ሞዛምቢክ በአደገኛ አውሎ ንፋስ ዳግም ልትመታ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዚህ ሳምንት መጨረሻ ሞዛምቢክ በአደገኛ አውሎ ንፋስ ዳግም ልትመታ እንደምትችል ተነገረ።
ፍሬዲ የሚል ስም የተሰጠው ይህ አውሎ ንፋስ ባለፈው ሰኞ ማዳጋስካርን የመታ ኃያል አውሎ ንፋስ ነው።
የማዳጋስካር መንግሥት እንዳለው በዚህ አውሎ ንፋስ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ አንድ ሺህ የሚጠጉት ቤት አልባ ሆነዋል።
ይህ አውሎ ንፋስ አደጋ ማድረስ የጀመረው በደቡብ ምሥራቅ አፍሪካ በየካቲት ወር አካባቢ ሲሆን በሁለቱ አገራት በድምሩ 21 ሰዎችን ገድሏል፤ ሺዎችን አፈናቅሏል።
የአየር ትንበያ አዋቂዎች እንደሚሉት አውሎ ንፋሱ እንዲህ ዓይነት የአቅጣጫ ለውጥ የማድረጉ ነገር እምብዛምም የተለመደ አይደለም።
ይህ የትሮፒካል አውሎ ንፋስ በታሪክ ረዥም ጊዜ የዘለቀ አውሎ ንፋስ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በየጊዜውም ግፊቱን እየጨመረ ነው የመጣው። አውሎ ንፋሱ ሕንድ ውቅያኖስ 8ሺህ ኪሎ ሜትር ተጉዟል።
ይህ ፍጥነቱ የብዙ የአየር ትንበያ ባለሙያዎችን ትኩረት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲስብ አድርጎታል።
ይህ አውሎ ንፋስ መነሻውን ያደረገው በሰሜን አውስትራሊያ ጠረፍ በየካቲት ወር ሲሆን ከዚያ በኋላ በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ በደቡባዊ የሕንድ ውቅያኖስ አድርጎ ሞሪሽየስ ላይ ጉዳት አድርሶ ከሁለት ሳምንት በፊት ማዳጋስካር ደርሷል።
ቀጥሎ ደግሞ በሞዛምፒክ ጉዳት ያደርሳል ተብሏል።
የአንድ አውሎ ንፋስ በተወሰነ ጊዜ ያለው ጉልበት ሲሰላ በሚያመጣው ጉልበት ሲለካ ይህን አውሎ ንፋስ ከባድ ክምችትና ጉልበት ያለው ሆኖ በክብረ ወሰን ተመዝግቧል።
ማዳጋስካር ባለፈው ሳምንት በወር ታገኝ የነበረውን አማካይ የዝናብ መጠን ሦስት እጥፍ አግኝታለች። ይህም ከአውሎ ንፋሱ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ያልተለመዱ የአየር ንብረት ለውጦችን የሚገመግመው ኮሚቴ አውሎ ንፋሱ ካለፈ በኋላ በጉዳዩ ላይ ጥናት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።












