ማር ሳይበላሽ ለረዥም ጊዜ የሚቆይበት ምክንያት ምንድን ነው? ምንስ ያበላሸዋል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማር ተፈጥሯዊ ማጣፈጫ ነው። ባክቴሪያዎች ደግሞ ጣፋጭ ነገር ይወዳሉ። ማር ግን ብልሽትን ተቋቁሞ ለረዥም ጊዜ ይቆያል። ማር ባክቴሪያዎችን ተቋቁሞ ለረዥም ጊዜ የመቆየት ምሥጢሩ ምንድን ነው?
በጠርሙስ ታሽገው የሚቀመጡ ጣፋጮች የቆይታ ጊዜ ይኖራቸዋል። ነገር ግን ለመበላሸት፣ ለመሻገት፣ ጠረን ለመቀየር የሚያስፈልጋቸው ጥቂት ነገር ብቻ ነው።
አንዳንድ ምግቦች አሉ ለረዥም ጊዜ ያለምንም እንከን ቆይተው ለምግብነት መዋል የሚችሉ።
ማር ከእነዚህም የምግብ ዓይነቶች መካከል አንዱ ነው። በጠርሙስ ወይንም ፕላስቲክ ውስጥ ታሽጎ ተቀምጦ እንኳ ወርቃማው ፈሳሽ ይጠጥር፣ይወፍር ይሆናል እንጂ መበላሸት የሚባል ነገር በአጠገቡም አያልፍም።
ማር ሳይበሰብስ፣ ሳይሻግት እና ጠረኑን ሳይለውጥ የመቀየቱ ምሥጢር የተመረተበት መንገድ እና በውስጡ የያዘው ንጥረ ነገር ነው።
ምግብ ተበላሸ ስንል ምን ማለታችን ነው?
ምግብ ተበላሸ ሲባል በዓይን ለማየት አስቸጋሪ የሆኑ ባክቴሪያ፣ ፈንገስ እና ሻጋታዎች በትንሽ መጠንም ቢሆን ገብተውበታል ማለታችን ነው።
አብዛኞቹ እነዚህ ረቂቅ ተሕዋስያን ለምግብ ልመት (ሜታቦሊዝም) እርጥበትን፣ ከፍ ያለ (ነገር ግን በጣም ከፍተኛ ያልሆነ) የሙቀት መጠን፣ መለስተኛ የአሲስ መጠን (ፒኤች) እና ብዙ ኦክስጅንን ይፈልጋሉ።
ሥጋ ወይም ፍራፍሬ ማድረቅ ባክቴሪያዎች ውሃ እንዳያገኙ ይከለክላቸዋል።
ምግብን በከፍተኛ ሙቀት ማብሰል እና ከዚያም ወደ ማቀዝቀዣው ውስጥ ማስገባት በመጀመሪያ ብዙ ተሕዋሲያንን ይገድላል። የቀሩም ካሉ ዕድገታቸውን በማዘግየት እንቅፋት ይፈጥራል።
በእቃ ውስጥ አሽጎ ማስቀመጥ ደግሞ ኦክስጅን እንዳያገኙ ይገድባል።
ምግብ ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ በጨው፣ በቅመማ ቅመም እና በአቼቶ ታሽተው ሲቀመጡ አሲዳማ እንዲሆኑ ስለሚያደርግ ባክቴርያዎችን፣ ሻጋታዎችን እና ሌሎች ጎጂ ፍጥረታትን ያስወግዳል።
የሰው ልጅ በዓይን ከማይታዩ ፍጥረታት ጋር የሚያደርገው ትግል ሁልጊዜም በተሸናፊነት የሚጠናቀቅ ነው።
በአብዛኛው የምግቦችን ደኅንንት ጠብቆ ለረዥም ጊዜ ለማቆየት የሚያደርገው ጥረት ቀስ ብለው ሰርገው በሚገቡ ባክቴሪያዎች ወይም ሻጋታዎች ይሸነፋል።
ማር ግን ከዚህ ሁሉ የተለየ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ንቦች ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር ከአበቦች ላይ ፈሳሽ የአበባ ወለላን ቱቦ በመሰለው ምላሳቸው እየቀሰሙ በሆዳቸው ውስጥ ባለ የማር ቋት ውስጥ ያጠራቅማሉ።
ከዚያም ተሸክመው ወደ ቀፏቸው ይወስዱታል። ቀጥሎም ፈሳሽ የአበባ ወለላውን ወደ ሌሎች ንቦች ያዘዋውሩታል።
ወለላውን የተቀበሉት ንቦች በአፋቸው ውስጥ ካሉት ዕጢዎች ከሚመነጭ ኢንዛይም ጋር እያዋሃዱ ለአንድ ሰዓት ከግማሽ ያህል "ያላምጡታል"።
ከዚያም ከሰም በተሠሩ ባለ ስድስት ማዕዘን ክፍሎች ውስጥ ያስቀምጡትና እርጥበቱ እንዲተን በክንፎቻቸው ያራግቡታል።
የውሃው መጠን ከ18 በመቶ በታች ሲሆን፣ ክፍሎቹን በሰም በስሱ ይሸፍኗቸዋል።
በዚህ መልኩ የተሸፈነ ማር ሳይበላሽ ለዘመናት ሊቆይ ይችላል።
ይህም ብቻ አይደለም በማር ውስጥ ብዙ ስኳር አለ። በእርግጥ ረቂቅ ተሕዋስያን ወደዚያ መሄድ እና መራባት ይወዳሉ።
ነገር ግን ንቦቹ ማርን በሚሠሩበት ወቅት የሚጠቀሙት በጣም ትንሽ ውሃ እና አሲዳማነት ባክቴሪያዎች እንዳይራቡ እና እንዳይበላሽ ያደርገዋል።

የፎቶው ባለመብት, Alamy
ንቦች በአበባ ፈሳሹ ላይ ኢንዛይም ስለሚጨምሩበት ማር ለስለስ ያለ የፀረ ባክቴሪያነት እና አንቲባዮቲክነት ባሕርይ እንዳለው ጥናቶች ይጠቁማሉ።
ይህ ኢንዛይም ጎጂ ባክቴሪያዎችን የሚገድል ሃይድሮጅን ፐርኦክሳይድ እንዲፈጠር ያደርጋል።
ንጹህ የተፈጥሮ ማር በውስጡ አሚኖ አሲድ፣ አንታይኦክሲደንት፣ ቫይታሚኖች፣ ሚኒራሎች እና ስኳር ይዟል።
ከቀፎ የተቆረጠ ማርን በእቃ ውስጥ አሽጎ ማስቀመጥ የኦክስጅንን አቅርቦት በመገደብ ባክቴርያ እንዳይራባ ያደርግልናል።
ይህ በምግብ ሳይንቲስቶች መካከል "ዝቅተኛ የውሃ እንቅስቃሴ" በመባል ይታወቃል። የአንድን ንጥረ ነገር የውሃ እንቅስቃሴ ዝቅ ማድረግ የተመረቱ ምግቦችን ለማቆየት የተለመደ ዘዴ ነው።
የውሃ ሞሎኪውሎች ከጨው ወይም ከስኳር ጋር በሚገናኙበት ጊዜ እርጥበት ያለው ምግብ እንዳይበላሽ ማድረግ ይቻላል።
ይህ ማለት ማር ሁሉንም አዲስ የተቆረጠ ሆኖ የመቆየት ፈተናዎችን ይቋቋማል ማለት አይደለም። አንድ በእቃ ውስጥ ያለ ማር ከተከፈተ በኋላ በየጊዜው ለአየር ይጋለጣል።
እናም እርጥብ ማንኪያዎችን ወደ ውስጥ ማስገባት እቃው በመጀመሪያ ሲታሸግ ያልነበሩ ባክቴሪያዎችን እና እርጥበትን ያመጣል።
ስለዚህም ማርን በእርጥብ ማንኪም ሆነ በሌላ ነገር ከተቀመጠበት ለማውጣት መሞከር ለመበላሸት እንዲጋለጥ ያደርገዋል።















