ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት መተግበር ለኢትዮጵያ ምን ያስገኛል?
የናይል ተፋሰስ አገራት ለሚያስተሳስራቸው የዓለም ረጅሙ ወንዝ፤ የትብብር እና አጠቃቀም ማዕቀፍ ለማዘጋጀት ሂደት የጀመሩት ከ27 ዓመት በፊት እ.አ.አ በ1997 ነበር። ሦስት አስር ዓመታት ገደማን የፈጀው ስምምነት የማርቀቅ፣ የድርድር እና የማፅደቅ ሂደት ባለፈው ሳምንት እሁድ ጥቅምት 3/2017 ዓ.ም. የመጨረሻውን ደረጃ አጠናቅቆ ተፈጻሚ መሆን ጀምሯል።
የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ወደ ትግበራ ስለመግባቱ በኤክስ (ቲውተር) ገጻቸው መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ስምምነቱ ወደ ሥራ የገባበት ቀን በተፋሰሱ አገራት ዘንድ “ታሪካዊ ምዕራፍ” ሆኖ እንደሚታወስ ገልጸዋል።
ለዓመታት ከቆየ ድርድር በኋላ ግንቦት 2002 ዓ.ም. በኡጋንዳ ኢንቴቤ ከተማ ለፊርማ የቀረበው ስምምነቱ፤ እስከ የካቲት 2003 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት አገራት ፊርማቸውን አኑረውበታል። ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በስምምነቱ ሂደት በታዛቢነት ስትሳተፍ የነበረችው ኤርትራ ፊርማቸውን ያላኖሩ የተፋሰሱ አገራት ናቸው።
ግብፅ እና ሱዳን ደግሞ ጭራሹኑ ስምምነቱን አልተቀበሉትም።
ስምምነቱን ተቀብለው የፈረሙ አገራትም ማዕቀፉን በየአገሮቻቸው ምክር ቤቶች አፀድቀው ሕግ ለማድረግ ዓመታት ወስዶባቸዋል። ስምምነቱን በማጽደቅ ቀዳሚዋ አገር ኢትዮጵያ ነበረች። ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ደግሞ እስከ ነሐሴ 2011 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ አጽድቀውታል።
የስምምነት ማዕቀፉ ወደ ተግባር እንዲገባ እና በውስጡ የያዛቸው መርሆዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ፤ ከተፋሰሱ 11 አገራት ውስጥ በስድስቱ መፅደቅ አስፈላጊ ነበር። ኢትዮጵያ፤ ስምምነቱ ያፀደቁ አገራት ቁጥር ስድስት ደርሶ ተፈጻሚ መሆን እንዲጀምር “ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ” ስታከናውን መቆየቷን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአገራት መሪዎችን ባገኙባቸው አጋጣሚዎች ስለ ናይል ውሃ “ፍትሐዊ የሆነ የጋራ ማልማት ትብብር” ሲያነሱ እንደነበር ዶ/ር ሀብታሙ ያስታውሳሉ።
ስምምነቱን በማፅደቅ አምስተኛዋ አገር የሆነችው ብሩንዲ፤ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ሕግ አድርጋ የተቀበለችው ፊርማዋን ካኖረች ከ12 ዓመታት በኋላ ነው። ስምምነቱ ለፊርማ በቀረበበት ወቅት አገር ያልነበረችው ደቡብ ሱዳን ደግሞ ሐምሌ 2016 ዓ.ም. ማዕቀፉን ተቀብላ ያጸደቀች ስድስተኛዋ አገር ሆናለች።
ዶ/ር ሀብታሙ፤ ስምምነቱ ወደ ሥራ እንዲገባ አስፈላጊ የሆኑት ሁለት አፅዳቂ አገራት በአንድ ዓመት ውስጥ የተገኙት “ተሠርቶበት ነው” ይላሉ።
“በተለይ የደቡብ ሱዳን ኤምባሲያችን ከፍተኛ ሥራ ሠርቷል። አምባሳደር ነቢል [መህዲ] ትልቅ ተግባር አከናውነዋል። ምክር ቤቶቹን በማሳመን፣ እዚያ አካበቢ ላይ የሚሠሩ ሥራዎችን ተግባራዊ እንዲሆኑ በማድረግ ትልቁን ድርሻ ስለተወጡ፤ ስለተሠራበትም ነው የመጣው” ሲሉ የኢትዮጵያን ጥረት አስረድተዋል።
የስምምነቱ ወደ ተግባር መግባት “ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስኬት” እንደሆነ የሚናገሩት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ፤ “ከፍተኛ ኃይል ማሰባሰብ የቻልንበት እና እውነታውን ለዓለም ማስረዳት ላይ ድርሻውን ከፍ የሚያደርግ ሥራ [ነው]” ሲሉ ይገልጹታል።
የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ ይዘት ምንድነው?
የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ የተፋሰሱ አባል ከሆኑት 11 አገራት ውስጥ ዘጠኙ ለዓመታት ድርድር ያደረጉበት ሰነድ ነው። የተፋሰሱ አባል የሆነችው ኤርትራ የተሳተፈችው በታዛቢነት ሲሆን፣ ሌላኛዋ የናይል ወንዝ አካል ደቡብ ሱዳን ደግሞ አገር ሆና የተመሠረተችው ከስምምነቱ ፊርማ በኋላ ነው።
ስምምነቱ ድርድር ሲያደርጉ ከነበሩት አገራት መካከል የታችኛው ተፋሰስ አገራት በመባል የሚጠቀሱት ግብፅ እና ሱዳን ይገኙበታል። ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ታንዛኒያ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎም ተሳትፈውበታል።
የስምምነት ማዕቀፉን ሂደት በበላይነት የሚመራው “የናይል ቤዚን ኢኒሺዬቲቭ”፤ የስምምነቱን ወደ ሥራ መግባት ባስታወቀበት መግለጫው፤ ስምምነቱ በተፋሰሱ አገራት መካከል “የትብብር፣ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት እና የመከባበበር” መርሆዎችን የሚደነግግ እንደሆነ ገልጿል።
ከዚህ ቀደም በናይል ቤዚን ኢኒሺዬቲቭ ሥር የሚገኘውን የምሥራቅ ናይል ቴክኒካዊ ቀጠናዊ ጽህፈት ቤትን ዋና ዳይሬክተር ሆነው የመሩት አቶ ፈቅ አህመድ በዚህ አገላለፅ ይስማማሉ።
በአሁኑ ሰዓት በውሃ ሀብት ልማት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና ሀይድሮ ዲፕሎማሲ አማካሪ የሆኑት አቶ ፈቅ፤ “ስምምነቱ የናይል ተፋሰስ አገራት ሉዐላዊነታቸው እና የግዛት አንድነታቸው ተጠብቆ የናይል ውሃን በጋራ ለመጠቀም፣ ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብ እና ለማስተዳደር በፈቃደኝነት ተስማምተው በራሳቸው ላይ አስገዳጅ እንዲሆን የገቡት ስምምነት ነው” በማለት የማዕቀፉን ምንነት ያስረዳሉ።
በ45 አንቀጾች የተዋቀረው የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ሦስት ዋነኛ መርሆዎች እንዳሉት አቶ ፈቅ ያስረዳሉ። “ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም” የሚለው መርህ ቀዳሚው ሲሆን “በሌሎች ተጠቃሚዎች ላይ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ ግዴታ” ሁለተኛው መርህ መሆኑን ያነሳሉ። በሦስተኛነት የሚጠቀሰው የስምምነቱ ዋና መርህ “በፈቃደኝነት መተባበር” መሆኑንም ይገልጻሉ።
ስምምነቱ፤ “የናይል ተፋሰስ አገራት በየግዛቶቻቸው የናይል ውሃን ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መጠቀም” እንደሚችሉ የሚገልፅ ሲሆን፣ የውሃ ልማት ሥራዎቻቸውም “የተሻለ እና ዘላቂ” ጥቅምን የሚያስገኙ እንደሚሆኑም አስፍሯል። እያንዳንዱ የተፋሰሱ አገር በናይል ወንዝ የውሃ ሀብት ላይ “ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ ድርሻ” እንደሚኖረው ያስቀምጣል።
ይሁንና አገራቱ በግዛታቸው ውስጥ ያለውን የናይል የውሃ ሀብት ሲጠቀሙ “በሌሎች የተፋሰሱ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስ ሁሉንም አስፈላጊ እርምጃዎች የመውሰድ” ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
ስምምነቱ ውስጥ የተካተቱት አገራት የተጣለባቸው ሌላኛው ግዴታ የመረጃ ልውውጥን የሚመለከት ነው። አገራቱ ናይል ወንዝን በተመለከተ የሚወስዱትን እርምጃ እንዲሁም የውሃ ሀብትን በተመለከተ “የተዘጋጀ እና ጠቃሚ ዳታ እና መረጃ በመደበኛ መልኩ” ለሌሎች የተፋሰሱ አገራት እንዲሰጡ ይጠበቃል።
ሌሎች የተፋሰሱን ተጠቃሚዎች የማሳተፍ ጉዳይ ደግሞ አገራት በውሃ ሀብቱ ላይ ፕሮጀክት ለማከናወን በሚያቅዱበት እና በሚተገብሩበት ወቅት የሚከወን ነው።
በስምምነቱ መሠረት፤ አገራት በናይል ውሃ ላይ ፕሮጀክት ለማከናወን ሲያስቡ በዕቅድ እና ትግበራው ሂደት ላይ በግንባታው ተፅዕኖ ሊደርስባቸው የሚችሉ አገራትን “ተገቢ በሆነ መልኩ” እንዲያሳትፉ ይገደዳሉ። አገራት በናይል ወንዝ ላይ የሚወስዱትን እርምጃም ሆነ የውሃ ሀብቱን የተመለከቱ መረጃዎች ለሌሎች አገራት የሚያደርሱት በስምምነቱ አማካኝነት በሚቋቋመው “የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን” ነው።
ስምምነቱ ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ የሚቋቋመው ይህ ኮሚሽን፤ በስምምነት ማዕቀፉ ውስጥ መርሆዎች፣ መብቶች እና ግዴታዎች ተፈጻሚነትን የሚያመቻች ተቋም ነው። የስምምነቱን አፈጻጸም በተመለከተ በአገራቱ መካከል አለመግባባር ሲከሰትም የሚፈታው በዚሁ ኮሚሽን አማካኝነት ነው።
ኮሚሽኑ፤ በመዋቅሩ ውስጥ የአገር መሪዎች ኮንፈረንስ፣ የሚኒስትሮች ካውንስል እንዲሁም ሁለት አማካሪ ኮሚቴዎችን ይይዛል። በዋና ፀሐፊም ይመራል። የተፋሰሱ አገራት መሪዎችን የሚይዘው ኮንፈረንስ የተቋሙ “የበላይ የፖሊሲ አውጪ አካል” ነው። በኮሚሽኑ መዋቅር ውስጥ ብዙዎቹ ኃላፊነቶች ተሰጡት ለሚኒስትሮች ካውንስል ነው።
የኮሚሽኑ አስተዳደር አካል የሆነው ይህ ካውንስል፤ የማዕቀፉን አፈጻጸም የሚቆጣጠር እና ለአማካሪ ኮሚቴዎች ኃላፊነት የሚሰጥ ነው። ካውንስሉ፤ ሕጎችን፣ አሠራሮችን እና መመሪያዎችን የማፅደቅ ሥልጣን ተሰጥቶታል። የተፋሰሱ አገራት የፍትሐዊ እና ምክንያታዊ ውሃ አጠቃቀምን የተመለከቱ ውሳኔዎች የሚተላለፉትም በዚህ ካውንስል ነው።
የስምምነት ማዕቀፉ “የካውንስሉ ውሳኔዎች የናይል ተፋሰስ አገራት ተፈጻሚነት ያላቸው” መሆናቸውን ይገልጻል።
የስምምነቱ ያስቀመጣቸው መርሆዎች እና ኢትዮጵያ
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሀብታሙ፤ የማዕቀፉ ትልቁ ዓላማ “ከዚህ በፊት የነበረውን ኢ-ፍትሐዊ የናይል ወንዝ አጠቃቀም” መቀየር እንደሆነ ይናገራሉ። ሚኒስትሩ “የውሃውን ፍትሐዊ እና እኩል የመጠቀም መብት ማረጋገጥ በሚያስችል ደረጃ ሕግ አውጥቶ ማስቀጠል ስለሚያስፈልግ ይህ ተሠርቷል” ሲሉ የስምምነቱን ጥቅም ያስረዳሉ።
የናይል ወንዝ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት በመባል የሚታወቁት ግብፅ እና ሱዳን “ይንጸባረቅ የነበረው የውሃ ሀብት አጠቃቀም የበላይነት (Hydro-hegemony) በፍትሐዊ እና ዕኩል ተጠቃሚነት” የቀየረ እንደሆነም ይጠቅሳሉ።
በውሃ ሀብት ልማት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና ሀይድሮ ዲፕሎማሲ አማካሪው አቶ ፈቅ አህመድም፤ አዲሱ ስምምነት በናይል ወንዝ ላይ ብቸኛ የነበረው የግብፅ እና ሱዳን ስምምነት በሌሎች የተፋሰሱ አገራት ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ የሚያስወግድ እንደሆነ ይስማማሉ።
አቶ ፈቅ እንደሚያስረዱት የናይል ወንዝን በተመለከተ የሚታወቁት “የቅኝ ግዛት እና የድኅረ ቅኝ ግዛት” በመባል የሚጠቀሱት የሁለቱ አገራት ስምምነቶች ናቸው። እ.አ.አ በ1929 የተፈረመው የመጀመሪያው ስምምነት ግብፅ እና ሱዳንን በቅኝ ግዛት ታስተዳደር በነበረችው ብሪታንያ መካከል የተደረገ ነው።
ይህ ስምምነት ከናይል የውሃ ድርሻ ውስጥ 48 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር የሚሆነው ውሃ ለግብፅ እንዲመደብ፤ ሱዳን ደግሞ 4 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር እንድታገኝ የወሰነ ነው።
ሱዳን ነጻ ከወጣች በኋላ ሁለቱ አገራት የውሃ ድርሻቸውን በጨመረ ሁኔታ እ.አ.አ በ1959 ስምምነታቸውን አሻሽለውታል። በዚህ የድኅረ ቅኝ ግዛት ስምምነት መሠረት ግብፅ በናይል ወንዝ ውሃ ላይ የነበራት ድርሻ ወደ 55.5 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ከፍ ብሏል። የሱዳንም ድርሻም በተመሳሳይ ወደ 18.5 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር አድጓል።
እነዚህ ስምምነቶች፤ የናይልን ውሃ “ለሁለቱ አገራት ሰጥቶ” ሌሎቹን የተፋሰሱ አገራት “የበይ ተመልካች” ያደረገ እንደሆነ አቶ ፈቅ ይከራከራሉ። ሌሎች አገራት በናይል ወንዝ ላይ ልማት ማከናወን ሲፈልጉ ፕሮጀክታቸው የሚያደርሰው ተፅዕኖን ለማወቅ እንደ መለኪያ የሚውለው በእነዚህ ስምምነቶች ለሱዳን እና ግብፅ የተሰጠው የውሃ ድርሻ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
አቶ ፈቅ፤ “እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ልማት ስታካሂድ ግብፆች [ሲያነሱ የነበረው] የ1959 እና 1929 ስምምነት የሰጠንን የውሃ ድርሻ ይጎዳል የሚል ነው። የዓለም ማኅበረሰብም ይህንን መለኪያ ወስዶ ነው ጫና እየፈጠረ ያለው” ሲሉ በሌሎች አገራት ዘንድ የሚታወቀው ስምምነት ይህ መሆኑ ያመጣውን ተፅዕኖ ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ እነዚህን ስምምነቶች ባትቀበልም “የዓለም ማኅበረሰብ እውቅና ሰጥቶት ስለነበረ ጫና ሲፈጠር” መቆየቱን አክለዋል። ይህንን የሚጋሩት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሀብታሙም፤ 85 በመቶው የሚሆነውን የናይል ውሃ የምታዋጣው ኢትዮጵያ ባልተቀበለችው ስምምነት ምክንያት “ከፍተኛ ተግዳሮት” ሲያጋጥማት እንደነበር አስታውሰዋል።
ዶ/ር ሀብታሙ፤ “የአሁኑ ስምምነት አገራት ተስማምተንበት ያደረግነው የጋራ ስምምነት እና የጋራ ሕግ ነው። ስለዚህ የልማት አጋሮቻችን በፊት ሲያጣቅሱት የነበረው የሁለትን አገር ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቅ ሕግ ከሚያዩ በትንሹ የስድስት አገራትን [መብት] ማስከበር፣ የታችኞቹንም [ጥቅም] ሳይጎዳ የተዘጋጀውን ሰነድ ያዩታል ብለን እናምናለን” ሲሉ ተስፋቸውን አንጸባርቀዋል።
አማካሪው አቶ ፈቅ በከኩላቸው፤ “ከዚህ በኋላ በተፋሰሱ ውስጥ ሁለት ስምምነቶች ይኖራሉ። አንደኛው ሁሉም አገራት የተደራደሩበት፤ ስድስት አገራት ያጸደቁት [ነው]። ሁለተኛው ደግሞ ሁለት አገራት ብቻ ውሃውን ሙሉ በሙሉ ለራሳቸው የተከፋፈሉበት ነው። ስለዚህ የዓለም ማኅበረሰብ ፍትሐዊ ከሆነ የትኛው ትክክል እንደሆነ ለይቶ መውሰድ ይችላል” ሲሉ የስምምነቱ ወደ ተግባር መግባት የሚያመጣውን ለውጥ ያስረዳሉ።
“ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ የምትገዛው ለዚህኛው ስምምነት ነው” የሚሉት አቶ ፈቅ፤ በአዲሱ ስምምነት ላይ በተቀመጠው መሠረት ኢትዮጵያ በናይል ውሃ ላይ ለምታከናውናቸው ፕሮጀክቶች ማረጋገጥ የሚጠበቅባት “የምታደርገው የልማት ሂደት የራሷ ፍትሐዊ የልማት ድረሻ ላይ የሚወቅድ መሆኑን ማረጋገጥ” ነው።
ይህ የማረጋገጥ ሂደት የሚከናወነው ስምምነቱ ባቋቋመው የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን አማካኝነት በመሆኑ፤ የአገራትን ፕሮጀክቶች “ለማሰናከል” የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚያስቀር ይከራከራሉ።
“[ኢትዮጵያ የምትገዛው በዚህ ስምምት መሆኑን] በትክክል ማስረዳት ከተቻለ፤ አንደኛ ጫና ይቀንሳል። ሁለተኛ፤ ብድርም ድጋፍም ማግኘት ይቻላል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የሦስተኛ ወገኖችን ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። ለሚደረገው የልማት፣ ግንባታ [ሥራ] ሕጋዊ ከለላ ይሰጣል። በየዓለም አቀፍ መድረክ እየሄዱ መክሰስ የሚባለው ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል” ሲሉ ኢትዮጵያ በስምምነቱ የምታገኛቸውን ጥቅሞች ይዘረዝራሉ።
ኢትዮጵያን ያስደሰተው የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ተፈጻሚ መሆን ግን በግብፅ እና ሱዳን ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል። የሁለቱ አገራት የናይል ውሃ ቴክኒካል ኮሚቴ፤ ከስምምነቱ ተግባራዊ ከመሆኑ አንድ ቀን በፊት ባወጣው መግለጫ፤ ስምምነቱ በሁለቱ አገራት ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን አስታውቋል።
የሁለቱ አገራት ሚኒስትሮች ካደረጉት ውይይት በኋላ የወጣው መግለጫ፤ ስምምነቱን የሚጠራው “ረቂቅ ሰነድ” በሚል ነው። “ረቂቅ ሰነዱ”፤ “አስፈላጊው መግባባት ያልተደረሰበት” እና “የዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎችን እና ምርጥ ዓለም አቀፍ አሠራሮችን ያልተከተለ” እንደሆነ በጥቀስ ማዕቀፉን አጣጥሏል።
በስምምነቱ አማካኝነት የሚቋቋመው ኮሚሽንም “በምንም ዓይነት ሁኔታ የናይል ተፋሰስን በሙሉ የሚወክል ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበትም” የአገራቱ የጋራ መግለጫ አሳስቧል።
የውሃ ሀብት ልማት አማካሪው አቶ ፈቅ፤ የስምምነት ማዕቀፉ ግብፅ እና ሱዳን ያልተቀበሉት እና ያልፈረሙበት መሆኑን በማስታወስ “እንዲቀበሉትም እንደማይጠበቅ” ይገልጻሉ። ሁለቱ አገራት ቀድሞውንም የነበሯቸውን የቅኝ ግዛት እና የድኅረ ቅኝ ግዛት ስምምነቶችን ይዘው መቀጠል እንደሚችሉ የሚያነሱት አማካሪው፤ እነዚህ ስምምነቶች ግን ከአሁን በኋላ ማስተዳደር የሚችሉት “በአገራቱ ድንበር ውስጥ የሚገባውን ውሃ ብቻ” መሆኑን ያስረዳሉ።
“የላይኛው ተፋሰስ ውሃ ከዚህ በኋላ የሚተዳደረው በዚህኛው ስምምነት ነው። ስለዚህ ያኛውን ስምምነታቸውን አምጥተው መጫን አይችሉም። እኛም እነሱ ላይ ይሄንን መጫን አንችልም። የእነሱ ስምምነት ግን ድንበራቸው ውስጥ ያለውን ውሃ ስለሚያስተዳድር ከዚያ ጋር ምንም የሚያገናኘን ነገር የለም” ይላሉ።
ግብፅ እና ሱዳንን ያላስማማው ንዑስ አንቀጽ
የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ግብፅ እና ሱዳንን ጨምሮ በሂደቱ ላይ በተሳተፉት ዘጠኝ የተፋሰሱ አገራት መካከል ድርድር የተካሄደበት ሰነድ እንደሆነ የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሷል። ከአንድ አንቀጽ በስተቀር ሁሉም የስምምነቱ ክፍሎች ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው እንደሆኑ መግለጫው ላይ ሰፍሯል።
ሁለቱን አገራት ያላስማማው ንዑስ አንቀፅ የሚገኝበት አንቀፅ 14 የውሃ ደኅንነትን የሚመለከት ነው። የዚህ አንቀጽ የመጀመሪያ ንዑስ አንቀፅ ሁሉም አገራት “የውሃ ደኅንነትን ለማረጋገጥ እና ለማስቀጠል” በጋራ እንደሚሠሩ የሚገልፅ ሲሆን፣ ይህ በሁሉም አገራት ስምምነት የተደረሰበት ነው።
ስምምነት ያልፈጠረው ንዑስ አንቀጽ አገራቱ “የትኛውም ሌላ የናይል ተፋሰስ አገር የውሃ ደኅንነትን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ” ማድረስ እንደሌለባቸው የደነገገ ነው። ይህ ንዑስ አንቀፅ ግብፅ እና ሱዳንን ያላስማማ ሲሆን፣ ካይሮ በሌላ እንዲተካ አማራጭ አቅርባለች።
የግብፅ አማራጭ “[አገራት] በማንኛውም ሌላ የናይል ተፋሰስ አገር የውሃ ደኅንነት እንዲሁም አሁናዊ አጠቃቀም እና መብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማድረስ የለበትም” የሚል ነው። ይህ አማራጭ በመጀመሪያ ንዑስ አንቀፅ ላይ “ከፍተኛ ተፅዕኖ” የሚል ሃሳብ “አሉታዊ ተፅዕኖ” በሚል የተካ ነው።
የግብፅ አማራጭ፤ የመጀመሪያው ንዑስ አንቀፅ ተፅዕኖ መድረስ የሌለበት በአገራቱ “የውሃ ደህንነት” ላይ እንደሆነ ካስቀመጠው ሃሳብ በተጨማሪ በአገራቱ “አሁናዊ አጠቃቀም እና መብትንም” ሊነካ እንደማይገባ ያመለከተ ነው።
አቶ ፈቅ፤ ይህ የግብፅ አማራጭ ሁለቱ አገራት “አሁን የሚጠቀሙትን የውሃ መጠን እና 1959 ስምምነት የተሰጣቸውን የውሃ መብት እንዲያከበር” የሚጠይቅ እንደሆነ ያስረዳሉ። በዚህ ንዑስ አንቀፅ ምክንያት ስምምነት ላይ ባለመደረሱ፤ አገራቱ ሌሎቹን የስምምነቱን አንቀጾች አፅድቀው ድርድር ለመቀጠል ተስማምተው እንደነበር አቶ ፈቅ ያስታውሳሉ።
የስምምነት ማዕቀፉ ተፈጻሚ መሆን በጀመረ በስድስት ወር ውስጥ በዚህ ንዑስ አንቀጽ ላይ የሚደረገው ድርድር እንደሚጠናቀቅ በስምምነት ሰነዱ ላይ ሰፍሯል። ይሁንና ንዑስ አንቀጹን የተቃወሙት ግብፅ እና ሱዳን በአሁኑ ሰዓት የኮሚሽኑ አባል ባለመሆናቸው መጀመሪያ ቀርቦ የነበረውን ሀሳብ የሚቃወም አካል ይኖራል ተብሎ እንደማይጠበቅ አቶ ፈቅ ያገልጻሉ።
“የላይኛው ተፋሰስ አገራት ቀድሞም ተቀብለውታል። ‘ማንኛውም የናይል ተፋሰስ አገር የሌላኛውን የተፋሰሱን አገር የውሃ ዋስትና ማክበር አለበት’ የሚለውን ስለተቀበሉት የሚደራደሩት ምንም ነገር የለም። [ግብፅ እና ሱዳን] ‘እንደራደራለን’ ብለው ከመጡ ግን ያው በዚህ ጉዳይ ላይ ተደራድረው በስድስት ወር ውስጥ ይቋጩታል ተብሎ ነው የሚጠበቀው” ሲሉ አብራርተዋል።
የናይል ቤዚን ኢኒሺዬቲቭ ባወጣው መግለጫም ስምምነት ያልተደረሰበት ንዑስ አንቀጽ ኮሚሽኑ በተቋቋመ በስድስት ወራት ውስጥ ውሳኔ እንደሚያገኝ አስታውሷል። ስምምነቱን ያልፈረሙ አገራት “በየትኛውም ጊዜ እንዲቀላቀሉ ማዕቀፉ ክፍት” መሆኑን ገልጿል።
የኮሚሽኑ አባል መሆን አገራት “በናይል ውሃ ሀብት ላይ ያላቸው ተደራሽነት እና ጥቅም ላይ ተፅዕኖ በሚያሳድር ውሳኔ ላይ ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ” እንደሚያደርጋቸው አስገንዝቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የስምምነቱን ተፈጻሚ መሆን መጀመር አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ በተመሳሳይ አገራቱ ማዕቀፉን እንዲቀላቀሉ ጠይቀዋል። ግብፅ እና ሱዳን ስምምነቱን እንዲቀላቀሉ ኢትዮጵያ “ከሌሎች የላይኛው ተፋሰስ አገራት ጋር በጋራ የማግባባት ሥራ” እንደምትሠራ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሀብታሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የውሃ ሀብት ልማት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና ሀይድሮ ዲፕሎማሲ አማካሪው አቶ ፈቅ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት ማዕቀፉን ሊቀላቀሉ የሚችሉት “ኮሚሽኑ ጠንካራ ሲሆን” መሆኑን ያነሳሉ።
“ኮሚሽኑ ጠንካራ ሆኖ ትላልቅ ውሳኔዎችን የሚወስን ከሆነ፣ የላይኛው ተፋሰስ አገራት የሚቋቋመውን ኮሚሽን በፋይናንስ ደግፈው፣ ጠንካራ ሥልጣን ሰጥተው፣ ብዙ ሥራዎችን እንዲሠራ፣ እንዲያስተባብር አቅም ከሰጡት፤ ግብፅ እና ሱዳንም ትላልቅ የናይል ውሳኔ ከሚወሰንበት መድረክ መጥፋት፣ መራቅ ስለማይችሉ እነሱንም ያመጣል” ሲሉ ያስረዳሉ።