ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አምስት አገራት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እየተካሄደ ያለው ግጭት አሳስቦናል አሉ
አምስት አገራት በቅርቡ በኢትዮጵያ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የተከሰቱት ግጭቶች እንዳሳሰባቸው በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታወቁ።
አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስትራሊያ፣ ጃፓን እና ኒው ዚላንድ ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ በሁለቱ ክልሎች በቅርቡ የተከሰተው ግጭት ለሰላማዊ ሰዎች ሞት እና አለመረጋጋት ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
በሁለቱ ክልሎች በሚካሄዱ ግጭቶች ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ ሰላማዊ ሰዎችን እንዲጠብቁ፣ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብሩ እና ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ አገራቱ ጠይቀዋል።
በአማራ ክልል ከሰሞኑ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ከማስከተሉ በላይ በክልሉ አለመረጋጋትን ፈጥሯል።
የክልል ልዩ ኃይሎችን ትጥቅ ከማስፈታት ጋር ተያይዞ በክልሉ ለወራት የቆየው ውጥረት ባለፈው ሳምንት ወደ ግጭት ካመራ በኋላ የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት አቋርጧል፣አንዳንድ አካባቢዎችም በታጣቂዎች ቁጥጥር ውስጥ ገብተው ነበር።
ይህ በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት ከክልሉ አቅም በላይ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ፣ የፌደራሉ መንግሥት በአዋጁ ያቋቋመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ወሰድኳቸው ባለው የሕግ ማስከበር እርምጃዎች ክልሉ ወደ አንጻራዊ ሰላም እየተመለሰ መሆኑን ገልጿል።
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንቅስቃሴን ተከትሎ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሰላም ከራቃቸው ዓመታት ተቆጥረዋል።
ታጣቂ ቡድኑ በስፋት በሚንቀሳቀስባቸው አራቱ የወለጋ ዞኖች፣ ሰሜን እና ምሥራቅ እና ምዕራብ ሸዋ እንዲሁም በቦረና እና እና ጉጂ ዞኖች የሰላም መደፍረስ ሲያጋጥማቸው ቆይተዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች የሰላማዊ ሰዎች ግድያ እና አፈና፣ የሰላም እጦት፣ የትራንስፖርት እና የስልክ ግንኙነት መቋረጥ በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ክስተቶች ናቸው።
በተለይ አሜሪካ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባት በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊዋ አንቶኒ ብሊንከን በኩል ባለፈው ሳምንት ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸው ነበር።
በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ያሳሰባቸው አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አውስትራሊያ ዜጎቻቸው ወደ አማራ ክልል እንዳይሄዱ፣ እዚያም ያሉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ ለመሄድ የሚፈልጉም ምክር እንዲጠይቁ ካሳሰቡ አገራት መካከል ይገኙበታል።
አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስትራሊያ፣ ጃፓን፣ ኒው ዚላንድ ዛሬ አርብ ነሐሴ 5/2015 ዓ.ም. ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ የኢትዮጵያውያንን የረዥም ጊዜ የተረጋጋ አገር የመፍጠር ግብን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መደገፉን ይቀጥላል ብለዋል።
ምዕራባውያን አገራት በተለይ ከሰሞኑ በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት እንዳሳሰባቸው እና የግጭቱ ተሳታፊዎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ሲጠይቁ ቆይተዋል።