የፌስቡክ ባለቤት የሆነው ሜታ ክፍለ ዓለማትን የሚያዳርስ የኢንተርኔት ገመድ ሊዘረጋ ነው

ሜታ 50 ሺህ ኮሎ ሜትር የሚረዝም የኢንተርኔት ገመድ ከውቅያኖስ በታች ሊዘረጋ መሆኑን አስታወቀ።

ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ፕሮጀክት ዋተርዎርዝ ሲል የጠራው የኢንተርኔት ገመድ ዝርጋታ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሕንድ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ብራዚልን እንዲሁም ሌሎች ሀገራትን የሚያገናኝ ነው።

ዝርጋታው ሲጠናቀቅ በዓለማችን ረዥሙ የኢንተርኔት ገመድ ይሆናል።

የፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ ባለቤት የሆነው ሜታ በቴክኖሎጂው ዓለም ያለውን ተፅዕኖ ከማኅበራዊ ሚድያው በላይ እንዲሆን ይሻል።

ድርጅቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ዘርፍ ግንባት ቀደም ለመሆን እየሠራ እንዳለ ተነግሯል።

ኩባንያው እንዳለው አዲሱ የኢንተርኔት ገመድ ዝርጋታ አምስት አህጉራትን የሚያገናኝ እና የኤአይ መሠረተ-ልማትን የሚደግፍ ነው።

"ይህ ፕሮጀክንት ታላቅ የምጣኔ ሀብት ትስስር ይፈጥራል፣ የዲጂታል አካትችነትን ያፋጥናል፤ በተጨማሪም በእነዚህ ክልሎች የቴክኖሎጂ ዕድገት እንዲፋጠን ምክንያት ይሆናል" ሲሉ ኩባንያው በመግለጫው ጠቅሷል።

የሚዘረጋው ገመድ 24 ፋይበር-ፔይር የተባለ ሲሆን ለፈጣን ኢንተርኔት ጥቅም ላይ የሚውል ነው።

በውቅያኖስ ግርጌ የሚዘረጉ የኢንተርኔት ገመዶች ዳታ በክፍለ ዓለማት መካከል በፍጥነት እንዲዘዋወር ትልቅ ጥቅም አላቸው።

አንድ መረጃ እንደሚጠቁመው 95 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን የኢንተርኔት ዝውውር የሚከናወነው ከውቅያኖስ ሥር በሚገኙ ገመዶች አማካይነት ነው።

ቴሌጄኦግራፊ የተባለው የቴሌኮሚዩኒኬሽን ጥናት ተቋም እንደሚለው በአሁኑ ወቅት 600 የሚሆኑ የኢንተርኔት ገመዶች ከውቅያኖስ ሥር ይገኛሉ።

ከእነዚህ መካከል በሜታ የሚደገፈው እና ኦሬንጅ፣ ቮዳፎን እና ቻይና ሞባይል የተባሉትን የኔትዎርክ አቅራቢዎች የሚያገናኘው 2አፍሪካ የተባለው ገመድ ይገኝበታል። ይህ ገመድ 45 ሺህ ኪሎ ሜትር ይረዝማል።

ጉግል በአውሮፓውያኑ 2024 ባወጣው መግለጫ አፍሪካ እና አውስትራሊያን የሚያገናኝ እና 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ገመድ በፓሲፊክ ውቅያኖስ ሥር እንደሚዘረጋ ማስታወቁ ይታወሳል።

በውቅኖሶች ሥር የሚዘረጉ ገመዶች ጥቃት ይደርስባቸዋል አሊያም ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው የሚል ስጋት አለ።

ሜታ በመግለጫው ገመዱን የሚቀብረው 7 ሺህ ሜትር ጥቅል በሆነ ሥፍራ መሆኑን አስታውቆ ይህን የሚያደርገው አደጋ እንዳይደርስባቸው ለማድረግ መሆኑን ጠቅሷል።