ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎችም በኃይል የተያዙባቸውን የማጭበርበሪያ ማዕከላት የምያንማር ጦር ሊያጠፋ ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, BBC/ Jonathan Head
ታይላንድን ከምያንማር በሚያዋስነው የሞኢ ወንዝ ላይ የነበረው ጸጥታ በሦስት ከፍተኛ ፍንዳታዎች ተሰብሯል። የካረን ጎሣ አባላት የጀመሩትን መታጠብ እና ዋና አቋርጠው ወደ ወንዙ ዳርቻ በድንጋጤ ሸሹ። ከኋላቸው ከፍተኛ ጭስ ሲወጣ ይታያል።
ከአምስት ዓመታት ገደማ በፊት በምያንማር ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ምክንያት የተነሳው ግጭት ወደ ድንበሩ አካባቢ ደርሷል።
የአሁኑ ውጊያው ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት በካረን ግዛት ውስጥ በተስፋፉ የቻይና የወንጀል ተቋማት በሚተዳደሩ የማጭበርበሪያ ማዕከላት ጋር የተያያዘ ነው።
"የበይነ መረብ የማጭበርበሪያ እንቅስቃሴዎችን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ እየሠራን ነው" ሲሉ የምያንማር ጁንታ ቃል አቀባይ ጄኔራል ዛው ሚን ቱን ተናግረዋል።
የጦሩ ሃሳብ ላይ ጥርጣሬ ለማንሳት በቂ ምክንያቶች አሉ። የምያንማር የእርስ በርስ ጦርነት እና የማጭበርበር ቀውስ ለመጀመሪያ ጊዜ ተያይዘዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አማፂ ቡድኖች የአገሪቷን በርካታ አካባቢዎች ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ ወታደራዊው ጁንታ በአዲስ ወታደሮች እና ቻይና እና ሩሲያ ባቀረቧቸው እንደ ድሮን ባሉ አዳዲስ መሣሪያዎች ተጠናክሮ መልሶ ማጥቃት ጀምሯል።
በካረን ግዛት ለስምንት አስርት ዓመታት ሲዋጋ የቆየውን እና የመፈንቅለ መንግሥቱን ከተቃወሙት አንዱ የሆነውን የካረን ብሔራዊ ኅብረት ኃይሎችን (ኬኤንዩ) ወደኋለ እንዲሸሽ አድርጎታል።
በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ሠራዊቱ በካረን ግዛት ውስጥ ካሉ ትላልቅ እና በጣም ታዋቂ ከሆኑ የማጭበርበር ማዕከላት አንዱ የሆነውን ኬኬ ፓርክን ወረረ።
በዚህም በበይነ መረብ ሲያጭበረብሩ የነበሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ የውጭ ዜጎችን አባርረዋል። አንዳንዶቹ በፈቃደኝነት ሌሎቹ ተታለሉ ወደ ሥራው የገቡ ናቸው።
ጦሩ የሞባይል ስልኮችን፣ ኮምፒውተሮችን እና የኤለን መስክ የስታርሊንክ አገልግሎት የሚሰጡ የሳተላይት ዲሾችን ሲወርሱ የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን አውጥቷል። ሕንፃዎችንም በፈንጂዎች ማፍረስ ጀምረዋል።
ይህ አስደናቂ ለውጥ ነው። የምያንማር ወታደራዊ ገዥዎች ለዓመታት ከታይላንድ ጋር ባለው ድንበር በፍጥነት እየተስፋፋ ያለውን እና በቢሊዮን ዶላር የሚያንቀሳቅሰውን የማጭበርበሪያ ማዕከላት ችላ ብለው ቆይተዋል።
ከጦሩ ጋር የተቆራኙ የአካባቢው የጦር አበጋዞች ከቻይናዊያን የማጭበርበሪያው ኃላፊዎች ጋር የንግድ አጋር ከመሆን ባለፈ በጣም ሃብታም ሆነዋል።
የተወሰነው ገንዘብ ወደ ጄኔራሎች ካዝና ውስጥ ገብቷል። ጁንታው ኬኤንዩን ለማጭበርበሮቹ ተጠያቂ ለማድረግ ሞክሯል። ከሌሎች የታጠቁ የካረን ቡድኖች በተለየ ኬኤንዩ ራሱን ከአጭበርባሪዎቹ ሲያርቅ ቆይቷል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በፍቅር ስም፣ በፍጥነት ሀብታም ለመሆን በሚደርጉ የክሪፕቶ ዕቅዶች እና በሐሰተኛ የገንዘብ ማግኛ ማጭበርበሪያዎች ላይ ሲፈስ ቆይቷል።
ኢንዱስትሪው ከሰዎች ዝውውር፣ ከሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ከሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር ይገናኛል።
ይህንን ለመዋጋት ዓለም አቀፍ ቅንጅት እየጨመረ መጥቷል። አሜሪካ ፀረ-ማጭበርበር ግብረ ኃይል አቋቁማለች። ከምያንማር ወታደራዊ ጁንታ የቅርብ አጋሮች አንዷ የሆነችው ቻይና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿ ላይ ማጭበርበር በመፈጸሙ እና የሕገ ወይ የሰዎች ዝውውር ሰለባ በመሆናቸው ጉዳዩን አጥብቃ ይዛዋለች።
ጦሩ በኬኬ ፓርክ ውስጥ መገኘቱ የተፈጠረው ጫና እየሠራ ያለ አስመስሏል።
በኬኬ ፓርክ ውስጥ የተፈጸመው ውድመት የማጭበርበሪያ መሠረተ ልማቶችን ያወደመ አይመስልም።
የጦሩ እንቅስቃሴዎች በዚህ ግቢ ላይ ብቻ ያተኮሩ ቢሆኑም በደርዘን የሚቆጠሩ ሌሎች ማዕከላት አሉ። የሽዌ ኮኮን የማጭበርበሪያ ከተማን ቢወርም ጥቂት ሕንጻዎች ውስጥ ብቻ ገብቶ አንዱን ብቻ አፍርሷል።

የፎቶው ባለመብት, BBC/ Jonathan Head
በሺህዎች የሚቆጠሩ የውጭ አገር ሠራተኞች ኬኬ ፓርክን እና ሽዌ ኮኮን ለቀው በሞኢ ወንዝ አቋርጠው ወደ ታይላንድ ተጉዘዋል።
ትራንስፖርት ማግኘት አስቸጋሪ እና ውድ ቢሆንም ሌሎች ደግሞ ወደተለያዩ ቦታዎች ተበታትነዋል። የመኪና ትራንስፖርት ዋጋ 700 ዶላር ገደማ ደርሷል። ዋናዎቹ አጭበርባሪዎች ማዕከሎቻቸውን ወደ ደቡብ የምያንማር ግዛቶች እንደወሰዱ ይገመታል።
ባለፈው ወር ሚንሌትፓን በተባለች ከተማ አንድ የማጭበርበሪያ ቡድን ሹንዳ እና ባኦሊ በሚባሉ ሁለት ግቢዎች ውስጥ ተይዟል።
እነዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት በወንዙ አጠገብ ከተገነቡት መካከል ናቸው። ከወታደራዊው ጁንታ ጋር ከተዋሃደው ሚሊሻዎች አንዱ በሆነው በዲኬቢኤ ቁጥጥር ሥር ያለ አካባቢ ውስጥ ይገኛሉ።
የኬኤንዩ ቃል አቀባይ እንደገለጹት፣ ተዋጊዎቻቸው ከሠራዊቱ ጋር ጦርነት ውስጥ በገቡበት ወቅት በዲኬቢኤ አባላት ተኩስ ተከፍቶባቸው ነበር።
የዲኬቢኤ አባላትን ሲያፈገፍጉ ሁለቱን የማጭበርበሪያ ማዕከላት እና እዚያ የሚሠሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ የውጭ ዜጎችን ተቆጣጠሩ።
ኬኤንዩ ጋዜጠኞች እና ዓለም አቀፍ የሕግ አስከባሪ ተቋማት በቁጥጥር ሥር የዋሉትን ማዕከላት እንዲያዩ በመጋበዝ ምሳሌ መሆን እንደሚፈልግ አስታውቋል።
ጦሩ በኬኬ ፓርክ እንዳደረገው ማስረጃውን ከማጥፋት ይልቅ ማጭበርበሪያው እንዴት እንደሚሠራ ለማጋለጥ ፎቶግራፎችን እና ሰነዶችን ይፋ አድርጓል።
በወንዙ በኩል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ወደ ታይላንድ ቢልክም ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ የቻይና ዜጎች ለመሄድ ፈቃደኛ አልሆኑም ተብሏል። ወደ ቻይና ቢመለሱ እንደሚከሰሱ ስለፈሩ ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል።

የፎቶው ባለመብት, BBC/ Jonathan Head
ይህ ሁሉ ድራማ በአንድ ነገር ላይ የተመሠረተ ነው። ጁንታው ከፍተኛ ትችት የተሰነዘረበትን ምርጫ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ለማካሄድ ዕቅድ አለው።
በመፈንቅለ መንግሥቱ የተነሳው የእርስ በርስ ጦርነት አገሪቱን እያወደመ ነው። ወታደራዊው አገዛዝ በአብዛኛዎቹ የምያንማር ዜጎች የተጠላ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነት የለውም።
ጄኔራሎቹ ሕጋዊነት የሚያስገኝላቸው እና ከብዙ ተቃዋሚዎቻቸው መካከል አንዳንዶቹን የሚያሸንፍላቸውን አማራጭ እየፈለጉ ነው።
ምርጫ ቢያስቡም ዋና ዋና የተቃዋሚ ቡድኖች ሊሳተፉበት ወይም ላይሳተፉበት የሚችል ከመሆኑም ባለፈ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ድምጽ ለመስጠት በሚያስችል ሰላም ውስጥ አይገኝም።
በዚህ ምክንያት ወታደራዊ ኃይሉ ከምርጫው በፊት ከአማፂያን እጅ በርካታ ቦታዎችን ማስለቀቅን ቅድሚያ ሰጥቶታል።
በማጭበርበሪያ ማዕከላት ላይ በሚያደርገው ከፍተኛ ጥቃት ምክንያት ስሙን ለመገንባት እየሞከረ ነው። አጋር የሆነችው ቻይና ደግሞ ይህንን በይበልጥ ትፈልገዋልች።
ተጨማሪ ሕንፃዎች ኬኬ ፓርክ ሲፈርሱ ታይተዋል። እዚያ ካሉት ትላልቅ ሕንፃዎች መካከል አንዳንዶቹ ተቆልፈው መስኮቶቻቸው ተሰባብረዋል፤ የሌሎች ግድግዳዎች በቆፋሪዎች እየፈረሱ ነበር።
ነገር ግን በርቀት ብዙ ሕንፃዎች አሁንም ሳይበላሹ ቀርተዋል። አንዳንዶቹ በጣሪያቸው ላይ የስታርሊንክ ሳተላይት ዲሽ የተገጠመላቸው ናቸው። ይህም አንዳንድ የማጭበርበር ሥራዎች አሁን እየተከናወኑ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል።
በበርማ እና በታይላንድ መካከል የምትገኘው ዋውላይ የይገባኛል ጥያቄ ይነሳባታል። ኬኤንዩ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በርካታ ወታደራዊ ማዕከሎችን ይዟል። መሻገሪያው ግን በዲኬቢኤ ቁጥጥር ሥር ነው።
በታይላንድ በኩል ሰዎች በማጭበርበሪያ ማዕከላት እንዳይታለሉ የሚገልጽ ትልልቅ ማስታወቂያ ይታያል።
ከጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ በወንዙ አጠገብ በግንብ እና በኤሌክትሪክ የሽቦ አጥር የተከበበ ግቢ ተገንብቷል። ሄንግሼንግ 3 በመባል የሚታወቅ ሲሆን የጀነሬተሮች እና የጠባቂዎችን ድምጽ መስማት የተለመደ ነው።
መስኮቶቹ የብረት ፍርግርግ ያላቸው፤ ጣሪያቸው ላይ የስታርሊንክ ዲሾች የተገጡመላቸው ናቸው። የክትትል ቡድኖች ይህንን እና ሌሎች በርካታ አዳዲስ ማዕከላትን በዋውላይ ዙሪያ ለይተዋል። በርካታ ቡድኖች ወደ ደቡብ ፓያቶንዙ ተንቀሳቅሰዋል።
እንደ ኬኬ ፓርክ እና ሽዌ ኮኮ ያሉ ታዋቂ የማጭበርበሪያ ማዕከላት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምንም ይሁን ምን የማጭበርበሪያ ማዕከላቱ ግን አሁንም በምያንማር እየተስፋፉ ነው።















