅና” ከኢትዮጵያ ለማግኘት ከስምምነት ላይ መድረሷን በመግለጽ ያወጣችውን መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚቀበለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ይህን የጋራ የመግባቢያ ሠነድ ታሪካዊ ሲሉ ቢገልጹትም በሶማሊያ በኩል ጠንካራ ትችት ተሰንዝሮበታል።
የሶማሊያ መንግሥት ሶማሊላንድ የፌደራል መንግሥቱ አንድ አካል መሆኗን ገልጾ፤ ስምምነቱንም “በሶማሊያ ነጻነት፣ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የሶማሊያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው” ብሎታል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ሠነዱን መፈራረማቸውን ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ካቢኔ አስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጦ ባወጣው መግለጫ የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እና የአፍሪካ ኅብረት በጉዳዩ ላይ በአስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ከዚህ በተጨማሪም የሶማሊያ መንግሥት ተመድ፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የእስላማዊ ትብብር ድርጅት፣ የአረብ ሊግ፣ የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና ሌሎች ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋ ድርጅቶች ከሶማሊያ ጎን እንዲቆሙ እና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕጎች ተገድባ እንድትቆይ ጫና እንዲያሳድሩ ጥሪ አቅርቧል።












