ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኬንያ ፕሬዚዳንት በቤተ መንግሥታቸው ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ሊገነቡ ነው
የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ናይሮቢ በሚገኘው ቤተ መንግሥታቸው ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ሊገነቡ እንደሆነ አሳወቁ።
ሩቶ ለቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ ራሳቸው ወጪያቸውን እንደሚሸፍኑ ገልጸው የማንም ፈቃድ እንደማያስፈልጋቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
"ቤተክርስቲያን ለመገንባት የማንም ይሁንታ አያስፈልገኝም። ሰይጣንን ሊያበሳጨው ይችላል እናም የፈለገውን ማድረግ ይችላል" ሲሉ ሩቶ አርብ ዕለት ተናግረዋል።
የፕሬዚዳንቱ ንግግር በሳቸው አመራር የቤተ ክርስቲያንን እና የመንግሥት በጽኑ መጣመር ቀድሞውኑ የሚተቹት ኬንያውያንን አበሳጭቷል።
ቢቢሲ የኬንያ መንግሥትን አስተያየት እንዲሰጠው ጠይቋል።
ሩቶ ስቴት ሃውስ በተሰኘው ቤተ መንግሥታቸው በሰጡት አስተያየት "ሰይጣን" ብለው የጠሩት አካል ማን እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም የቤተ ክርስቲያኑን ፕሮጀክት ከመቀጠል የሚያግዳቸው ምንም ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።
"ይህንን ቤተ ክርስቲያን መገንባት የጀመርኩት ወደ ቤተ መንግሥት ስገባ አይደለም። እዚሁ በቆርቆሮ የተሰራ ቤተ ክርስቲያን አገኘሁ። ይህ ለቤተ መንግሥቱ የሚመጥን ይመስላችኋል?" ሲሉ አርብ ዕለት ከፖለቲከኞች ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
አርብ ዕለት ከኬንያ ታዋቂ ከሆኑት ጋዜጦች አንዱ የሆነው ዴይሊ ኔሽን 8 ሺህ ሰዎችን የሚይዝ ትልቅ ህንጻ የሚያሳይ ዲዛይን አትሟል።
ጋዜጣው፤ ይህ ፕሮጀክት መንግሥትና ሃይማኖት የተነጣጠለ ነው የሚለውን የኬንያ ሕገ መንግሥት የሚያከብር ነው ወይ? የሚል ጥያቄን አቅርቧል።
በርካታ ኬንያውያን በዋጋ ግሽበት እና በኑሮ ውድነት እየተፈተኑ ባለበት በዚህ ወቅት 9 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስወጣ የተገመተው ይህ ቤተ ክርስቲያን ትችቶችን እያስተናገደ ነው።
ሩቶ የቤተክርስቲያኑን ወጪ ከኪሳቸው እከፍላለሁ ቢሉም በሕዝብ ንብረት ላይ ይህን ያህል ትልቅ መዋቅር የመገንባት አቅም አላቸው ወይ የሚል ጥያቄ አጭሯል።
የኬንያ ኢ-አማኒያን ማህበር የቤተ ክርስቲያኑን ግንባታ አስደንጋጭ እና ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ገልጾ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።
"ይህ ድርጊት ጸረ ዲሞክራሲያዊ፤ እንዲሁም ፕሬዚዳንት ሩቶ ክርስቲያናዊ አርበኝነትን የማነሳሳት ተግባር አድርገን ነው የምንመለከተው። ኬንያ የክርስቲያኖች አገር ብቻ እንዳልሆነች ልናሳስባቸው እንፈልጋለን" ሲሉ የማህበሩ ኃላፊ ሐሪሰን ሙሚያ አጽንኦት ሰጥተዋል፥
ዊልያም ሩቶ የመጀመሪያው የኢቫንጀሊካል ክርስትና ተከታይ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ በአንዳንዶችም ዘንድ "የእየሱስ ምክትል" የሚል ቅጽል ስም አትርፈዋል።
ሩቶ በሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ዓመታት ከመጽሃፍ ቅዱስ ጥቅሶች በመምዘዝ በአደባባይ ሲያለቅሱ ታይተዋል። ይህም ባህርያቸው የሳቸውን እምነት የማይከተሉ ኬንያውያንን ያገለለ ሆኖ ታይቷል።
ሩቶ ምክትል ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ከረን በሚገኘው መኖሪያቸው ውስጥ ቤተ ክርስቲያን አቁመው የተለያዩ ዕምነት ያላቸውን የሃይማኖት መሪዎችን ለማስተናገድ ይጠቀሙበት ነበር።
በኬንያ 85 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የክርስትና እምነት ተከታይ ሲሆን፣ 11 በመቶ ገደማ ሙስሊሞች እንዲሁም ሂንዱይዝም እና ባህላዊ እምነት ተከታዮች አሉ።