ሔዝቦላህ ሊባኖስ የጦር መሳሪያን ለመገደብ የወሰደችውን እርምጃ 'ከባድ ስህተት' ሲል ውድቅ አደረገ

የሔዝቦላህ ባንዲራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሺዓ ታጣቂ እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሔዝቦላህ የሊባኖስ መንግሥት ጦሩን የጦር መሳሪያን በብቸኝነት እንዲቆጣጠር የሚያደርገውን ውሳኔ እንደማይቀበል አስታወቀ።

ሔዝቦላህ ረቡዕ ዕለት በሰጠው መግለጫ "ይህን ውሳኔ እንደሌለ እና እንዳልተደረገ አድርገን እንቆጥረዋለን" ሲል "ከባድ ስህተት" በማለት ገልጾታል።

የሔዝቦላህ አስተያየት የተሰማው ቡድኑ ትጥቅ እንዲፈታ ዓለም አቀፋዊ ግፊት እየተደገ ባለበት ወቅት ነው።

በኢራን የሚደገፈው ቡድን ባለፈው ዓመት ከእስራኤል ጋር ባደረገው ጦርነት በከፍተኛ ደረጃ ተንኮታክቶ የነበረ ሲሆን፣ እስካሁን የአሜሪካ እና የአገር ውስጥ ተቀናቃኞች ጥሪ ቢያደርጉም የጦር መሳሪያውን ለማስረከብ ፈቃደኛ አልሆነም።

ሔዝቦላህ በተጨማሪም የሊባኖስ ካቢኔ የጦር መሳሪያ አቅርቦትን እና ምርትን በመንግሥት ኃይሎች ለመገደብ የወሰደው ውሳኔ የአሜሪካ "ተጽዕኖ" ውጤት ነው ብሏል።

"ከወረራ አንጻር" ሳይሆን "በአገራዊ የጸጥታ ስትራቴጂ" ላይ ለውይይት እና ለውይይት ክፍት እንደሆነም።

ማክሰኞ የሊባኖስ ካቢኔ በዓመቱ መጨረሻ ሁሉንም የጦር መሳሪያዎች በመንግሥት ቁጥጥር ስር ለማድረግ የሚያስችል እቅድ እንዲያቀርብ የአገሪቱን ጦር ጠይቋል።

ዕቅዱ በተያዘው ወር መጨረሻ ለውይይት እና ለማፅደቅ ለካቢኔ እንደሚቀርብ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም ለስድስት ሰዓታት ከፈጀው የካቢኔ ስብሰባ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

በሰኔ ወር የአሜሪካ ባለስልጣናት ሔዝቦላህ ሙሉ ትጥቅ የማስፈታት ሃሳብ ያለውን ፍኖተ ካርታ ለሊባኖስ ባለስልጣናት ያቀርቡ ሲሆን በፍኖተ ካርታው መሰረት በምትኩ እስራኤል ጥቃቷን እንድታቆም እና ባለፈው ሕዳር ወር የተኩስ ማቆም ስምምነት ቢደረግም እስካሁን ከያዘቻቸው እና በደቡብ ሊባኖስ ከሚገኙ አምስት ቦታዎች ወታደሮቿን እንድታስወጣ ይደረጋል።

የቡድኑ መሪ ናኢም ቃሴም የካቢኔው ስብሰባ እየተካሄደ ባለበት ወቅት በቴሌቭዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር ሔዝቦላህ የእስራኤል ጥቃት ባልቆመበት ሁኔታ "በጦር መሳሪያው ጉዳይ" ላይ እንደማይወያይ ገልፀው፣ እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነትን ጥሳለች ሲሉ ከሰዋል።

እስራኤል ጥቃቷ ሔዝቦላህ መልሶ እንዳይሰባሰብ እና እንዳይታጠቅ ለማድረግ ነው ትላለች።

ሔዝቦላህ ደረጃው ቢዳከምም በሊባኖስ የሺዓ ሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ አለው።

ትጥቅ በማስፈታት ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች በአገሪቱ ያለውን ውጥረት ከፍ ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ብዙዎች አሁንም የ1975-1990 የእርስ በርስ ጦርነትን ያስታውሳሉ።