በረራ ላይ ሳሉ የተኙ ሁለት የኢንዶኔዢያ አየር መንገድ አብራሪዎች ምርመራ ተከፈተባቸው

በኢንዶኔዢያ በረራ ላይ ሳሉ ለ28 ደቂቃዎች ተኝተው በነበሩ ዋና አብራሪ እና ምክትል አብራሪ ላይ ምርመራ መከፈቱ ተገለጸ።

የአገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስቴር የባቲክ አየር መንገድ አብራሪዎች ከሥራ ታግደው ምርመራው እየተካሄደባቸው እንደሆነ አስታውቋል።

ሁለቱ አብራሪዎች በረራ ላይ ሳሉ እንቅልፍ የጣላቸው ከ7 ሳምንታት በፊት በነበረ ወደ መዲናዋ ጃካርታ ሲደረግ በነበረ የአገር ውስጥ በረራ ላይ ነበር።

አብራሪዎቹ ምንም እንኳ ለበርካታ ደቂቃዎች ተኝተው የነበረ ቢሆንም 153 መንገደኞችን እና የበረራ ሠራተኞችን ጭኖ የነበረው ኤየርባስ ኤ320 አውሮፕላን በመዳረሻው በሰላም አርፏል።

የአገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ባወጣው ሪፖርት ዋና አብራሪው እረፍት ማድረግ ስለሚፈልግ ምክትል አብራሪው በረራውን እንዲቆጣጠር ኃላፊነት ሰጥቶታል። የ28 ዓመቱ ምክትል አብራሪም ትዕዛዙን ተቀብሏል።

ይሁን እንጂ ምክትል አብራሪውም ሳያውቀው እንቅልፍ ወስዶት ነበር። ይህን ተከትሎ በጃካርታ የሚገኙ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ሁለቱን አብራሪዎች በራዲዮ አማካኝ ለማነጋገር ያደረጉት ጥረት ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል።

አሁን ላይ እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች እንደሚሉት ከሆነ ሳያውቀው እንቅልፍ የጣለው ምክትል አብራሪ በቅርቡ መንታ ልጅ የተገላገለች ባለቤቱን በልጅ እንክብካቤ ሲረዳ ቆይቷል።

አብራሪዎቹ ከእንቅልፍ እስኪነቁ ድረስ የሬዲዮ ግንኙነቱ ለ28 ደቂቃዎች ተቋርጦ ነበር። የትራንስፖርት ሚኒስቴር ባወጣው ሪፖርት ላይ ዋና አብራሪው ከእንቅልፉ ሲነቃ ምክትል አብራሪው እንደተኛ እና አውሮፕለኑ ከበረራ አቅጣጫው ለአጭር ጊዜም ቢሆን ወጥቶ እንደነበረ ተገንዝቧል ይላል።

ከክስተቱ በኋላ ሁለቱ አብራሪዎች ለአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ክፍል ምላሽ በመስጠት አውሮፕላኑን በጃካርታ አሳርፈዋል።

ከበረራ በፊት ለአብራሪዎቹ የተደረገ የጤና ምርመራ ለበረራ ብቁ መሆናቸውን አሳይቶ ነበር። ደም ግፊታቸው እና የልብ ምታቸው ችግር ያልታየበት ሲሆን አልኮል በሰውነታቸው እንደሌለም በምርመራ ተረጋግጧል።

ይሁን እንጂ የኢንዶኔዢያ የአየር ትራንስፖርት ኃላፊ ክሪስቲ ኤንዳህ ሙራኒ አየር መንገዱ ሠራተኞቹ በቂ እረፍት እያገኙ ስለመሆኑ የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት በማለት ለባቲክ አየር መንገድ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል።

አየር መንገዱ በበኩሉ ሠራተኞች በቂ እረፍት ማግኘት አለባቸው በሚል ፖሊሲ እንደሚመራ ገልጾ ወደፊት ተመሳሳይ ክስተቶች እንዳያጋጥሙ ምክረ ሃሳቦችን እንደሚቀበል አስታወቋል።