የሰላም ስምምነቱ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ለምን ‘ድል’ ሆነ?

የፎቶው ባለመብት, FANA BROADCASTING CORPORATE
- ፀሐፊ, አሌክስ ዲ ዋል
- የሥራ ድርሻ, የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ
ሁለት ዓመት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማብቃት የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት የደረሱትን የሰላም ስምምነት አገራት እና ተቋማት በበጎ ጎኑ ተቀብለውታል።
ጥያቄው ግን ስኬታማ ይሆናል ወይ የሚለው ነው?
የሰላም ስምምነቱ በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ ከተፈረመ ከአንድ ቀን በኋላ በትግራይ ተራሮች የከባድ መሳሪያ ተኩስ ድምጽ መሰማቱ ቀጥሏል።
ሁለቱ አካላት የፈረሙት የሰላም ስምምነት ዓላማ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕምድ ከሁለት ዓመት በፊት በህወሓት ላይ “የሕግ ማስከበር እርምጃ” ብለው ከጀመሩት ኦፕሬሽን ጋር በስፋት የሚጣጣም ነው።
በስምምነቱ መሠረት የህወሓት ታዋጊዎችን ትጥቅ ለማስፈታት የሚኖር ዝርዝር አካሄድ ይኖራል።
ይህ ስምምነት የተፈጸመው ከትግራይ ተወላጆች ፍላጎት በተለየ መልኩ ከ ‘’ትግራይ መንግሥት” ጋር ሳይሆን ከህወሓት ጋር ነው።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሁለት ዓመት በፊት በህወሓት የበላይነት የተጠናቀቀው የትግራይ ምርጫን ውድቅ በማድረግ ሌላ ምርጫ እንዲደረግ እቅድ አላቸው።
የፌደራሉ መንግሥት ህወሓት ሙሉ በሙሉ እጅ እንዲሰጥ ቢፈልግም ያ ሳይሆን ቀርቷል። ህወሓትን ከሽብርተኝነት መዝገብ ፍቆ ትግራይ ወደፊት ልትተዳደር ስለምትችልበት ሁኔታ ከህወሓት ጋር ፖለቲካዊ ድርድር ለማድረግ ቃል ገብቷል።
በስምምነቱ መሠረት ሁለቱም አካላት ሥራ ላይ ባለው የአገሪቱ ሕገ-መንግሥት ተገዢ ለመሆን ተስማምተዋል። ይህም በጦርነቱ ጅማሮ ወቅት በአማራ ኃይሎች ተይዞ የሚገኘው ለም የሆነው የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት መፍትሄ መስጠትን ይጨምራል።
ለአካባቢው ምላሽ ከመሰጠቱ በፊት የትግራይ አስተዳደር ወይም ከስፍራው የተፈናቀሉት ቀድመው ስለመመለሳቸው ያለው ነገር የለም።
የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን የሚመለከተው የስምምነቱ ክፍል የበርካቶችን ሕይወት ለቀጠፈው ረሃብ ማብቂያ ሊሆን ይችላል።
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጥምር ጦር፤ አንዲሁም በአማራ ኃይሎች ለሁለት ዓመታት መንገድ ተዘግቶባቸው ረሃብ ውስጥ በመቆየታቸው የትግራይ መሪዎች ተረትተዋል።
የትግራይ መሪዎች ከዚህ ውሳኔ የደረሱት የትግራይ ሕዝብ ኅልውናን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይመስላል።
ሰኔ ላይ ጦርነቱ ዳግም ማገርሸቱን ተከትሎ የእርሻ ስራቸውን ማከናወን ያልቻሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
ሰዎች ታክመው ሊድኑ በሚችሉ በሽታዎች ሕይወታቸው እያለፈ ነው። ሆስፒታሎች እንደ ኢንሱሊን እና አንቲባዮቲክስ ያሉ መሠረታዊ መድሃኒቶች ጨርሰዋል። የዚህ ቀውስ ማብቅያ ምልክት የለውም ነበር።
መሠረታዊ ጥያቄዎች
በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ። ሦስቱ ደግሞ መሠረታዊ ናቸው።
የመጀመርያው የኤርትራ ጉዳይ ነው።
ከምዕራባውያን ዲፕሎማቶች የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ የትግራይ ተዋጊዎችን መስመር የበታተነው ከአሥመራ ትዕዛዝ የሚቀበል የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ጥምር ጦር የማጥቃት እርምጃ ነው።
በዚህ የሰላም ስምምነት ላይ ኤርትራ በስም አልተጠቀሰችም። ይሁን እንጂ በስምምነቱ ላይ “ከውጪ ኃይል” ጋር መተባበር የሚል ሃርግ በአንድ አንቀጽ ሰፍሯል። ይህም ኤርትራን የሚያመላክት ሊሆን ይችላል።
ብዙዎች የፌደራሉ መንግሥት ይህን በማክበሩ ላይ ጥርጣሬ አላቸው።
በስምምነት ውስጥ ያልተካተቱት የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ምንም አይነት ስምምነት ላይ ቢደርሱ ኢሳያስ ጦርነቱ ማስቀጠል ይችላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሁለተኛው ጉዳይ ክትትል እና ማረጋገጥ ነው።
ይህ ስምምነተ ምዕራባውያንን በሩቁ በማቆየቱ ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ስርትራቴጂ ድል ነው።
ስምምነቱን መከታተል፣ ማጣራት እና አፈጻጸሙ በስምምነቱ መሠረት መሆኑን የሚያረጋግጠው 10 አባላት ያሉት ቡድን ለቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴንጉን ኦባሳንጆ ሪፖርት ያደርጋል።
ኦባሳንጆ ደግሞ ሪፖርት የሚያደርጉት ለአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ነው።
ለአፍሪካ ሕብረት ሰላም እና ደኅንነት ምክር ቤት እንኳ አይደለም። የተባበሩት መንግሥታት ሙሉ በሙሉ ተገልሏል።
የጥሰት ሪፖርቶች እና አለመግባባቶች የሚፈቱት በሁለቱ ሰዎች ብቻ ነው- በኦባሳንጆ እና ፋኪ።
እንዲህ አይነት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው የሰላም ስምምነቶች በዓለም አቀፍ አጋሮች ጭምር ክትትል እንዲደረግባቸው መፍቀድ የተለመደ ነው።
የአፍሪካ ኅብረት የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ እና ኢጋድ ሰምምነቱን እንዲታዘቡ ቢፈቅድም ማናቸውም ስምምነቱን አልፈረሙም።
የአውሮጳ ሕብረት ምንም እንኳ የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛው ለጋሽ ቢሆንም፣ የሰላም ስምምነቱን እንዳይታዘብ ተደርጓል።
ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ኅብረት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ኢትዮጵያ በበከሏ ከፍተኛ የሆነ የውጪ እርደታ ትፈልጋለች።
ሦስተኛው ነጥብ ፍትህ እና ተጠያቂነት ማስፈን ነው።
ስምምነቱ የኢትዮጵያ መንግሥት “አጠቃላይ የሆነ ብሔራዊ የሽግግር ስርዓት ፖሊሲ’ እንደሚያዘጋጅ ያስቀምጣል።
ነገር ግን እንደ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ካውንስል ወይንም የአፍሪካ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን በመርማሪነት አልጠቀሰም።
ኦባሳንጆ የስምምነት ሰነዱ ሲፈረም ማየት መቻላቸው አንዱ እርምጃ ቢሆንም፣ ተግባራዊ ማድረግ ላይ ግን ብርቱ ስራ ይጠይቃል።
ለሰላም ያለው ተስፋ፣ በትግራይ የሚደርሰው ግድያ እና ረሃብ ለማቆም እንዲሁም የአገሪቱ መረጋጋት የተመሰረተው በፌደራል መንግሥቱ በጎ ፈቃድ ላይ ነው።
የመጀመርያው ፈተና ህወሓት እና መንግሥት “ጠብ አጫሪ ፕሮፓጋንዳዎችን፣ ቅስቀሳዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን” ለማቆም በመስማማት የጋራ መግለጫ ማውጣት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
‘አንገት የሚያስደፉ የስምምነት አንቀጾች’
በአገር ውስጥ እና በባህር ማዶ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በስምምነቱ ደስተኞች አይደሉም።
የተወሰኑ የትግራይ ጦር አመራሮች ‘ይህንን አንገት የሚያስደፋ ስምምነት’ ተቀብለው ከመገዛት ይልቅ የሽምቅ ውግያን ማድረግን ሊመርጡ ይችላሉ።
በርካታ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እድሉ ካላቸው ወደሰላም፣ ዲሞክራሲ እና መረጋጋት መድረክ ለመመለስ እና ለሰላም እድል ለመስጠት ፈቃደኝነቱ አላቸው ብለው ያምናሉ።
ሌሎች ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፤ ከፍተኛቁጥር ያለው የጦር ኃይል በማሰማራት፣ ረሃብ እንዲኖር በማድረግ እና የኮሙኑኬሽን መስመሮችን በመዝጋት ዓላማን ማስፈጸሚያ መሳርያ ማድረግን እንደሚቻል ስለመማራቸው ይሰጋሉ።
ኢትዮጵያኖች በበኩላቸው በትግራይ የተከሰተው ዓይነት በሌሎች ክልሎች፣ በኦሮምያ፣ ያሉ የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት እንዳይውል ስጋት አላቸው።
ይህ ሳምምነት የተደረሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አገሪቱን ከቀውስ አዙሪት ያወጧታል በሚል እምነት ነው።
የመጀመርያው ተስፋ የነበረውም ሐሙስ ዕለት የጠብመንጃ አፈሙዞች ዝም ይላሉ የሚለው ነበር። ያ ግን ሳይሆን ቀርቷል።
ትናንት ሐሙስ፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራሠራዊት በሶስት ግንባሮች ከባድ ውግያ ሲያካሄዱ መዋላቸውን በክልሉ የሚገኙ ምንጮች ይናገራሉ።
የትግራይ ተዋጊዎችም የያዙትን ቦታ ላለመልቀቅ ከባድ ፍልሚያ አድርገዋል።
የሰላም ስምምነቱን በባለቤትነት የመራው የአፍሪካ ኅብረት እና የተገኙ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ተዓማኒነታቸው የሚታየው በሁለቱምወገን የሚኖርን ጥሰት በግልጽ መኮነን ሲችሉ ነው።













