እንቁራሪት እና እባብ ዓለምን 16 ቢሊዮን ዶላር አሳጥተዋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከቁጥጥር ውጪ በብዛት እየተራቡ ነው የተባሉት የእባብ እና የእንቁራሪት ዝርያዎች ዓለምን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረጉ ነው ተባለ።
በዓለም ዙሪያ በወራሪ ተባዮች/እንስሳት የሚደርሰውን ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራን የሚገመግሙ ሳይንቲስቶች ባወጡት ሪፖርት በሁለት ዝርያዎች አማካይነት ከፍተኛ ውድመት መድሰሩን ገልጸዋል።
እንደ ተመራማሪዎቹ ከሆነ በአሜሪካ የሚገኘው 'ቡልፍሮግ' የተሰኘው አንቁራሪት ዝርያ እና ቡናማ ቀለም ያለው የዛፍ ላይ እባብ ከ1986 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ 16.3 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ አድርሰዋል።
ከሥነ ምኅዳር ጉዳት በተጨማሪ ሁለቱም የእርሻ ሰብሎችን ከማበላሸት ባለፈ፣ ከፍተኛ ኪሳራ ያስከተለ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ አድርሰዋል።
የተመራማሪዎቹ የጥናት ውጤት ወደፊት ወራሪ ዝርያዎቹን ለመግታት ለሚደረግ ጥረት ግብዓት ይሆናል ተብሏል።
ሳይንቲስቶቹ ቡናማ ቀለም ያለው እባብ ለብቻው 10.3 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ውድመት በማድረስ ዋነኛው ተጠያቂ ያደርጉታል። በተለይም በበርካታ የፓስፊክ ደሴቶች ላይ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መንገድ በመስፋፋት ነው ጉዳቱን ያደረሱት ብለዋል።
ይህ የእባብ ዝርያ በኤሌክትሪክ ሽቦዎች ላይ ተስቦ በመውጣት ከፍተኛ ኪሳራ ያደረሰ የኃይል መቋረጥ አድርሷል።
ከሁለት ሚሊዮን በላይ ቡናማ ቀለም ያላቸው እባቦች ጉዋም የምትሰኘውን የአሜሪካ ግዛት የሆነች ደሴትን ወረዋታል።
የደሴቲቱ ሥነ ምኅዳር ለወራሪ ዝርያዎች የበለጠ ተጋላጭ ነው ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን፣ ይህም በአካባቢዎቹ ብርቅዬ እንስሳት እና እጽዋትት ላይ የበለጠ የመጥፋት ስጋትን ይደቅናል።
በአውሮፓ የአሜሪካ ዝርያ ያላቸውን እንቁራሪቶች ለመቆጣጠር ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ የመቆጣጠሪያ ፕሮግራሞች ማስፈለጉ ተነግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስከ 30 ሴ.ሜ ርዝመት እና ግማሽ ኪሎ ግራም ክብደት ያለው እንቁራሪት እንዳይስፋፋ ለመከላከል ባለሥልጣናት በመራቢያ ቦታዎች ላይ ውድ የሆነ የእንቁራሪት መከላከያ አጥር ለመትከል ተገድደዋል።
አንቁራሪቶቹ ሌሎች የእንቁራሪት ዝርያዎችን ጨምሮ ማንኛውንም ነገር እንደሚበሉም ተነግሯል።
ሌላ የእንቁራሪት ዝርያ ደግሞ በተለየ መንገድ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ማድረሱ ታውቋል። በስፋት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ድምጽ የሚያወጡት እንቁራሪቶች መኖሪያ የቤቶችን ዋጋ እንዲቀንስ አድርጓል ተብሎ ይታመናል።
አጥኚዎቹ ግኝታቸው በተባይ መቆጣጠሪያ እና ሌሎች የተፈጥሮ ጥበቃ እርምጃዎች ላይ ባለሥልጣናት ይበለጥ ገንዘብ እንዲያፈሱ የሚያበረታታ እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋሉ።












