አስተማሪውን በጥይት የመታው የስድስት ዓመቱ አሜሪካዊ ከክስ ነፃ ሊሆን ነው

በዩናይትድ ስቴትስ ቨርጂኒያ ግዛት አስተማሪውን በጥይት የመታው የስድስት ዓመት ሕፃን ከክስ ነፃ እንደሚሆን አቃቤ ሕግ አስታወቀ።

ነገር ግን በሁኔታው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃቸው አለበት የተባሉ አዋቂዎች ክስ ሊመሰርትባቸው ይችላል።

ኒውፖርት ኒውስ በተሰኘው ከተማ ነው ነፍስ ያልገዛ ሕፃን ልጅ አስተማሪውን በጥይት የመታት።

ፖሊስ እንደሚለው ባለፈው ጥር ሕፃኑ ተማሪ ሽጉጡን በቦርሳው ታጥቆ ነው ሪችኔክ ወደሚባለው አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የገባው።

የ25 ዓመቷ አቢጌይል ዝዌነር እግሯና አንገቷ አካባቢ ጥይት ቢያገኛትም ከሞት ተርፋለች።

ረቡዕ ዕለት የኒውፖርት ኒውስ አቃቤ ሕግ ሃዋርድ ግዊን ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ቢሯቸው ሕፃኑን አይከሰውም።

አቃቤ ሕጉ እንደሚሉት “ሕፃን ልጅን ከሶ ለፍርድ ማቅረብ የማይታሰብ ነው” ምክንያቱም ጨቅላው ሕጉ ምን እንደሚል እንኳን አያውቅም።

አቃቤ ሕጉ አክለው በፍጥነት ምንም ዓይነት ውሳኔ እንደማይሰጡና ሁኔታዎችን እንደሚያጤኑ ተናግረዋል።

“እውነታውን ካጠራን በኋላ ያለምንም ጥርጥር ወንጀል ሠርቷል ብለን የምናስበው ሰው ካለ ክስ እናቀርብበታለን።”

ግዊን፤ እንደሚሉት የስድስት ዓመቱ ልጅ “የሰው ልጅ ላይ ወንጀል ለመሥራት አስቦ የሚፈፅመው ነገር ስለሌለ ክስ ማቅረብ የማይሆን ነገር ነው።”

ቀን እጇንና ደረቷ አካባቢ በጥይት የተመታችው አስተማሪ ትምህርት ቤቱን ልትከስ አስባለች።

ፖሊስ እንደሚለው አስተማሪዋ ከሕፃኑ ጋር በገቡት አለመግባባት ነው ሕፃኑ አንጠልጥሎ ከሚዞረው ቦርሳ ሽጉጥ አውጥቶ የመታት።

ከሕግ እውቅና ውጭ የተገዛ ነው የተባለው ሽጉጥ የሕፃኑ እናት ንብረት መሆኑን ፖሊስ አረጋግጧል።

ሕፃኑ አስተማሪውን በጥይት ከመታት በኋላ ፖሊስ ወደሥፍራው ሲደርስ አንድ ሌላ ግለሰብ ሕፃኑን ይዞት አግኝቶታል።

አስተማሪዋ ሁለት ጎዜ በጥይት ከመታች በኋላ እርዳታ ከመጥራቷ በፊት ሌሎቹ ሕፃናት አደጋ እንዳይደርስባቸው ከመማሪያ ክፍሉ እንዲወጡ አድርጋ ነበር።