ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ ተቃዋሚ አበሳጭቷቸው አዲስ አልበም አወጡ

ጆርጅ ዊሃ

የፎቶው ባለመብት, LUDOVIC MARIN

የላይቤሪያው ፕሬዝዳት ጆርጅ ዊሃ አንድ ማንነቱ ለጊዜው ያልተገለጸ ተቺ አበሳጭቷቸው አዲስ ዘፈን ዘፍነው ለሕዝብ እንዲለቁ ተገደዋል፡፡

አዲሱ ዘፈኑ ‹አንተ ወላዋይ! አንተ ዋሾ አባይ!› የሚል ነው፡፡ በእንግሊዝኛው የአልበሙን ሥም Mr Liar Man የሚል ርዕስ ሰጥተውታል፡፡

የሙዚቃው ስልት በአመዛኙ ሬጌ ሲሆን በሙዚቃው ግጥሞች በብዛት ይህንን በስም ያልጠቀሱትን ተቃዋሚያቸውንና ተቺያቸውን በነገር የሚሸነቁጡበት ነው ተብሏል፡፡

ፕሬዝዳንት ዊሃ በዚህ ሳምንት ለአድማጫቸውና ለሚመሩት ሕዝብ ባደረሱት በዚህ የሙዚቃ ሥራቸው እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

‹‹ በገዛ አገሬ ያሳድዱኛል፣

ምን ላርግ ስላቸው እንጃባህ ይሉኛል፣

አቤት የውሸት ዓለም አቤት የውሸት ነገር፣

ወይ አይሰሩ አያሰሩ፣ ሁልጊዜ መንጰርጰር››

ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሀ ይህንን ሙዚቃ ሲለቁ ለአራተኛ ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሦስት ሙዚቃዎችን ለሕዝባቸው አድርሰዋል፡፡

ጆርጅ ዊሃ በዚህ የሙዚቃ ሥራቸው ሊነቅፉት የፈለጉት ሰው አብረሃም ዳሪዮስ ዲሎን የተባለ ተቃዋሚ መሪን እንደሆነ የአገሬው ጋዜጦች እየጻፉ ይገኛሉ፡፡

ሰውየው የዋና ከተማዋ የሞኖሮቪያ ተመራጭ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነው ተብሏል፡፡

በቅርቡ በአንድ የራዲዮ ፕሮግራም ቀርቦ ፕሬዝዳንት ዊሃን ከፍ ዝቅ ሲያደርግ ነበር፤ ይህም ፕሬዝዳንቱን አስቆጥቶ ሙዚቃ እንዲለቁ አድርጓቸዋል የሚል ግምት አለ፡፡

የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት ግን ይህንን ግምት አስተባብሏል፡፡

ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሀ የቀድመው የኤሲሚላን እና የቼልሴ አጥቂ ነበሩ፡፡ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ደግሞ ሙዚቃን አልፎ አልፎ ይለቃሉ፡፡

በ2000ሺህ ዓመተ ምሕረት አውሮጳ ከሚጫወቱ አፍሪካ ተጫዋቾች ስለ አፍሪካ አንድነትና ፍቅር አዚሟል፡፡

በ2014 ዓ/ም ደግሞ ከጋናዊ አርቲስት ሲድኒ ኢቦላን ስርጭት ለመግታትና ግንዛቤን ለማስጨበጥ ሙዚቃ መስራታቸው ይታወሳል፡፡

በቅርቡም ኮቪድን በተመለከተ ፕሬዝዳንቱ አዲስ የሙዚቃ ሥራቸውን አበርክተዋል፡፡

ይህ አራተኛው የሙዚቃ ሥራቸውን ግን አዲስ ተህዋሲ ሳይሆን አዲስ ተቃዋሚ አበሳጭቷቸው ያንጎራጎሩት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡