ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ከኮሮናቫይረስ የዳነው ሰው ዳግም በወረርሽኙ ተያዘ
የሆንግ ኮንግ ሳይንቲስቶች መጥፎ ዜና ይዘዋል፡፡
ዕድሜው በ30ዎቹ የሚገመት አንድ ሰው በኮሮና ተይዞ ሙሉ በሙሉ ከዳነ በኋላ በድጋሚ መያዙን ደርሰውበታል፡፡
በተለምዶ ይታመን የነበረው አንድ የተያዘ ሰው ማገገም ከቻለ ሰውነቱ ከዚያ በኋላ ተህዋሲውን የሚቋቋም መከላከያ ስለሚያመርት በተመሳሳይ ተህዋሲ በድጋሚ አይወድቅም የሚል ነበር፡፡
ይህ ሆንግ ኮንግ በድጋሚ ተይዞ የተገኘው ሰው መጀርመያ ኮቪድ-19 ተህዋሲ የነካው ከአራት ወር ተኩል በፊት ነበር፡፡
ከዚህ ዘለግ ያለ ጊዜ በኋላ ነው በድጋሚ መያዙን የሆንግ ኮንግ ሳይንቲስቶች የደረሱበት፡፡
የሆንግ ኮንግ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት የሰውየው ዘረመል ጥልፍልፍ (genome sequencing) ያሳያቸው ነገር ቢኖር ሰውየው መጀመርያ የተያዘበት የቫይረሱ ዓይነት ከአራት ወራት በኋላ ከያዘው ጋር ፍጹም የሚለይ ቅርጽ አለው፡፡
በመሆኑም ግለሰቡ በዓለም የመጀመርያው በቫይረሱ በድጋሚ መያዙ የተረጋገጠ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ይህ ክስተት ላለፉት ዘለግ ያሉ ወራት በጤና ባለሞያዎች ዘንድ ሲያከራክር ለነበረው ጉዳይ ምላሽ የሰጠ ነው፡፡ አንድ ሰው በቫይረሱ ከተያዘ በኋላ ከዳነ መልሶ ሊያዝ አይችልም የሚለውን አስተሳሰብም ውሀ ቸልሶበታል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ በአንድ ሰው የጤና ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ድምዳሜ ላይ መድረስ አያሻም ይላል፡፡ በድጋሚ መያዝ በአንዳንድ ሰዎች ብቻ አልፎ አልፎ የሚያጋጥም ነገር ሊሆን ይችላል ይላል፤ ደብሊው ኤች ኦ፡፡
አሁን በመላው ዓለም 23 ሚሊዮን ሰዎች በላይ በተህዋሲው ተነክተዋል፡፡
ተህዋሲው ሰውነታቸው የገባባቸው ሰዎች ከዳኑ በኋላ ያ ተህዋሲ በድጋሚ እንዳይዛቸው የሚያስችል በቂ ትጥቅ ነጭ የደም ሴላቸው አዘጋጅቷል ተብሎ ነው የሚገመተው፡፡
በተህዋሲው በጣም የታመሙ ሰዎች ሰውነታቸው በጣም ጠንካራ የመከላከያ መሰናዶ ስለሚያደርግ በድጋሚ የመያዝ እድላቸው ጠባብ ነው ይላሉ፣ ተመራማሪዎች፡፡
ነገር ግን አሁንም ድረስ ያልታወቀው ነገር ይህ ሰውነት የሚያሰናዳወው የመከላከል ትጥቅና ስንቅ ምን ያህል ጠንካራ ነው፣ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል የሚለው ነው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በዚህ ጉዳይ ላይ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ በበርታካ የቫይረሱ ታማሚዎች ላይ ጥናት መደረግ አለበት ይላል፡፡
ኮቪድ-19 ተህዋሲ መልኩን የሚለዋውጥ ከሆነና ብዙ የቫይረስ ዝርያ ካለው ሰዎችን በተደጋጋሚ እየመጣ ሊጎበኝ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል፡፡ ክትባቱንም ዋጋ ቢስ እንዳያደርገው ይፈራል፡፡