የአሜሪካ ፍርድ ቤት በኡበር አሽከርካሪ መደፈሯን ለገለጸች ሴት ኩባንያው 8.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ወሰነ

የኡበር ስቲከር የተለጠፈበት መኪና

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ ፍርድ ቤት፤ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢው 'ኡበር' አሽከርካሪ በሆነ ግለሰብ መደፈሯን ለገለጸች ሴት ኩባንያው 8.5 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍል ወሰነ። ይህ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ኩባንያው ላይ የቀረቡ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ተመሳሳይ ክሶች ውጤት ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ተገልጿል።

ለሁለት ቀናት የፍርድ ሂደቱን ያካሄዱት የአሪዞና ፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች፤ አሽከርካሪው ለፈጸመው ድርጊት ኡበር ተጠያቂ እንደሆነ ደምድመዋል። ኡበር በበኩሉ የፍርድ ውሳኔው ላይ የይግባኝ አቤቱታ እንደሚያቀርብ ገልጿል።

ዳኞቹ ከዚህ ጋር ተያይዞ የቀረቡላቸውን ሌሎች ክሶች ግን ውድቅ አድርገዋል። ውድቅ የተደረጉት ክሶች ኡበር ቸልተኛ እንደሆነ እንዲሁም የደንበኛ ደኅንነት ሥርዓቶቹ ጉድለት እንዳለባቸው የሚገልጹ ነበሩ።

ክሱን ያቀረበችው ጄይሊን ዲን በአውሮፓውያኑ 2023 በኡበር መኪና ጠርታ ወደ ሆቴሏ እየተጓዘች ባለችበት ሰዓት ፆታዊ ጥቃት እንደተፈጸመባት ገልጻለች።

ኡበር አሽከርካሪዎቹ ስለሚፈጽሟቸው በርካታ ፆታዊ ጥቃቶች ቢያውቅም የደንበኞቹን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል መሠረታዊ የማሻሻያ እርምጃዎችን እንዳልወሰደ በመግለጽ ከስሳለች።

አሽከርካሪው ድርጊቱን የፈጸመው ኩባንያውን ወክሎ እየሠራ ባለበት ወቅት እንደሆነ የጠቀሰው ፍርድ ቤቱ፤ በዚህም ምክንያት ኩባንያው ተጠያቂ እንደሆነ አስታውቋል። ለከሳሿ 8.5 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍልም አዝዟል።

ፍርድ ቤቱ ይህንን የካሳ ገንዘብ መጠን የወሰነው ከሳሿ ዲን የጠየቀችውን ከ144 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆነ የቅጣት ክፍያ ውድቅ በማድረግ ነው።

የዲን ጠበቃ ሳራ ለንደን፤ ውሳኔው "ታላቅ የግል መስዋዕትነት ከፍለው ብቅ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጎጂዎችን ትክክል ያደረገ ነው" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፍትሕ መሰጠቱ "በትክክል የሚለካው በቀጣይ በሚደረጉ የፍርድ ሂደቶች ውጤት እና በቀጣይ ተጓዦችን ለመጠበቅ የሚያስችል ትርጉም ያለው የደኅንነት ማሻሻያ ይደረጋል ወይስ ይደረግም በሚለው ነው" ብለዋል።

ይህ የዲን ክስ፣ ኡበር ላይ ከቀረቡ እና በቀጣይ በተከታታይ ለፍርድ ከሚቀርቡ 20 "ማሳያ" ክሶች መካከል አንዱ ነው። እነዚህ ክሶች በፌደራል ፍርድ ቤት በተመሳሳይ ክስ ለቀረቡ 2,500 ገደማ ሌሎች መዝገቦች ማጣቀሻ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላኛዋ የዲን ጠበቃ አሌክሳንድራ ዎልሽ፤ ኡበር ራሱን በምሽት ብቻቸውን ለሚጓዙ ሴቶች ደኅንነቱ የተጠበቀ አማራጭ አድርጎ እንደሚያስተዋውቅ በፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

"ሴቶች አደገኛ ዓለም መሆኑን ያውቃሉ። የፆታዊ ጥቃት ስጋት መኖሩን እናውቃለን። [ኡበር] ከዚህ ስጋት ነፃ የሆነ ቦታ እንደሆነ እንድናምን አድርጎናል" ብለዋል።

ኡበር በበኩሉ መተግበሪያውን የሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች ለሚፈጽሙት የወንጀል ድርጊት ተጠያቂ መሆን እንደሌለበት ተከራክሯል። አሽከርካሪዎቹ ገለልተኛ ኮንትራክተር እንደሆኑ እና ከመመዝገባቸው በፊት የወንጀል ታሪክ ምርመራ እንደሚደረግባቸው ገልጿል።

ድርጊቱ አስቀድሞ ሊታይ የሚችል እንዳልነበረ የተከራከሩት የኩባንያው ጠበቆች፤ ክስ የቀረበበት አሽከርካሪ በተሳፋሪዎች ከፍተኛ ደረጃ (rating) የተሰጠው እንዲሁም ምንም የወንጀል ታሪክ የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።

የኩባንያው ቃል አቀባይ በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ "ኡበር ቸልተኛ ነበር ወይም የደኅንነት ጥበቃ ሥርዓቶቹ ጉድለት አለባቸው የሚሉትን ክሶች ውድቅ አድርጓል" ብለዋል።

"የተወሰነው የካሳ መጠን ከተጠየቀው በጣም ያነሰ ነው፤ የቅጣት ክፍያውም ሙሉ በሙሉ ውድቅ ተደርጓል። ይህ ውሳኔ ኡበር በኃላፊነት ስሜት እንደተንቀሳቀሰ እና በተሳፋሪዎች ደኅንነት ላይ ትርጉም ያለው ኢንቨስትመንት ማድረጉን የሚያረጋግጥ ነው" ብለዋል።