የአይ ኤስ መሪ አልቁረይሺ መገደሉን የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ተናገሩ

የቱርክ ልዩ ኃይል በሰሜን ሶሪያ በኦፕሬሽን ላይ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የቱርክ ልዩ ኃይል በሰሜን ሶሪያ በኦፕሬሽን ላይ

በሶሪያ የኢስላሚክስ ስቴት (አይ ኤስ) መሪ አልቁረይሺ በቱርክ ኃይሎች መገደሉን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶዋን ተናገሩ።

አቡ ሑሴይን አልቁረይሺ በሚል ሙሉ ስሙ የሚታወቀው የአይ ኤስ መሪ መገደሉን ኤርዶዋን ይፋ ያደረጉት ለቲአርቲ ሚዲያ ነው።

ይህን እርምጃ የወሰዱት ደግሞ የቱርክ የስለላ እና ደኅንነት አባላት መሆናቸውን ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ገልጸዋል።

ኢስላሚክ ስቴት (አይ ኤስ) እስከ አሁን ዜናውን አላስተባበለም።

ቢቢሲ የኤርዶዋንን ቃል ከሌላ ገለልተኛ አካል አላጣራም።

የቱርክ የስለላ እና ደኅንነት መሥሪያ ቤት ቁራይሺን ረዘም ላለ ጊዜ ሲከታተለው እንደነበር ኤርዶዋን አብራርተዋል።

“ከአሸባሪዎች ጋር የምናደርገው ትግል አሁንም ይቀጥላል” ሲሉም ተናግረዋል።

ሮይተርስ ያነጋገራቸው በሶሪያ የሚገኙ ምንጮች በበኩላቸው ይህ ኦፕሬሽን የተደረገው ከቱርክ ድንበር አቅራቢያ ጃንዳሪስ በምትባል ትንሽ ከተማ ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፈው ኅዳር የጂሃዲስት ቡድኑ የዚያን ጊዜ መሪው አቡ አል ሐሳን አል ሒሺሚ መገደልን አረጋግጦ ነበር።

አሜሪካ አል ሐሳን አል ሐሺሚ ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ በሶሪያ ነጻ አውጪ ሠራዊት መገደሉን ይፋ ካደረገች በኋላ ነበር ቡድኑ ይህንኑ ያረጋገጠው።

ጆ ባይደን ይህን በማስመልከት በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት “የዓለም ትልቁ የሽብር ስጋት ተገድሏል” ብለው ነበር።

አሁን የተገደለው አልቁራይሺ የአል ሐሺሚን መገደል ተከትሎ የኢስላሚክ ስቴት መሪ ሆኖ የተሾመ ነው።

አይ ኤስ ከዓመታት በፊት 88 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሆን ሰፊ ግዛት ተቆጣጥሮ እስላማዊ መንግሥት (ካሊፌት) መስርቶ ማስተዳደር ጀምሮ ነበር።

ይህም ከሰሜን ምሥራቅ ሶሪያ እስከ ሰሜን ኢራቅ የሚዘረጋ እና ከ8 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሚኖርበት አካባቢ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2019 በተደረገ ኦፕሬሽን ቡድኑ ክፉኛ ተሸንፎ ተበታትኖ ቆይቷል።

አሁን በሶሪያ እና በኢራቅ እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ተዋጊዎች እንዳለው ይነገራል።

ለአይ ኤስ ድጋፋቸውን የሚሰጡ ቡድኖች ግን በአፍጋኒስታን፣ በሶማሊያ እና በቻድ አሁንም ድረስ አሉ።