ጎርፍ፡ በኢትዮጵያ በመቶ ዓመታት ይከሰታል በተባለ ጎርፍ ግማሽ ሚሊዮን ሰው ተጎዳ

በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች በደረሰው የጎርፍ አደጋ፣ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች መጎዳታቸውን መንግሥት ገለፀ።

የሰላም ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚል እና የውሃ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ለጋዜጠኞች በትናንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ የዘንድሮ ክረምት ዝናብ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በቤቶችና መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈርያት ካሚል በሶስት ክልሎች እና 23 ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ መከሰቱን ገልፀው፣ 580 ሺህ ዜጎች መጎዳታቸውንና ከእነዚህም ውስጥ 217 ሺህ የሚሆኑት ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸው ተገልጿል።

በ100 ዓመታት መካከል አንዴ የሚከሰት

እንደ ውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ገለፃ ከሆነ ሰሞኑን የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከአዋሽ ወንዝ መነሻ እስከ መድረሻው ፣ በኦሞ ወንዝ፣ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ በሚገኙ እንደ ባቱ (ዝዋይ) እና መቂ ባሉ ከተሞች፣ በአባይ ተፋሰስ አካባቢ እና ጣና ሐይቅን ጀምሮ እስከ ሱዳን እንደዚሁም ደግሞ በባሮ ወንዝ መሆኑን ተናግረዋል።

ሰሞኑን በአንዳንድ ቦታዎች የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በመቶ አመታት ውስጥ አንዴ የሚከሰት መሆኑን ዶ/ር ስለሺ ጨምረው አስረድተዋል።

በአዋሽ ወንዝ የተከሰተው ደግሞ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ መሆኑን አክለዋል።

ዘንድሮ ከባድ ዝናብ መተንበዩን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንም አብራርተዋል።

እንደምሳሌም በኦሮሚያና በአፋር ክልል ውስጥ 134 ኪሜትር ርዝመት ያለው የውሃ መውረጃ መስመር ጥገና መሰራቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የተፋሰሱ ምክር ቤት ከክልሎች ፕሬዝዳንቶች እና ጉዳይ የሚመለከታቸው ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ጋር መወያየታቸውንና ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ይናገራሉ።

አደጋው የደረሰበት ስፍራ "በሄሊኮፕተር በመታገዝ በሰው ሕይወት ላይ አደጋ ሳይደርስ የተሳካ ስራ መስራት ተችሏል፤ ጎርፉ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በተወሰኑ ከብቶች ላይ አደጋ ደርሷል፤ የተወሰኑ ቤቶችም በጎርፍ ተውጠዋል" ብለዋል።

ከነፍስ ማዳን ስራ ባሻገር ሰዎች ለችግር እንዳይጋለጡ ማድረግ እና የምግብና ሌሎች ቁሳቁስ አቅርቦቶች እየተሰራ መሆኑን የሚናገሩት የሰላም ሚኒስትሯ፣ ጎርፉ ካለፈ በኋላ የመልሶ ማቋቋም ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።