በአማራ ክልል እየተዋጉ ያሉ ወገኖች ግጭት አቁመው ወደ ንግግር እንዲገቡ የአፍሪካ ኅብረት ጠየቀ

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ

የፎቶው ባለመብት, Moussa Faki Mahamat/ Twitter

በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት እንዳሳሰበው የገለጸው የአፍሪካ ኅብረት ተፋላሚ ወገኖች ግጭቱን አቁመው ወደ ንግግር እንዲገቡ ጠየቀ።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት በክልሉ ውስጥ እየተዋጉ ያሉ ወገኖች ግጭቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ፣ እንዲሁም የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቁ ረቡዕ ነሐሴ 10/2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ አሳስበዋል።

ሊቀ መንበሩ በተጨማሪም በቀጣይነት በክልሉ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ውጊያውን አቁመው ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ወደ ንግግር እንዲገቡም ጠይቀዋል።

ያለውን ግጭት በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነ የገለጸው የአፍሪካ ኅብረት ለኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት፣ የግዛት አንድነት፣ ሉዓላዊነት ቀናዒነት እንዳለውም ሊቀ መንበሩ ገልጸዋል።

ኅብረቱ በአገሪቱ እንዲሁም በቀጠናው ውስጥ መረጋጋት እንዲሰፍን እና ለዚህም በኢትዮጵያ ተነሳሽነት ለሚደረግ የሰላም መፍትሄ ድጋፍ እንደሚያደርግ ሊቀመንበሩ ባወጡት መግለጫ ላይ ሰፍሯል።

በክልሉ የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ በንግግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቀናት በፊት ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ከፍትህ ሚኒስትሩ ጌዴዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ጋር በመሆን መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ማክሰኞ ነሐሴ 09/2015 ዓ.ም ባደረጉት ገለጻ ነው።

በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ አቶ ደመቀ፣ ለግጭቱ ሰላማዊ እልባት ለማግኘት ተጀምሯል ስለተባለው ጥረት ዝርዝር መረጃ ስለመስጠታቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያለው ነገር የለም።

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን በበኩላቸው ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ በንግግር ለማምጣት እንዲሁም ሁኔታዎችን ወደ ቀደመው መልካቸው ለመመለስ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት በሰላም መቋጨት ይቻል ዘንድ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ፣ የአገሪቱ የተለያዩ የእምነት ተቋማት እና ግለሰቦች ጥሪ እያደረጉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም በጠየቀበት መግለጫው በክልሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም የተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መንግሥታዊ መዋቅሮች መፍረሳቸውን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ከተሞች እና በከተሞች ዙሪያ ግጭቶች መከናወናቸውን አረጋግጫለሁ ያለ ሲሆን፣ በእነዚህ ግጭቶች ከባድ የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን፣ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት የንጹሃን ሕይወት መጥፋቱን፣ ንብረት መውደሙን እና ዘረፋ መፈጸሙን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ እንዲሁ ባለፈው ሳምንት አስታውቋል።

በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት መባባስ ተከትሎ በክልሉ በዋነኝነት እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች እንደ አስፈላጊነቱ ተፈጻሚ እንዲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ተደንግጓል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማ እና በዙሪያዋ በሚገኙ አካባቢዎች የጅምላ እስሮች እየተፈጸሙ እንደሆነ እና እነዚህም እስሮች አብዛኛዎቹ የሕግ ሥርዓትን ያልተከተሉ ተጠርጣሪዎችም ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ነሐሴ 08/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

በአማራ ክልል የተፈጠረውን “ግጭት ለማባባስ የከተማ ውስጥ ግዳጅ በመውሰድ የሎጅስቲክስ እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ ነበር” ያላቸውን 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መምሪያ ዕዙ ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ ይታወሳል።