በጀርመን ሚስቱን ለዓመታት አደንዛዥ ዕጽ በመስጠት የደፈረው እና ፊልም የቀረጸው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

ፈርናንዶ ፒ በምዕራብ ጀርመን፣ አቼን በሚገኘው ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ፊቱን ሸፍኖ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፈርናንዶ ፒ በምዕራብ ጀርመን፣ አቼን በሚገኘው ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ፊቱን ሸፍኖ ነበር

በጀርመን ሚስቱን በተደጋጋሚ አደንዛዥ ዕፅ በመስጠት ራሷን እንድትስት በማድረግ እና በመድፈር እንዲሁም ድርጊቱን በመቅረጽ እና በኢንተርኔት ላይ በማጋራት ወንጀል የተከሰሰ ግለሰብ ስምንት ዓመት ከስድስት ወር እስር ተፈረደበት።

በጀርመን ባለው የግለሰቦች ደህንነትን የመጠበቅ ሕግ ፈርናንዶ ፒ ብቻ ተብሎ የሚጠራው ይህ ተከሳሽ በከባድ የአስገድዶ መድፈር፣ ከባድ የአካል ጉዳት በማድረስ እና የግል መብትን በመጣስ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

ፍርድ ቤቱ የ61 ዓመቱ አዛውንት እአአ ከ2018 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት ውስጥ ባለቤቱን በቤታቸው ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ ሰጥቶ በማደንዘዝ እና በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቶታል።

ግለሰቡ ከስዊዲን ወደ ጀርመን መጥቶ መኖር እንደጀመረ ተገልጿል።

የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ ካትሪና ኤፈርት እንዳሉት ግለሰቡ ጥቃቱን በቪዲዮ ቀርጾ በኢንተርኔት ላይ አጋርቷል።

"እነዚህን ድርጊቶች በቪዲዮ ቀርጾ በኦንላየን ላይ በሚገኙ የውይይት ቡድኖች እና የኢንተርኔት መድረኮች በመልቀቅ ለሌሎች ተጠቃሚዎች ተደራሽ እንዲሆን አድርጓል" ብለዋል።

አብዛኛው የችሎቱ ሂደት የሚስቱን ማንነት ለመጠበቅ በሚል በዝግ ችሎት የተካሄደ ነበር።

የጥቃቱ ሰለባ የሆነችው ባለቤቱ ጠበቃ የሆኑት ኒኮል ሰርቫቲ ለጋዜጠኞች "በክስ ሂደት ውስጥ ከእርሷ ወገን የቀረበው መከራከሪያ ተሰምቷል" እና "መመስከር፣ ስሜቷን መግለጽ እና ተጨማሪ ነገሮች የማስረዳት ሸክሞች ነበሩባት" ሲሉ ተናግረዋል።

ውሳኔው የተከሰተውን ነገር ማካካስ እንደማይችል ጨምረው የተናገሩት ጠበቃዋ "ነገር ግን ነገሮችን ለመቋቋምና ለማስኬድ ትንሽ ሊረዳ ይችላል" ብለዋል።

ተከሳሽ ላይ የተሰጠው ፍርድ አሁንም ለይግባኝ ክፍት መሆኑ ተገልጿል።

ፈርናንዶ ፒ ፍርድ ቤት ቀርቦ የዳኛውን ውሳኔ በሚሰማበት ወቅት ፊቱን በኮፍያ ሸፍኖት ታይቷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፈርናንዶ ፒ ፍርድ ቤት ቀርቦ የዳኛውን ውሳኔ በሚሰማበት ወቅት ፊቱን በኮፍያ ሸፍኖት ታይቷል

የጀርመን ሚዲያዎች ጉዳዩ ባለፈው ዓመት በፈረንሳይ ከታየው የዶሚኒክ ፔሊኮት ክስ ጋር እጅጉን ተመሳሳይነት አለው ብለዋል።

የ72 ዓመቷ ዥዜል ፔሊኮን በወቅቱ የትዳር አጋሯ በሆነው ግለሰብ አደንዛዥ ዕፅ ተሰጥቷት ራሷን ስትስት በኢንተርኔት በመለመላቸው ሰዎች ለዓመታት ያስደፍራት ነበር።

ባለቤቱን ለዓመታት እያደነዘዘ የደፈረው እና ከ50 በላይ በሚሆኑ ወንዶች ያስደፈረው ዶሚኒክ ፔሊኮት የተባለው ፈረንሳዊ በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል።

ጥቃቱ የተፈጸመባት የ72 ዓመቷ ጂዜል ፔሊኮት የፈረንሳይ ሕግ የሰጣትን ማንነቷን የመደበቅ መብቷን በመተው ታሪኳንም ሆነ ራሷን ለሕዝብ ይፋ አድርጋለች።

ይህንን በማድረጓ የዥዜል ጥንካሬ 'ማፈር ያለበት ደፋሪው እንጂ የተደፈረች ሴት አይደለችም' የሚል ንቅናቄን በፈረንሳይ እና በመላው አውሮፓ ፈጥሯል።

የጀርመን የፌዴራል የወንጀል ፖሊስ ቢሮ አደንዛዥ ዕፅ በመስጠት ራሳቸውን እንዲስቱ ከተደረጉ በኋላ በሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት ሰለባ የሚሆኑት "በሙሉ ሴቶች ናቸው" ብሏል።

እንዲህ ያሉ ወንጀሎች ብዙውን ጊዜ የሚፈጸሙት በጋብቻ፣ በፍቅር አጋር፣ በቤተሰብ ወይም በቅርብ በሚያውቋቸው ሰዎች መካከል የሚኖርን "መተማማን ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን በመጠቀም ነው" ብሏል።