ትራምፕ እና የደኅንነት ተቋማት ኃላፊዎቻቸው ምስጢራዊ መረጃ በሲግናል ተልኳል መባሉን አጣጣሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የደኅንነት ተቋማት ኃላፊዎቻቸው ሲግናል በተባለው የመልዕክት መላላኪያ አማካይነት ምስጢራዊ መረጃ ተልኳል መባሉን አጣጥለዋል።
አንድ ጋዜጠኛ የደኅንነት ኃላፊዎች የሚነጋገሩበት ቡድን ውስጥ መግባቱ የደኅንነት ስጋት እንዳልሆነ ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
ዘ አትላንቲክ የተባለው መፅሔት ዋና አርታኢ የአሜሪካ ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣናት የሚነጋገሩበት የሲግናል ግሩፕ ውስጥ ገብቶ መረጃ መስማቱን ተከትሎ የትራምፕ አስተዳደር ትችት እየቀረበበት ይገኛል።
የደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊዎቹ በዚህ የሲግናል 'ግሩፕ' አማካይነት የየመን ሁቲ አማፂያን ላይ ስለሚደረግ ጥቃት ሲነጋገሩ ጋዜጠኛው ተመልክቷል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ ቱልሲ ጋባርድ እና የሲአይኤ ኃላፊ ጆን ራትክሊፍ በሴኔት ፊት ቀርበው በሰጡት ቃል ምንም ዓይነት ምስጢራዊ መረጃ አልተጋራም ሲሉ አስተባብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒተር ሄግሴዝ በጉዳዩ ምክንያት በርካታ ወቀሳ ቢቀርብባቸውም በሴኔት ፊት ቀርበው ቃል አልሰጡም።
የሴኔት አባል የሆኑ ዲሞክራቶች ባለሥልጣናቱ ብሔራዊ ደኅንነት ለማስከበር "ብቁ ያልሆኑ" ሲሉ ባለሥልጣናቱን ወርፈዋል።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለመረጃው መሹለክ ምክንያት ናቸው የተባሉትን የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክ ዋልትዝን ደግፈው አስተያየት ሰጥተዋል።
እንዴት የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የትኛውም ሰው የሚጠቀምበትን የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያ ተጠቅመው ምስጢራዊ የሆነ መረጃ ይላላካሉ የሚለው አሜሪካዊያንን እያነጋገረ ይገኛል።
የአትላንቲክ መፅሔት ዋና አርታኢ ጄፍሪ ጎልድበርግ 18 ሰዎች ያሉበትን የሲግናል ግሩፕ ውስጥ የተካተተው በስኅተት ሲሆን መጀመሪያ አጭበርባሪዎች ናቸው ብሎ ማሰቡን በፅሑፉ ያትታል።
ነገር ግን በየመን ላይ ጥቃት በተደረገ ወቅት ነው የተካተተበት የሲግናል ግሩፕ እውነተኛ መሆኑን ያረጋገጠው።
አሜሪካ ከሁለት ሳምንታት በፊት በየመን በፈፀመችው ጥቃት 53 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን አሜሪካ ጥቃቱ ዒላማ ያደረገው በኢራን የሚደገፉ የሁቲ ታጣቂዎችን ነው ብላለች።
ከራትክሊፍ እና ጋባርድ በተጨማሪ ምክትል ፕሬዝደንቱ ጄዲ ቫንስ እና የዋይት ሐውስ ኃላፊ ሱዚ ዋይልስም በዚህ የሲግናል ግሩፕ ውስጥ ተካተው ነበር።
ማክሰኞ ዕለት የተሰየመው ሴኔት ፊት ቀርበው ምላሽ የሰጡት ጋባርድ እና ራትክሊፍ ድርጊታቸውን አስተባብለዋል። ጉዳዩ ትልቅ ስኅተት ነው ብለው ያስባሉ ተብለው የተጠየቁት ራትክሊፍ "አላስብም" ሲሉ መልሰዋል።
ጋባርድ በበኩላቸው "ምንም ዓይነት ምስጢራዊ መረጃ አልተጋራም" ሲሉ በተደጋጋሚ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጋዜጠኛው በፅሑፍ አብዛኛው ምስጢራዊ የሚባለው መረጃ ይላክ የነበረው ከመከላከያ ሚኒስትሩ ፒተር ሄግሴዝ እንደሆነ ፅፏል።
በተለይ ዲሞክራት የሴኔት አባላት ሁለቱን ባለሥልጣናት አፋጠው ሲይዙ ተስተውለዋል። የኮሎራዶው ማይክል ቤኔት በጉዳዩ የተሳተፉ ዝርክርክ እና ብቁ ያልሆኑ እንዲሁም ለአሜሪካ ደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ክብር የሌላቸው ናቸው ሲሉ ወርፈዋል።
ዲሞክራቶች ብቻ ሳይሆኑ ሪፐብሊካን የሴኔቱ አባላትም በሁኔታው ደስተኛ አለመሆናቸውን ገልፀው ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ትራምፕ እና የዋይት ሐውስ ቡድናቸው የሰሞኑ ውዝግብ እሳቸው ያሳኩት ነገር እንዳይነገር የተደረገ "የተቀናጀ እንቅስቃሴ" ነው ብለዋል።
"ዋልትዝ ትምህርት ቀስሞበታል። እሱ መልካም ሰው ነው" ሲሉ አማካሪያቸውን ያደነቁት ትራምፕ ጋዜጠኛው የባለሥጣናቱ የሲግናል ግሩፕ ውስጥ መካተቱ "ምንም ተፅዕኖ የለውም" ሲሉ ተደምጠዋል።
ጋዜጠኛውን የወረፉት ትራምፕ ወደ ሲግናል ግሩፕ ሊካተት የቻለው ከዋልትዝ ረዳቶች መካከል አንድ ሰው በስኅተት ስላስገባው መሆኑን ጠቁመዋል።












