ሕንዳዊው ነጋዴ ለሚስቱ ታጅ መሐልን የመሰለ ቤት አሠራ

ቤቱን ለመገንባት ወደ 260,000 ዶላር ወጪ ተደርጓል ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, ANAND PRAKASH CHOUKSEY

የምስሉ መግለጫ, ቤቱን ለመገንባት ወደ 260,000 ዶላር ወጪ ተደርጓል ተብሏል

የ52 ዓመቱ ሕንዳዊ ነጋዴ 27 ዓመታት በትዳር አብረው ለኖረች ሚስቱ መኖሪያ እንዲሆን ታጅ መሐልን የመሰለ ቤት አስገነባ።

አናንድ ፕራካሽ ቹክሴይ በማዕከላዊ ሕንድ በሚገኘው ማድያ ፕራዴሽ ግዛት በቡርሃንፑር ከተማ ነው "የፍቅር ሐውልቱን" ያስገነባው።

"ለባለቤቴ የተሰጠ ስጦታ ነው። ለእሷ ብቻ ሳይሆን ለከተማዋ እና ለሕዝቦቿም ጭምር የተበረከተ ስጦታ ነው" ሲል ቹክሴይ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ቤቱን ለመገንባት ወደ 260,000 ዶላር ወጪ ተደርጓል ተብሏል።

ታጅ መሐል በአግራ ከተማ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባ መቃብር ነው። የሙጋሉ ንጉሠ ነገሥት ሻህ ጃሃን 14ኛ ልጃቸውን ሲወልዱ ሕይወታቸው ላለፈው ንግሥት ሙምታዝ መታሰቢያ ነው የተገነባው።

በረቀቀ ሥራው የሚታወቀው አስደናቂው የዕምነ በረድ ሐውልት የሕንድ ትልቁ የቱሪስት መስህብ ነው። ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ዝነኞችን እና ታዋቂ ሰዎችን ጨምሮ በየቀኑ እስከ 70,000 የሚደርሱ ሰዎች ይጎበኙታል።

ቹክሴይ ያስገነባው ቤት ሆስፒታልን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን በሚሰጠው ባለ 50 ሄክታር ግቢ ውስጥ የተንጣለለ ሲሆን ጎብኝዎችንም እየሳበ ነው። ሰዎች እየተዘዋወሩ ፎቶ ያነሳሉ።

ቹክሴይ "ብዙ ሰዎች ከሠርጋቸው በፊት ፎቶ ለመነሳት መምጣት ጀምረዋል" ብሏል።

"እኔ አልከለክላቸውም። ምክንያቱም ከተማችን ሁሉም ሰው የሚተዋወቅበት የአንድ ማኅበረሰብ ነው። ስለዚህ ቤቴ ለሁሉም ክፍት ነው።"

ቹክሴይ ሁሉም ጎብኚዎች ወደ ቤቱ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም። ምክንያቱም "ምንም ቢሆን የምንኖርበት ቤታችን ነው" ብሏል።

ቤቱ በሁለት የተለያዩ ወለሎች ላይ የሚገኙ ሁለት ዋና የመኝታ ክፍሎችን የያዘ ነው። ቤተ መጻሕፍት እና የሜዲቴሽን ክፍልም አለው።

ቾክሴይ እንደተናገረው፤ ምንም እንኳን ታጅ መሐል መነሻው ቢሆንም የውስጥ ክፍሎቹ ንድፍ እስላማዊ አይደሉም። የዘመናዊ ኪነ ሕንጻ ተጽዕኖ አርፎባቸዋል።

ይህንንም ከሶፋዎች እና ከመጋረጃዎች ምርጫ ማወቅ ይቻላል።

የታዋቂውን ሐውልት ቅጂ ለመገንባት ሦስት ዓመት ፈጅቷል።

ቹክሴይ "ቤቱን ለመገንባት ብዙ የታጅ መሐልን አውታር ምስሎች ከበይነ መረም ወስደናል" ብሏል።

መሐንዲሶች የቤቱን መጠን ከትክክለኛው ሐውልት በአንድ ሦስተኛ አሳንሰውታል።

በታጅ መሐል ውበት የተነሳሳው ቹክሴይ ብቻ አይደለም።

እአአ በ2013 በሰሜን ሕንድ ኡታር ፕራዴሽ ግዛት አንድ ጡረታ የወጣ የመንግሥት ባለሥልጣን ለሚስቱ መታሰቢያ እንዲሆን ታጅ መሐልን የሚመስል ቤት አሠርቷል ።

ቹክሴይ ቤቱ ለሚስቱ ብቻ የተሰጠ አለመሆኑን አስታውቋል።

"ዛሬ በአገራችን ብዙ ጥላቻ አለ። ሰዎች በሃይማኖትና በጎጥ ስም እየተከፋፈሉ ነው" ብሏል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የሂንዱ ብሔረተኛው ቢጄፒ ፓርቲና መንግሥት ሕንድን በሃይማኖት በመለያየት አለመቻቻልን እያስፋፋ ነው ተብሎ ተከሷል።

ሌላው ቀርቶ ታጅ መሐል እንኳን በጉዳዩ ተካቷል።

እአአ በ2017 የቢጄፒ የሕግ ባለሙያ የሆኑ ግለሰብ መታሰቢያ ሐውልቱን በ"ከዳተኞች" የተገነባ "የሕንድ ባህል ጥቁር ነጥብ" ብሎታል።

ቹክሴይ በእንደዚህ ዓይነቱ አስጨናቂ ጊዜያት ፍቅርን ማስፋፋት እንደሚፈልግ ተናግሯል።

"እናም ይህ ቤት ከማኅበራዊ ልዩነቶቻችን እና ከፖለቲካዊ ጫጫታ በላይ ለእኔ ፍቅር ምልክት ነው።"