ምግቦቻችንን ለማብሰል የትኛውን ዓይነት ዘይት እንጠቀም?

የተለያዩ ዓይነት ዘይቶች በብልቃጥ ተደርድረው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በመንደራችን የሚገኙት ሱቆችም ሆኑ የሱፐርማርኬት መደርደሪያዎች ኪስን እምብዛም ከማይጎዱት የሱፍ እና የአትክልት ዘይት ውድ እስከሆኑት የወይራ፣ የአቮካዶ እና የኮኮናት ዘይቶች ይዘዋል።

ዘይቶቹ የተለያዩ የጤና ጥቅሞች አሏቸው ከሚል ማሻሻጫ ጋር የየዕለት ማዕዳችንን ለማጣፈጥ እንጠቀማቸዋለን።

ዘይቶችና ስቦች ለዓመታት በጤና ላይ ባላቸው በጎ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ የተነሳ የክርክር ማዕከል ሆነው ቆይተዋል።

ሁሉም ስቦች በሰውነታችን ውስጥ አንድ ዓይነት ባህሪ አያሳዩም፤ አንዳንዶቹ ኮሌስትሮልን ከፍ የሚያደርጉ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ለመቀነስ ይረዱናል።

ኮሌስትሮል በጉበት ውስጥ የሚመረት ተፈጥሯዊ ስብ ያለው ንጥረ ነገር ሲሆን ከምንመገባቸው ምግቦች ውስጥም ይገኛል።

ጎጂ ኮሌስትሮል በደም ሥሮች ግድግዳ ውስጥ የስብ ክምችቶችን ከፍ ሊያደርግ ይችላል፤ ይህም የደም ስራችን እንዲጠብ ወይም እንዲዘጋ ያደርጋል።

በዘይት አጠቃቀማችን ላይ የሚነገሩ የተለያዩ መልዕክቶች የትኛውን ምርት መጠቀም እንዳለብን አጣብቂኝ ውስጥ ይጥሉናል።

በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕዝብ ጤና እና ሥነ ምግብ ፕሮፌሰር የሆኑት ኒታ ፎሮሂ አንድም ዘይት ለጤና አስማታዊ የሆነ መፍትሄ እንደሌለው ይናገራሉ።

ምግብን ለማብሰል የሱፍ እና የአትክልት ዘይት ጥሩ ነው?

ከሌሎች ዘይቶች ጋር ሲወዳደሩ የሱፍ እና የአትክልት ዘይቶች ዋጋቸው ርካሽ ናቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከሌሎች ዘይቶች ጋር ሲወዳደሩ የሱፍ እና የአትክልት ዘይቶች ዋጋቸው ርካሽ ናቸው

ከጎመን ዘር የሚመረት ዘይት (በተለምዶ የአትክልት ዘይት የሚባለው) እና የሱፍ ዘይቶች ብዙውን ጊዜ እጅግ በጣም በፋብሪካ የተቀነባበሩ ናቸው የሚል አሉታዊ ወሬ ይናፈስባቸዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የልብ እና የደም ቧንቧ ጤና ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላል ይባላል።

ነገር ግን ይህንን አሉባልታ ለመቀበል የሚያስችል ምንም ተጨባጭ ማስረጃ የለም።

በእርግጥ እነዚህ ዘይቶች አነስተኛ መጠን ያለው ከ5-10 በመቶ ድረስ ጤናማ ያልሆነ የሳቹሬትድ ስብ (satuated fat) እና ከፍተኛ ጤናማ ሞኖ እና ፖሊዩንሳቹሬትድ ስብ አላቸው።

እነዚህ ዘይቶች ጤናማ ካልሆነ ሳቹሬትድ ስብ የሚገኝባቸው ከ5-10 በመቶ ብቻ ነው። በብዛት የሚመረቱት ሞኖ እና ፖሊአንሳቹሬትድ ስቦች ከምንላቸው ነው።

ፖሊአንሳቹሬትድ ስቦች (ኦሜጋ -3 እና ኦሜጋ -6ን ጨምሮ) ለአንጎል እና ለልብ ጤና አስፈላጊ ናቸው።

ፎሮሂ እነዚህ ዘይቶች "ፍፁም ለኛ ጥሩ ናቸው" ብለዋል።

"[ኮሌስትሮል ከፍ ከሚያደርጉ] እንደ ቅቤ፣ከአሳማ ሆድ ዕቃ የሚወጣ ስብ ወይም ከወተት የሚሰራ ስብ (ghee) በእነዚህ ዘይቶች የሚተኩ ከሆነ" የበሽታ ስጋትን መቀነስ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በአብዛኛዎቹ ሱፐርማርኬቶች በአንጻራዊነት በቅናሽ የሚገኙ ሲሆን በቤት ውስጥ ለማብሰል ሳይጎዱ ጥሩ አማራጭ ሆነው ያገለግላሉ።

ማርጋሪን ኮሌስትሮልን ይቀንሳል?

የገበታ ቅቤ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማርጋሪን ለዓመታት መጥፎ ስም ተሰጥቶት ስለቆየ ብዙዎቻችን ከእሱ መራቅ እንዳለብን እናምናለን።

ይህ የሆነበት ምክንያት ከዚህ ቀደም ጎጂ የሆኑ እና ከልብ ሕመም ጋር ግንኙነት ያላቸውን ትራንስ ስቦችን ስለሚይዝ ነው።

እንደ ፎሮሂ ገለፃ ከሆነ አሁን የሚመረቱ ማርጋሪኖች "ወደ ዜሮ የሚጠጋ ትራንስ ስብ አላቸው።"

"ስለዚህ የጤናማ አመጋገባችን አካል ሊሆን እና ጎጂ ኮሌስትሮልን ሊቀንስ ይችላል።"

"ቅቤ የሚወዱ ከሆነ፣ ለምሳሌ በተጠበሰ ዳቦ ላይ፣ በሌሎች ምግቦች ውስጥ" ይላሉ ፎሮሂ ቅቤም እንዲሁ ሙሉ በሙሉ ከዝርዝሩ ውጪ አይደለም።

ማርጋሪን እና ቅቤን ምግብ ለማብሰል መጠቀም ይችላል። ነገር ግን ፎሮሂ አንዳንድ ጊዜ አነስተኛ መጠን ሳቹሬትድ ስብ ባላቸው ዘይቶች መተካት ይመከራል።

የዩናይትድ ኪንግደም የጤና መመሪያዎች የምንመገበውን ሳቹሬትድ ስብ ካሎሪ ከ10 በመቶ በታች ለማድረግ በቅቤ ፋንታ በዘይት ማብሰል ይመክራሉ።

ለመጠባበስ የወይራ ዘይት አይመከርም

ምግብ ሲጠባብሱ የሱፍ ወይንም የአትክልት ዘይት ይጠቀሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዘይቶች ሲግሉ የተለየ ባህሪ ይኖራቸዋል፤ ይህም አንዳንዶቹን ለመጥበስ የማይመቹ ያደርጋቸዋል።

ለምሳሌ ኤክስትራ ቨርጅን ኦሊቭ ኦይል በፀረ-ኦክሲዳንት እና ጠቃሚ ውህዶች የተሞላ ነው።

ነገር ግን ለሚጠባበሱ ምግቦች ከመጠቀም ይልቅ በዝቅተኛ ሙቀት ስለሚቃጠል ለሰላጣ ወይም ምግብ ላይ በትንሹ ፈሰስ አድርጎ ቀላቅሎ ለመመገብ መጠቀም ይሻላል።

በዝቅተኛ ሙቀት ይቃጠላል ማለት በዘይቱ ውስጥ ያሉት ስቦች መሰባበር የሚጀምሩበት እና ጎጂ ውህዶች የሚለቀቁበት ፍጥነት ሲሆን ይህም ዘይቱ መራራ፣ የተቃጠለ ወይም ደስ የማይል ጣዕም እንዲኖረው ያደርጋል።

የሬስቶራንት ባለሙያ ቲም ሃይዋርድ ምግብ ለማብሰል ከሆነ መደበኛውን የወይራ ዘይት እጠቀማለሁ ብሏል።

ነገር ግን እንደ የድንች ጥብስ ቺፕስ ወይም አሳ ለመጥበስ የአትክልት ወይም የሱፍ ዘይት መጠቀም ከፍተኛ ሙቀትን ስለሚቋቋም የተሻለ ነው።

አንዳንድ ጥናቶች የአትክተልት እና የሱፍ ዘይቶች ቶሎ ከሚግሉ ዘይቶች የበለጠ መርዛማ ኬሚካሎችን እንደሚለቁ ያሳያሉ።

ነገር ግን ፕሮፌሰር ፎሮሂ በቤት ውስጥ በዚህ መንገድ ምግብ ማብሰል በጣም የተለመደ አይደለም። ስለዚህ የረዥም ጊዜ የጤና ጥናቶች አሁንም የሚያሳዩት የአትክልት ዘይቶች "ያለምንም ልዩነት ለአደገኛ በሽታዎች የማጋለጥ እድላቸው ዝቅተኛ መሆኑን ነው።"

ምግባችንን ለማብሰል የትኛውን ዘይት እንጠቀም?

በምግብ ማብሰያዎ ውስጥ ቀለል ያለ ስልት እያሰቡ ከሆነ፡

  • በየዕለቱ ለማብሰል የሱፍ ወይንም የአትክልት ዘይት ዋጋው ኪስ አይጎዳም፤ ጤናማ ነው፤ ለተለያዩ ምግቦች ሊውል ይችላል። መደበኛውን የወይራ ዘይትም መጠቀም ይችላሉ።
  • ለሰላጣ እና ምግብ ላይ ፈሰስ አድርጎ ለመመገብ ኤክስትራ ቨርጅን ኦሊቭ ኦይል የተሻለ ጣዕም እና ጥቅም አለው።
  • ለመጠባበስ የአትክልት እና የሱፍ ዘይትን መጠቀም ይመረጣል።
  • ለተለያየ ጣዕም የተለያዩ የጤና ጥቅም ቢኖራቸውም የወይራ ዘይት፣ የሰሊጥ፣ ኮከናት ወይም አቮካዶ ዘይቶችን በቀዝቃዛ ምግቦች ላይ ለጣዕም መጠቀም ይቻላል።

በአጠቃላይ ፕሮፌሰር ፎሮሂ የትኛውን ዘይት መግዛት እና መጠቀም አለብኝ ብሎ ከመጨነቅ ይልቅ አጠቃላይ አመጋገብን መመልከቱ የተሻለ ነው ይላሉ።

"ምን ዓይነት ጣዕም እና ዋጋ ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብኝ የሚለውን እና አንዳንድ የጤና ጥቅማ ጥቅሞችን በሚያስገኝልዎት የተለያዩ የዘይት ዓይነቶችን እንዲሞክሩ እመክራለሁ" ብለዋል።