መምህራን በሴቶች ላይ አሉታዊ አመለካከት ያላቸው ታዳጊ ወንዶችን እንዲለዩ ሥልጠና ሊሰጥ ነው

ታዳጊዎች

የፎቶው ባለመብት, PA Media

ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ሴቶች ላይ የሚደርስ ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል ያወጣችው ዕቅድ፤ መምህራን ፆተኛ ባህሪ የሚያሳዩ ታዳጊ ወንዶችን የሚለዩበት ሥልጠናን ያካትታል።

ይፋ የሚደረገው አገር አቀፍ ዕቅድ ታዳጊ ወንዶች አክራሪ እንዳይሆኑ መከላከልን ይጨምራል።

ፆተኛነት (misogyny) በሴቶች ላይ ፆታን መሠረት ያደረገ መድልዎ እና ጥላቻን የሚገልጽ ቃል ሲሆን፤ ሴቶች ላይ ለሚደርስ ፆታዊ ጥቃት መነሻ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ ነው።

ታዳጊ ወንዶች ፈቃድ መስጠት (consent) ምን ማለት እንደሆነ እንዲሁም የሰዎችን ግላዊ/ምሥጢራዊ ምሥሎች (intimate images) ማጋራት ስለሚያስከትለው አደጋ ሥልጠና ይሰጣቸዋል።

በተጨማሪም በሕይወታቸው ላይ አወንታዊ ሚና ያላቸው ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን መለየት እንዲችሉ እንዲሁም ስለ ሴቶች እና ስለ ፍቅር ግንኙነት የተዛቡ ምልከታዎችን እንዳያራምዱም ይሠለጥናሉ።

ወጣቶች በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ጥቃት ሲፈጸምባቸው ጥቆማ የሚሰጡበት ነጻ የስልክ መስመር ተዘጋጅቷል።

ዩኬ ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል ላወጣችው ዕቅድ 20 ሚሊዮን ፓውንድ መድባለች።

ታዳጊዎች ዕድሜያቸው ሲጨምር ጥቃት አድራሽ እንዳይሆኑ ፆተኛ ባህሪ ማሳየት ሲጀምሩ እንዲታረሙ ማድረግ በዕቅዱ ተካቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ የሆኑ ታዳጊ ወንዶች የባህሪ ማስተካከያ ሥልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል። ስለ ታዳጊ እና አዋቂ ሴቶች ያላቸውን አመለካከት ለማቃናት እንደሚሠራም ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር "ሁሉም ወላጅ ሴት ልጁ ትምህርት ቤት ስትሄድ፣ በበይነ መረብ ላይ እንዲሁም በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ሆና ደኅንነቷ የተጠበቀ መሆኑን ማወቅ አለበት" ብለዋል።

"መርዛማ ባህሪ የሚጀምረው በታዳጊነት ነው። ምንም መፍትሔ ሳይሰጠውም ወጣቶቹ ዕድሜያቸው ይጨምራል" ሲሉም አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ መንግሥታቸው በአፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ ወስኗል።

"መምህራን የፆተኛ ባህሪ ምልክትን እንዲለዩ እናግዛለን። ጉዳት ሳይደርስ በፊት መቀልበስ መቻል አለብን" ብለዋል።

ከተመደበው በጀት ውስጥ 16 ሚሊዮን ፓውንድ የሚሆነው ከታክስ የሚሰበሰብ ሲሆን፤ የተቀረውን 4 ሚሊዮን ፓውንድ የሚሸፍኑት በጎ አድራጊዎች ይሆናሉ።

'ሪድዩሲንግ ዘ ሪስክ' የተባለው የተራድዖ ድርጅት ባወጣው አሃዝ መሠረት በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ከሚገኙ ታዳጊዎች መካከል 40 በመቶ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል።

የበይነ መረብ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ለጥቃቶች መጨመር ዋነኛ ተጠያቂ ተደርገዋል።

ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 15 ከሚደርስ አምስት ታዳጊ ወንዶች ቢያንስ አንዱ ለአንድሪው ቴት በጎ አመለካከት እንዳለው የመንግሥት መረጃ ቋት 'ዩ ጎቭ' ይጠቁማል።

አንድሪው ቴት ራሱን ፆተኛ ሲል ይጠራል።

የቤከን ሂል አካዳሚ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት ሱክጆት ዳሚ "መንግሥት ጤናማ የፍቅር ግንኙነትን ለማበረታታት የሚወስደውን እርምጃ እንደግፋለን። እኛም ለዓመታት ተመሳሳይ እርምጃዎች ወስደናል" ብለዋል።

መንግሥት የመደበው በጀት "በተገቢው መንገድ" ጥቅም ላይ እንዲውልም አሳስበዋል።

የትምህርት ቤት አመራሮች ማኅበር ዋና ፀሐፊ ፖል ዋይትማን የመንግሥትን እርምጃ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቶች የሚወሰደው እርምጃ እንዳለ ሆኖ በጤናው ዘርፍ፣ በማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማት፣ በፖሊስ መዋቅር እና በወላጆች መስተጋብርም ለውጥ መምጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

መንግሥት በበይነ መረብ የሚፈጸም ጥቃት ላይ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል።

የቤት ውስጥ ጥቃት የተፈጸመባት ኒኮላ ማክፈርቲ እንዳለችው፤ ታዳጊዎችን ማስተማር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።

"ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችም ወንዶችም ታዳጊዎችን ማስተማር አለባቸው። ከተሞክሯቸው የሚሰጡት ትምህርት ለውጥ ያመጣል" ብላለች።

የዩኬ መንግሥት ያወጣው ዕቅድ ላይ ወሲባዊ ጥቃትን የሚመለከት ልዩ የፖሊስ ክፍል ማቋቋም ተካቷል።

ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሰዎች ጥበቃ የሚደረግበት አሠራር እንደሚዘረጋ ተገልጿል።

ጥቃት አድራሾች ጥቃት ከፈጸሙባቸው ሰዎች ጋር እንዳይገናኙ ማገድ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ጎጂ ይዘት እንዳይለጥፉ መከልከልም የዕቅዱ አካል ነው።

የዩኬ ብሔራዊ የጤና ማዕቀፍ ጥቃት ለደረሰባቸው ሰዎች የሚሰጠው ድጋፍ እንዲጠናከር ተወስኗል።