ከአደገኛ እጽ አዘዋዋሪነት ወደ ፓስተርነት

ሚክ ፍሌሚንግ በ40ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው።

አንድ ምሽት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ በር ላይ ሰው እየጠበቀ ነበር።

ሚክ የነበረበት የተሰረቀ መኪና ሞተሩ አልጠፋም። የሚጠብቀውን ሰው በፍጥነት ተገላግሎ ለመሄድ ወስኗል።

"እሱም እንደኔው አደገኛ እጽ አዘዋዋሪ ስለሆነ እንቅስቃሴው ምን እንደሚመስል አውቃለሁ" ሲል ምሽቱን ያስታውሳል።

ሚክ በሰሜን ምዕራብ እንግሊዝ እጽ አዘዋዋሪዎች ዘንድ ይታወቃል። የእጽ ዝውውር ክፍያ ያልፈጸመ ሰው ካለ የሚላከው እሱ ነው። እንዳይሞቱ እንዳይተርፉ አድርጎ ይቀጠቅጣቸዋል።

"በዚያ ምሽት ሽጉጤ ፕላስቲክ ውስጥ ነበር። የጣት አሻራ አያርፍበትም። ስድስቱ ጥይት የሚፈለገውን ተግባር ለመፈጸም ይውላል።"

ብዙም ሳይቆይ የሚጠበቀው ሰው መጣ።

"ከስፖርት ማዘውተሪያው ሲወጣ ሁለት ልጆች ይዞ ነበር። አምስት ዓመት የሚሆናቸው ሴት ልጆች አብረውት ነበሩ። ከመኪናው ሽጉጡን ይዤ ወረድኩ። ስጠጋው እነዛን ንጹህ ልጆች በቅርበት አየኋቸው" ሲል ያስታውሳል።

ከዚያ የተከሰተውን እንዲህ ይተርካል. . .

"ከልጆቹ ከአንዷ መዳፍ ጨረር ይፈልቅ ነበር። በጣም ነጭ ነው። ለ15 ሰከንዶች ማየት አልቻልኩም። ፀሐይን ለማየት እንደመሞከር ነበር። አቅም አሳጣኝ። ራሴን ሳትኩ። ከዚያም እየተንገዳገድኩ ወደ መኪናዬ ተመለስኩ። ታመምኩ፤ ሰውነቴ ተንዘፈዘፈ፤ አላበኝ፤ ልቤ በጣም ይመታ ጀመር። ምን እየሆንኩ እንደሆነ አልታወቀኝም።"

ፈጣሪ እንዲረዳው ቢማጸንም ምንም አልተፈጠረም። መኪናው ውስጥ ከሚጫወተው የጆኒ ካሽ ሙዚቃ ውጪ ምንም አይሰማም ነበር።

ያቺ ምሽት የሚክን ሕይወት እስከወዲያኛው እንደቀየረችው ይናገራል።

"ሽጉጡን ከፕላስቲኩ ሳላወጣ ራሴ ላይ አቀባበልኩ"

በግድያ ሙከራ፣ በአፈና፣ መሣሪያ ይዞ በመገኘት ታስሯል። በዛች ምሽት የተመሰቃቀለ ሕይወቱ ተስፋ አስቆርጦት እንደነበር ያስታውሳል።

"ሽጉጡን ከፕላስቲኩ ሳላወጣ ራሴ ላይ አቀባበልኩ። ስተኩስ ምንም ሳይፈጠር ቀረ። ስቅስቅ ብዬ ማልቀስ ጀመርኩ። የመኪናውን ራድዮ በቡጢ ስመታው እጄ ደም በደም ሆነ።

በዛ ቅጽበት እውነተኛ ማንነቴ ቁልጭ ብሎ ታየኝ። ከዚያ በፊት ለ30 ዓመት አላለቀስኩም ነበር። ለመጨረሻ ጊዜ ያለቀስኩት በ11 ዓመቴ ነበርና እዛ መኪና ውስጥ አለቅስ የነበረው ለልጅነቴ፣ ሊኖረኝ ይችል ስለነረው ሕይወት ነው።"

ሚክ አሰቃቂ ድርጊቶቹ ባጠቃላይ በህሊናው ይመላለሱ ጀመር።

እአአ በ1966 ኢንግላንድ ውስጥ የተወለደው ሚክ ከሠራተኛ መደብ ቤተሰብ ነው የተገኘው። አባቱ መስኮት አጽጂ ነበሩ።

ወግ አጥባቂ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደገው። ቤተ ክርስቲያን መሄድ ግዴታ ነበር።

በ1977 ሚክ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ ፓርክ ውስጥ ወሲባዊ ጥቃት ደረሰበት። 11 ዓመቱ ነበር።

"ልረጋጋ አልቻልኩም። ሕይወቴ ተናወጠ" ሲል ወቅቱን ያስታውሳል።

ከዚያም እህቱ በልብ ድካም እንደሞተች አባቱ ነገሩት። የ20 ዓመቷ እህቱ አን ትንከባከበው ነበር። ከሷ ሞት በኋላ ሕይወቱ ሌላ መስመር እንደያዘ ይገልጻል።

"አደገኛ እጽ እና አልኮል ጀመርኩ። ቀጣዩ 30 ዓመት ሲኦል ሆነብኝ" ይላል።

"በእግዚአብሔር አምናለሁ። ግን የሚወደኝ አይመስለኝም"

አደገኛ እጽ መሸጥ የጀመረው በ14 ዓመቱ ነው።

"አደገኛ እጽ አዘዋዋሪ ሆንኩ። የገንዘብ እዳ ካለባቸው ሰዎች የምሰበስበውም እኔ ነኝ። ሰዎችን መጉዳት ብዙም አያስጨንቀኝም ነበር። ሁለቴ በግድያ፣ ሦስቴ በዝርፊያ ታስሬያለሁ። መሣሪያ በመያዝ ምን ያህል ጊዜ ዘብጥያ እንደወረድኩ ማስታወስ እንኳን አልችልም። በጣም ብዙ ገንዘብ አገኝ ነበር። ህመሜን ለመደበቅ ብሞክርም አልተሳካልኝም።"

በ1990ዎቹ ሚክ ሁለት ጊዜ የግድያ ሙከራ ተደርጎበታል።

አንደኛው የትራፊክ መብራት አስቁሞት የተሰነዘረ ጥቃት ነው። ቤት ሲዘርፍም ሕይወቱን ሊያጣ ተቃርቦ ነበር።

ከወንጀል ውጪ ሌላ ሥራ መሥራት እንደማይችል አምኖ ነበር። በ16 ዓመቱ ጓደኛው ከመጠን በላይ ጠጥቶ ሞተ። በ17 ዓመቱ ደግሞ ሌላ ጓደኛው ከመጠን በላይ እጽ ተጠቅሞ ሕይወቱ ተቀጠፈ።

"በእግዚአብሔር አምናለሁ። ግን የሚወደኝ አይመስለኝም" ይላል።

አግብቶ 3 ልጆች ቢወልድም ልጆቹን መንከባከብ ባለመቻሉ እናቱ ያሳድጓቸው ነበር።

ፖሊሶች አደንዛዥ እጽ ወይም መሣሪያ ፈልገው በተደጋጋሚ ቤቱን ይበረብሩ ነበር።

"ሁሉም ነገር ተደማምሮ የአእምሮ ጤናዬን አቃወሰው። የበለጠ እጽ መውሰድ ጀመርኩ። እጅግ አደገኛ ሰው ሆንኩ። ሕይወቴ በአጭሩ እንደሚቀጭ ነበር የማስበው። እንዴት መለወጥ እንደምችል አላውቅም ነበር። መኖር አልፈልግም ነበር።"

ሚክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ በር ላይ የተገኘው በ2009 ነው። ራሱን ሊያጠፋ ከሞከረ በኋላ ወደ አእምሮ ህሙማን ማቆያ ገባ።

ሌሎቹ የአእምሮ ህሙማን ይንከባከቡት እንደነበር ያስታውሳል። በማቆያው ሳለ ከፓስተር ቶኒ ጋር ተዋወቀ።

ያወሩ፣ አብረው ይጸልዩ ጀመር። ሰዎችን ከመጉዳት ወደ መርዳት ተሸጋገረ።

ማንችስተር ዩኒቨርስቲ ሥነ መለኮት መማር ጀመረ። ብዙም ማንበብና መጻፍ ስለማይችል የመጀመሪያውን ዓመት ቢወድቅም በርትቶ በማጥናት 2.1 አግኝቶ ዲግሪ ያዘ።

"ከዚያ በኋላ አደገኛ እጽ መውሰድ፣ መጠጣት አቆምኩ።"

ፓስተር ሚክ

ዛሬ ፓስተር ሚክ በርንሌ ውስጥ እርዳታ በሚሰጥ ቤተ ክርስቲያን ይሠራል። የጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ አደንዛዥ እጽ ተጠቃሚዎችን ወዘተ. . . ይረዳል።

በተለይ ደግሞ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ድጋፍ የሚሰጧቸው ተበራክተዋል።

ከወዳጆቹ ጋር በመሆን ወረርሽኙ ክፉኛ ለጎዳቸው አቅመ ደካሞች ምግብና ልብስ ያቀርባል።

እርዳታ ከሚሰጣቸው አንዷ "ገንዘብና ምግብ ማግኘት ከብዶናል። በየሁለት ቀኑ ምግብ ማግኘት ለኛ ትልቅ ትርጉም አለው" ስትል ነው የምትገልጸው።

ሌላው ተረጂ በ30ዎቹ እድሜ ክልል ትገኛለች። ድብርት እንዳለባትና ወረርሽኙ ሁኔታዋን እንዳባባሰው ትናገራለች።

"እነዚህ ሰዎች ባይረዱኝ ኖሮ ሞቼ ነበር" ትላለች።

የፓስተር ሚክን እርዳታ የሚሹ ብዙ ናቸው።

በ20ዎቹ እድሜ ክልል ያለ ወጣት ካልሲ አጥቶ በቅዝቃዜ እንደተሰቃየ ሲነግረው ያለብሰዋል።

ልጇን ማስተኛ ላጣች እናት አልጋ ይሰጣል። በየቀኑ የተለያዩ ቤተሰቦችን እየተዘዋወረ ይጎበኛል።

በርንሌይ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ስለወደቁ ከሌሎች የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ጋር በመሆን ለመደገፍ ይሞክራሉ።

በእዳ ውስጥ የተዘፈቁት ጥንዶችና ልጃቸው ፓስተር ሚክ ድጋፍ ከሰጧቸው መካከል ይገኛሉ።

ባለ እዳው ፒት "የምንበላው የምንገዛበት ብድር ወስደን ከአንድ ሺህ ፓውንድ በላይ እዳ ውስጥ ገብተን ነበር። እድሜ ለፓስተር ሚክ አሁን እዳውን ከፍለን 300 ፓውንድ ብቻ ይቀርብናል። በእዳው ሳቢያ ልጄና ባለቤቴ ተደብተዋል" ይላል።

የእንቅስቃሴ ገደብ ሲታወጅ የአእምሮ ጤናዋ የተነካው የ55 ዓመቷ ቪቭ "ለአንድ ሳምንት ስላልበላሁ መጸዳጃ ቤት መሬት ላይ ራሴን ስቼ ነበር" ትላለች።

ከዚያም ሆስፒታል ገብታ አገግማ ወጥታለች። ሚክ ሰውነት ገንቢ ምግብና መጠጥ ያቀርብላታል። መድኃኒትም ይገዛላታል።

የካንሰር ታማሚዋ የ50 ዓመቷ ሺላ ኮሮናቫይረስ በጣም ካስፈራቸው አንዷ ናት።

"በየወሩ የደም ምርመራ ማድረግ አለብኝ። ግን ለስድስት ወራት ሕክምና አላገኘሁም። ቀዶ ሕክምና ከተደረገልኝ ላልተርፍ እችላለሁ"።

ከፓስተሩ ውጪ የምታግዛት የ21 ዓመት የልጅ ልጇ ብቻ ናት።

በኮሮናቫይረስ ወቅት እንዳስተዋለው አይነት ማኅበራዊ ቀውስ ገጥሞት እንደማያውቅ ይናገራል።

"እርዳታ የምሰጣው ለቀደመ ጥፋቴ ራሴን ለመቅጣት አይደለም። ሰዎችን ማገልገል ክብር ነው" የሚለው ፓስተር ሚክ፤ በቀደመ ሕይወቱ ላደረገው ነገር ሁሉ ከራሱ ጋር ሰላም ማውረዱን ያስረዳል።

ታዳጊ ሳለ ፓርክ ውስጥ አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ እርዳታ ካደረገላቸው አንዱ መሆኑንም ይናገራል።

ግለሰቡ የጎዳና ተዳዳሪና ጠጪ ነበር። መጠጥ እንዲያቆምና ከቤተሰቡ ጋር እንዲቀላቀል የረዳው ሚክ ነበር።

ከሁለት ዓመት በፊት ይህ ግለሰብ ሕይወቱ አልፏል።

"ለሱም ይሁን ለቤተሰቡ ወይም ለፖሊስም ታዳጊ ሳለሁ እንደደፈረኝ አልተናገርኩም። ይህንን ያደረግኩት ለቀደመ ሕይወቴ ይቅር እንደተባልኩ ስላመንኩ ነው። እሱ እኔ ላይ ያደረገውን ሌሎች ላይ ባልፈጽምም ብዙ ሰው ጎድቻለሁ። በሱ ሀጢያት ውስጥ መኖር አልፈልግም። አሁን ነጻ ነኝ። ሕይወቴን በሀዘን ሳይሆን በይቅርታ አሳልፋለሁ።"