'በኢላን መስክ ቢትኮይን' 9ሺህ ፓዎንድ የተጭበረበረች ሴት

በኢንተርኔት አጭበርባሪዎች ተሸውዳ ያጠራቀመችውን ገንዘብ ያጣችው ሴት ሌሎች ከእስርሷ ተምረው ከመሰል አጭበርባሪዎች እንዲጠነቀቁ መልዕክቷን አስታልፋለች።

ጁሊ በሽኔል እንደምትለው በቢትኮይን ስም በተፈጸማባት ማጭበርበር ምክንያት 9 ሺ ፓውንድ እንዳጣችና በዚህም በራሷ እንድታፍርና የመዋረድ ስሜት እንዲሰማት ማድረጉን ትገልጻለች።

አጭበርባሪዎቹ የታዋቂው ስራ ፈጣሪና ቢሊየነሩ ኢላን መስክን ስም በመጠቀም እንዲሁም ሐሰተኛ የቢቢሲ ድረገጽ ላይ ገንዘቧን ክሪፕቶከረንሲ ላይ ብታውል በእጥፍ ትርፍ እንደምታገኝ የሚገልጽ ጽሁፍ አሳይተዋታል።

ነዋሪነቷን በብራይተን ያደረገችው ጁሊ "በእያንዳንዱ ቀን በእያንዳንዷ ደቂቃ ስለተፈጠረው ነገር ማሰብ አላቆምም" ብላለች።

ከዚህ በፊት ክረፕቶከረንሲ ላይ ልምድ እንዳላት የምትናገረው ጁሊ፤ አጭበርባሪዎቹ ባሳዩዋት ሐሰተኛ የቢቢሲ ድረገጽ ላይ ቢሊየነሩ ኢላን መስክ ገንዘባቸውን ክሪፕቶከረንሲ ላይ ለሚያውሉ ሰዎች በቢትኮይን በኩል በእጥፍ ገንዘብ እንደሚከፍል የሚገልጽ ጽሁፍ ተመልክታለች።

ጁሊ ይህን ከተመለከተች በኋላ ቤት ለመግዛት ስታጠራቅመው የነበረውን 9 ሺ ፓውንድ ከፍላለች። ነገር ግን በእጥፍ ይከፈልሻል የተባለውን ገንዘብ ቁጭ ብላ ብትጠብቅም የውሃ ሽታ ሆነ ቀርቷል። በመጨረሻም እንደተጭበረበረች ገባት።

"በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቶኛል። ያንን ውሳኔ የወሰንኩበትን ሰዓት ተመልሼ ባገኘው ደስ ይለኛል። በጊዜ ማሽን ወደ ኋላ ተመልሼ ያደረኳቸውን ነገሮች በሙሉ ባስተካክል ደስ ይለኛል" ትላለች።

ጁሊ መጭበርበሯን ካወቀች በኋላ ለሰሴክስ ፖሊስ ጉዳዩን አሳውቃለች። "ገንዘቤን ብቻ ሳይሆን ክብሬን፣ ለራሴ የምሰጠውን ክብር እና ጥንካሬዬን ነው የተሰረቅኩት። በሕይወቴ ሊኖረኝ የሚችለውን ደስታ በሙሉ ነው የነጠቁኝ'' ብላለች።

"ሌሎች ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች እኔን ያጋጠመኝ ተመሳሳይ ነገር እንሱንም እንዳይገጥማቸው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መስራት እፈልጋለሁ"

የሚያስገርመው ደግሞ ሐሰተኛው የቢቢሲ ድረገጽ አሁንም ድረስ አለመዘጋቱ ነው።

በክሪፕቶከረንሲ አማካኝነት የሚደረጉ ማጭበርበሮች ላይ ጥናት የሰራው 'ክሪፕቶ ኮምዩኒቲ' እንደሚለው በአውሮፓውያኑ 2021 የመጀመሪያ ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ አጭበርባሪዎች ከ18 ሚሊየን ዶላር በላይ በተመሳሳይ መንገድ አጭበርብረዋል። ከ5 ሺ 600 በላይ ሰዎች ደግሞ በዚህ ማጭበርበር ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ባለፈው 2020 ሙሉ ዓመት ደግሞ 10 ሺ 500 ሰዎች ተመሳሳይ ማጭበርበር አጋጥሟቸዋል።

ቢቢሲ ተመሳስሎ የተሰራውን ሐሰተኛ የቢቢሲ ድረገጽ ለማዘጋት ጥረት እያደገ እንደሆነ በመግለጽ "ሰዎች የድረገጾችን ተዓማኒነት በደንብ ማጣራት አላባቸው፤ የግል መረጃቸውን በቀላሉ መስጠት የለባቸውም'' ብሏል።