በስመ ጥር ሩስያዊያን ላይ ያነጣጠረው የዩክሬን ሰላዮች ጥቃት

ዘመቻው ሰፊ እና አስገራሚ ነበር።

ፈንጂዎች በኤሌክትሪክ ሳይክል መሳይ (ስኩተር) ውስጥ ተደብቀው ከርቀት ባሉ ተቆጣጣሪዎች መፈንዳታቸውን የዩክሬን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሌተናል ጄኔራል ኢጎር ኪሪሎቭ ዩክሬን ከተወረረች ወዲህ ከጦር ሜዳ ውጭ የተገደሉ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣን እንደሆኑ ይታመናል።

ግድያው የሩስያን ወታደራዊ እና የፖለቲካ ተቋማትን አስደንግጧል። የዩክሬን የስለላ ተቋም ኤስቢዩ ምንጮች ተቋሙ ከግድያው ጀርባ እንደነበር አስታውቀዋል።

በዩክሬን ግዛት በሩስያ ወታደሮች ላይ ያነጣጠሩ በርካታ የዩክሬን ዘመቻዎች ነበሩ።

የዩክሬን የስለላ ተቋም የኒውክለር፣ ባዮሎጂካል እና ኬሚካል መከላከያ ኃይል ኃላፊን በደቡብ ምስራቅ ሞስኮ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ ዒላማ ማድረግ መቻሉ ስለ ሩስያ ደህንነት ጥያቄ ሲያስነሳ የዩክሬን አቅም ምን ያህል የጠነከረ እንደሆነ ያሳያል።

ለጥቃቱ የኤሌክትሪክ ስኩተር መምረጥ ብልሃት የተሞላበት እርምጃ ነበር። በሞስኮ ጎዳናዎች ላይ እንደልብ ስለሚገኙ ትኩረት አይስቡም።

መሳሪያው በትክክለኛው ጊዜ ፈንድቷል። ጄነራል ኪሪሎቭ ከረዳታቸው ጋር ሆነው ከመኖሪያ ቤታቸው ሲወጡ ጥቃት አድራሾቹ ፈንጂውን ለማፈንዳት በካሜራ ወይም በአካል በስፍራው ሆነው መመልከት ይጠበቅባቸው ነበር።

የጄነራሉ ግድያ ኤስቢዩ በሩሲያ ትላልቅ ከተሞች የፈጸመው የመጀመሪያው ጥቃት እንዳልሆነ ይታሰባል። ቀደም ሲል በሩስያ በፖለቲከኞች እና በወታደራዊ ባለስልጣናት ላይ ይሰነዘር የነበረው ጥቃት እንደዚህ አይነት ድርጊቶች እንዴት እንደተፈፀሙ የተወሰነ ፍንጭ ሊሰጥ ይችላል።

እአአ ሚያዝያ 2023 "የፈጠራ ምሽት" በሚል ታዋቂው የጦርነት ጦማሪ ቭላድለን ታታርስኪ በሴንት ፒተርስበርግ ካፌ ውስጥ ከደጋፊዎች ጋር ቀጠሮ ነበረው።

ዝግጅቱ ስትሪት ፉድ ባር ነምበር 1 ነበር የተሰናዳው። የሥነ ጥበብ ተማሪ ያለችው ዳርያ ትሬፖቫ የአንድ ወታደር ጭንቅላትን የተቀረጸ ምስል በስጦታ አበረከተለት። ታታርስኪ ስጦታውን ወደ ካርቶኑ ሲያስገባ ፈንድቶ ገደለው። ታዳሚዎችም ጉዳት ደረሰባቸው።

ትሬፖቫ በፍርድ ቤት በሰጠችው ቃል ስጦታው ፈንጂ እንዳለው እንደማታውቅ ተናገረች። በዩክሬን የሚካሄደውን ጦርነት እንደምትቃወመው አምና፣ በስጦታው ውስጥ ማይክሮፎን እንዳለ ብቻ እንደተነገራት ገለጸች።

ፍርድ ቤቱ የ27 ዓመት እስራት ፈርዶባታል።

እሷ አስቀድማ የምታውቀው ምንም ይሁን ምን፤ የዩክሬን የደህንነት ተቋም ስለዩክሬን ርህራሄ ያላቸውን ሩሲያውያን እንደሚጠቀም ምንም ጥርጥር የለውም።

ይህም ዝግጅቶችን ከማጨናገፍ እስከ ቦምብ ጥቃት ሊደርስ ይችላል።

ኤስቢዩ ግቡን ለማሳካት ብዙ የስለላ ተቋማት እንደሚያደርጉት የአልሞ ተኳሽ ከመላክም አይቆጠብም።

ከአንድ ዓመት በፊት የሩስያ ደጋፊ የነበረው የቀድሞ የዩክሬን የፓርላማ አባል ኢሊያ ኪቫ ከሞስኮ ወጣ ብሎ በሚገኝ መንደር በጥይት ተመትቶ ተገድሏል። ገዳዩ ሳይታወቅ ሆቴሉ ግቢ ውስጥ ገብቶ ኪቫን በሆቴሉ ሜዳ ሲዝናና ሁለት ጊዜ ተኩሶ መቶታል።

ዩክሬን ምንም አይነት ኦፊሴላዊ መግለጫ ባትሰጥም የኤስቢዩ ምንጮች እነሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከአምስት ቀናት በፊት ደግሞ ታዋቂው የሩሲያ የሚሳዔል ሳይንቲስት ሚካሂል ሻትስኪ ከሞስኮ ወጣ ብሎ በሚገኝ ጫካ ውስጥ በጥይት ተገድሏል። ምንም ማረጋገጫ ባይኖርም ግድያውን የዩክሬን ወታደራዊ መረጃ አገልግሎት ፈጽሟል ተብሏል።

ሻትስኪ በዩክሬን ብዙ ውድመት እና የህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑትን የሩሲያን ኬኤች-59 እና ኬኤች-69 ክሩዝ ሚሳዔሎችን የማዘመን ኃላፊነት ነበረው።

የኪሪሎቭ ግድያ በተፈጸመ በጥቂት ቀናት ልዩነት በሻትስኪ መገደሉ የዩክሬን ሰላዮች ምን ያህል ወደ ሩስያ ዘልቀው እንደገቡ ያሳያል።

ከጦር ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ፖለቲከኞች ወይም ሩስያውያን ብቻ አይደሉም ጥቃት የደረሰባቸው።

እአአ ነሐሴ 2022 ዳርያ ዱጊና በመኪና የቦምብ ጥቃት ተገድላለች። ሞስኮ በዩክሬን የምታደርገውን ወረራ በመደገፍ ለሚታወቀው ለአባቷ ለአሌክሳንደር ዱጊን የተላለፈ ግልጽ መልዕክት ነበር።

እንደ የሩስያ መርማሪዎች ከሆነ በጥቃቱ ውስጥ ሁለት የዩክሬን ዜጎች ተሳትፈዋል። ይህም ዩክሬን ዒላማዋን "ለማስወገድ" ወደ ሩስያ ሰላዮቿን እንምትልክ ማሳያ ነው ።

የ43 ዓመቷ ናታሊያ ቮቭክ በምስራቃዊ ዩክሬን ከምትገኘው እና በሞስኮ ቁጥጥር ስር ከምትገኘው ከዶኔትስክ ሩሲያ ተሻግራ ነበር።

በኋላም ቦምቡን የገጣጠሙበትን ቤት ከተከራየ ሌላ ዩክሬናዊ ጋር ተገናኘች። በችሎቱ ወቅት እንደተገለጸው ከሆነ ሁለቱም ዩክሬናውያን ዱጊና ከመገደሏ ከአንድ ቀን በፊት ከሩሲያ ለማምለጥ ችለዋል።

እነዚህ ሁሉ ጥቃቶች የዩክሬን የስልላ ተቋም ያሉትን ሰፊ ዘዴዎች ያሳያሉ። አንዳንድ ባለሙያዎች ግን ሌተናል ጄኔራል ኪሪሎቭን የገደለችው ኪዬቭ ላትሆን ትችላለች ብለው ያምናሉ።

መቀመጫቸውን በኪዬቭ ያደረጉት ወታደራዊ ተንታኝ ዩሪ ካሪን እንዳሉት ከሆነ ይህ በሩስያ ጦር ውስጥ ካለ የስልጣን ሽኩቻ ወይም ክሬምሊን የጦር ወንጀሎች ዋና ምስክሮችን ለማስወገድ ያደረገችው ሙከራ ሊሆን ይችላል።

ኤስቢዩ ከሆነ "በሞስኮ ቀለበት መንገድ ላይ እንኳን የሩሲያ ጄኔራሎች ደህንነት ሊሰማቸው አይችልም" የሚል ግልጽ መልዕክት የሚያስተላለፍ ነው ብለዋል።