በሩሲያ ደሴት ከ500 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ እሳተ ገሞራ ፈነዳ

የፎቶው ባለመብት, Institute of Volcanology and Seismology
በሩሲያ ሩቅ ምሥራቅ በምትገኝ ደሴት ከ500 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ እሳተ ገሞራ ፈነዳ።
ባለሙያዎች ይህ ካለፈው ሳምንት ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
በካምቻትካ የሚገኘው የክራሼኒኒኮቭ እሳተ ገሞራ በአንድ ሌሊት እስከ ስድስት ኪሎ ሜትር ከፍታ ያለው አመድ ተፍቷል።
የሩሲያ የድንገተኛ አደጋ ሚኒስቴር ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ምንም ዓይነት ስጋት የለም ሲል ብሏል።
ከሰዓታት በኋላ በሩሲያ የተከሰተ ሌላ ትልቅ ርዕደ መሬት በሦስት የባሕረ ሰርጥ አካባቢዎች የሱናሚ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥ አድርጓል።
ሁለቱም ክስተቶች ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ ስፍራ ላይ ከተከሰተው እና 8.8 ከተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ ጋር የተገናኙ ሊሆኑ ይችላሉ።
ይህም እስከ ፈረንሳይ ፖሊኔዥያ እና ቺሊ ድረስ የሱናሚ ማስጠንቀቂያዎችን እንዲሰጡ አድርጎ ነበር።
የሩስያ ባለሞያዎች ረቡዕ ዕለት ከደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ ለበርካታ ሳምንታት የሚቀጥል ኃይለኛ ርዕደ መሬት ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ይህም በታሪክ ከተመዘገቡት ርዕደ መሬቶች እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀያቸው ካፈናቀሉት የበለጠ ነው።
እሁድ ዕለት የተከሰተው የርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 7.0 የተመዘገበ ሲሆን የኩሪል ደሴቶችን በመምታቱ እስከ 18 ሴ.ሜ የሚረዝም ማዕበል ሊያስከትል እንደሚችል የሩሲያ የድንገተኛ አደጋ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ዝቅተኛ የሞገድ ከፍታ ቢኖረውም በካምቻትካ ሦስት አካባቢዎች ያሉ ሰዎች አሁንም "ከባህር ዳርቻው መራቅ አለባቸው" ብሏል።
የካምቻትካ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ምላሽ ቡድን መሪ እንደተናገሩት የመጨረሻው የክራሼኒኒኮቭ እሳተ ገሞራ የተከሰተው በ15 ኛው ክፍለ ዘመን ነበር።
ኦልጋ ጊሪና ቀደም ሲል ከተከሰተው እና 8.8 ከተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችልም ገልፀዋል ሲል የሩሲያ መንግሥት የዜና ወኪል ዘግቧል።
የካምቻትካ ባሕር ሰርጥ ርቆ የሚገኝ ቢሆንም በ"የፓሲፊክ የእሳት ቀለበት" ውስጥ ይገኛል።
ስያሜው የተሰጠበት ምክንያትም ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ እና እሳተ ገሞራዎች የሚከሰቱት በዚህ አካባቢ በመሆኑ ነው።
ረቡዕ ጠዋት በሩሲያ ካምቻትካ ባሕረ ሰርጥ አካባቢ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በ8.8 በሬክተር ስኬል የተመዘገበ ሲሆን እስካሁን ከተመዘገቡት ርዕደ መሬቶች ሁሉ እጅግ ጠንካራው ነው።















