ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወግ አጥባቂው የዩኬ የሕዝብ እንደራሴ በመድፈር ተጠርጥረው ታሰሩ
ስማቸው ያልተገለጸ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ወግ አጥባቂ የሕዝብ እንደራሴ በመድፈር እንዲሁም ወሲባዊ ትንኮሳ በማድረስ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።
ሜትሮፖሊታን ፖሊስ እንዳለው ግለሰቡ ጥቃት የፈጸሙት እአአ ከ2002 እስከ 2009 ባሉት ዓመታት ነው።
ወግ አጥባቂው ፓርቲያቸው ጉዳዩ ላይ ምርመራ ተደርጎ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ግለሰቡ ወደ ፓርላማ እንዳይገቡ አግዷል።
ግለሰቡ የተጣለባቸውን እምነት በመሸርሸር እንዲሁም በሕዝብ ቢሮ ያልተገባ ድርጊት በመፈጸምም ተከሰዋል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ የግለሰቡን ማንነት ወይም የሕዝብ እንደራሴ መሆናቸውን በግልጽ አልተናገሩም። ሆኖም ግን "ጥር 2020 ላይ በደረሰን ሪፖርት መሠረት ግለሰቡ ከ2002 እስከ 2009 ባሉት ዓመታት ወሲባዊ ጥቃት እንደፈጸሙ ተገልጿል" ብለዋል።
በደረሳቸው ሪፖርት መሠረት ጥቃቶቹ የተፈጸሙት በለንደን እንደሆነም ገልጸዋል።
"ግለሰቡ በመድፈር፣ በወሲባዊ ትንኮሳ፣ በወሲባዊ ጥቃት፣ እምነትን በማጉደል እና በሕዝብ ቢሮ ያልተገባ ድርጊት በመፈጸም ክሶች ተጠርጥረው ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት" ሲሉም አክለዋል።
የወግ አጥባቂ ፓርቲው የሥነ ምግባር ክፍል እንዳለው፣ ግለሰቡ ላይ እየተካሄደ የሚገኘው ምርመራ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ወደ ፓርላማ እንዳይገቡ ታግደዋል።
የሥነ ምግባር ክፍሉ ቃል አቀባይ "ምርመራው ሳይጠናቀቅ ግለሰቡ ወደ ፓርላማ እንዳይመጡ ፓርቲው አሳውቋቸዋል። ምርመራው እስከሚያልቅ ድረስ ስለ ጉዳዮ ተጨማሪ አስተያየት አንሰጥም" ብለዋል።
ፖሊስ እንዳለው፣ የወንጀል ምርመራ ክፍል ባልደረባ ጉዳዩን እየተከታተሉ ነው።