ቻይና በአደንዛዥ ዕጽ ወንጀል አራት ካናዳውያንን በሞት ቀጣች

ቻይና በአደንዛዥ ዕጽ ወንጀል አራት ካናዳውያንን በሞት መቅጣቷን የካናዳ ባለስልጣናት አረጋገጡ።

የተገደሉት ሁሉም ግለሰቦች ጥምር ዜግነት ያላቸው ሲሆን ማንነታቸውም ይፋ እንዳልተደረገ የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜላኒ ጆሊ ተናግረዋል።

በካናዳ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ካናዳ "ኃላፊነት የጎደላቸው አስተያየቶችን ከመስጠት እንድትታቀብ" አሳስበዋል።

ለዓመታት ግንኙነታቸው ሻክሮ የነበረው ሁለቱ አገራት የበለጠ ውጥረት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ብለዋል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ "በህጉ መሰረት" እርምጃ መወሰዱን የገለጸ ሲሆን፤ ኤምባሲው በበኩሉ ለወንጀላቸው "ጠንካራ እና በቂ" ማስረጃ አለ ብሏል።

ኤምባሲው አክሎም ካናዳ "የቻይናን የፍትህ ሉዓላዊነት" እንድታከብር አሳስቧል።

ቻይና የጥምር ዜግንትን ጽንሰ ሃሳብ የማትቀበል ሲሆን በአደንዛዥ ዕጽ ወንጀሎች የተከሰሱ ሰዎችን በከባዱ ትቀጣለች።

ሆኖም የውጭ አገር ዜጎችን በሞት መቅጣት ለቻይናም ቢሆን የተለመደ አይደለም።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ የግለሰቦቹን ክስ ለወራት በቅርብ ሲከታተሉት እንደነበር እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት ጋር በመሆን የሞት ቅጣቱን ለማስቆም መሞከራቸውን ገልጸዋል።

"እነዚህ ግለሰቦች ምህረት እንዲደረግላቸው ከፍተኛ ባለስልጣናት ጭምር በተደጋጋሚ ጠይቀዋል። በማንኛውም ክስ የሞት ቅጣት ተፈጻሚ እንዳይሆን መወትወቷን ካናዳ ትቀጥላለች" ሲሉ ግሎባል አፌይርስ ቃል አቀባይ ሻርሎት ማክሊየድ ለካናዳ ሚዲያ በሰጡት መግለጫ አትተዋል።

ቻይና ከባድ የምትላቸውን ወንጀሎች እንደ አደንዛዥ ዕጽ፣ ሙስና እና ስለላን በሞት ትቀጣለች።

የሞት ቅጣት በሚስጥር የሚያዝ ቢሆንም፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ቻይና በዓለም ላይ ከፍተኛ የሞት ፍርድ ከሚፈጸምባቸው አገሮች አንዷ ናት ብለው ያምናሉ።

"በካናዳ ዜጎች ላይ የቻይና ባለስልጣናት የፈጸሙት ኢ-ሰብዓዊ የሞት ቅጣት ለካናዳ የማንቂያ ደወል ሊሆን ይገባል" ሲሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ካናዳ ኬቲ ኒቪያባንዲ ተችተዋል።

"ለተጎጂ ቤተሰቦች ጥልቅ ሃዘን ተሰምቶናል። እናም በዚህ በማይታሰብ ሁኔታ ሃዘን ላይ የወደቁ ቤተሰቦች ልባችን ከናንተ ጋር ነው" ብለዋል።

አክለውም "በቻይና የሞት ቅጣት ተፈጻሚ ሊሆንባቸው ያሉ የካናዳ ዜጎች እንዲሁም በእስር ቤት ውስጥ የት እንደደረሱ ለማይታወቁ ሃሳባችን ከናንተ ጋር ነው" ሲሉም አትተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2019 የካናዳ ዜግነት ያለው ሮበርት ሎይድ ሼለንበርግ በቻይና በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ወንጀል የሞት ፍርድ ተፈርዶበታል።

የካናዳ መንግሥት ይህንን ያወገዘ ሲሆን ጉዳዪም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት የሞት ቅጣት ተፈጻሚ ከሆነባቸው ካናዳውያን መካከል አልተካተተም።

"በጠንካራ ማውገዛችንን ከመቀጠላችን በተጨማሪ በተመሳሳይ ሁኔታ ላሉ ካናዳውያን ምህረትን እንጠይቃለን" ብለዋል ጆሊ።

ካናዳ የቻይናን የቴሌኮም ስራ አስፈጻሚ ሜንግ ዋንዙን በአሜሪካ አሳልፋችሁ ስጡኝ ጥያቄ በአውሮፓውያኑ 2018 መያዟን ተከትሎ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ሻክሯል።

ቻይና ብዙም ሳይቆይ ሁለት ካናዳውያንን በቁጥጥር ስር ያዋለች ሲሆን አሁን ሁለቱም ተለቀዋል።