"የፌደራል መንግሥት ግጭት ቆስቋሽ በሆኑ ክልላዊ መንግሥታት ላይ ኃይልን አይጠቀምም" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በዛሬው ዕለት ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት ያካሄዱ ሲሆን ለአንዳንድ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም ምላሽ ሰጥተዋል።

የዛሬው ውይይት በዋናነት በሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክር መድረክ እንዲካሄድ ቀጣይ አቅጣጫን ማስቀመጥ እንዲቻል እና የልማት ጉዳዮች እንዲሁም ሰላምና ደህንነትን የመሳሰሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ የፖርቲ አመራሮቹ ያላቸውን አቋምም በዚህ ውይይት ላይ አንፀባርቀዋል።

የህዳሴ ግድብ የስራ ክንውን መፋጠንን አስመልክቶ እንዲሁም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት መንግሥት የወሰዳቸውን እርምጃዎችና የቫይረሱን ስርጭትም ለመቆጣጠር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ላይ ያላቸውን ድጋፍ የፓርቲ አመራሮቹ ገልፀዋል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ ቢራዘምም የትግራይ ክልል ምርጫ አካሂዳለሁ ማለቱ "ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓትን መናድ ነው፣ ሕገ-መንግሥቱን በመጻረር በሚደረጉ ተግባራት ላይ ሕግ የማስከበር ሥራ እንዲሠራ ጠይቀዋል።" ማለታቸውን መግለጫው አትቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በበኩላቸው ምርጫ ለማድረግ የተዘጋጁ ክልሎች ላይ ምላሽ የሰጡ ሲሆን መንግሥታቸው ኃይልን እንደማይጠቀም ተናግረዋል።

"ፌደራል መንግሥት ግጭት ቆስቋሽ በሆኑ ክልላዊ መንግሥታት ላይ ኃይልን አይጠቀምም፡፡ የፌደራል መንግሥት የኃይል እርምጃን እንደሚወስድ በማሰብ በግልጽ ግፊት እየተደረገበት ቢሆንም፣ ሀገሪቱን የሚያስተዳድሩ ተቋማት እና ሕገ መንግሥታዊ አካሄድ ተጠናክረው መከናወናቸውን ይቀጥላሉ" ማለታቸውን መግለጫው አስፍሯል።

የሃገሪቱን ሰላምን ማስከበርና ደህንነት ከማስጠበቅ ጋር በተመለከተም መንግሥት በሕገ መንግስቱ የተሰጠውን ህግ የማስከበር ስልጣን በሚገባ እንዲጠቀም፣ ሰላምን የሚያውኩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል።

የሙዚቀኛ ሃጫሉ ሁንዴሳ በመኪና ውስጥ መገደል ተከትሎ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ለእስር መዳረጋቸው ፖርቲዎችን ኢላማ ያደረገ ነው መባሉ ትክክል አለመሆኑና የነዚህ ሰዎች እስር "በቅርቡ በተፈጸመው የአመጽ ሥራ ውስጥ የተሳተፉ" ና ኃላፊነታቸውንም የዘነጉ ናቸው ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በመሆናቸው ሊነኩ አይገባም የሚለው እሳቤ ስህተት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትኞቹም ፖለቲካ ፓርቲዎች ከህግ ውጪ እንዳልሆኑም አስምረዋል።

አክለውም ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባቸው አካላትም በፍትህ ስርአቱ መሰረት ይጠየቃሉ ብለዋል።

"ማንም ሰው ጤናው እንዲጓደል አንሻም፣ ሊስተካከሉ የሚገባቸው ሁኔታዎችን እናስተካክላለን። ነገር ግን፣ ሕግ የበላይ ሆኖ ይቀጥላል።" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በእስር ያሉ ግለሰቦች እንዲፈቱ አንዳንድ ግለሰቦች ጥረት ማድረጋቸውን የገለፁት ዶክተር ዐብይ ይህ ተግባራዊ እንደማይሆንም ተናግረዋል።

"በቅን ልብ በእስር ላይ ያሉ ግለሰቦች እንዲፈቱ ለማሸማገል በግል የሚቀርቡኝን ሰዎች ቅንነት ባከብርም፣ ጥያቄያቸው የፍትሕ ስርዓቱ እንዲዛባ የሚያደርግ በመሆኑ እና እኔ በግሌ የሚፈታንም ሆነ የሚታሰርን ሰው ለመምረጥም ለመወሰንም የማልችል በመሆኑ አግባብነት የለውም።" በማለት አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ መግለጫው እንዳተተው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ካሉ "ፅንፈኞችና ለውጡን የሚያደናቅፉ" ያሏቸው ከቀድሞው ስርዓት ተከታዮች የማጥራት ስራም እንዲሰራ እኚሁ ፓርቲዎች ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ባነሱት ሃሳብ ተስማምተው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ "የተሰገሰጉ አውዳሚ ግለሰቦች እና ሌቦች" ያሏቸው አካላት ለውጡን ለማደናቀፍ እየሰሩም ነው ብለዋል።

ሆኖም ተቋማዊ ግንባታ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ መሆኑ እንዲታሰብና የማጥራት ስራ የሚቀጥል እና በጊዜም ውስጥ ያሏቸው ተቋማዊ ማነቆዎች ይወገዳሉ ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላማዊ ፖለቲካ ተሳትፎ ያለውን ጠቃሚነት አፅንኦ በመስጠት በፖለቲካ ውይይቶች ወቅት መከባባር አስፈላጊ ነው ብለዋል፥።

"ጥንካሬ የሚገለጸው ገንቢ ሃሳቦችን በማፍለቅ እንጂ በጡንቻ አማካኝነት አይደለም" በማለት አበክረው ተናግረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አመራሮች በተጨማሪ ቀጣዩ አገራዊ ምርጫንም በተመለከተ አንዳንድ ሃሳቦች ያነሱ ሲሆን በቀጣዩም ብሔራዊ መግባባትን በተመለከተ የውይይት ርዕስ እንዲሆን መወሰኑን መግለጫው አመላክቷል።