ሳኡዲ አረቢያ የገዛ የደኅንነት ሹሟን እያደነችው ነው

ልኡልና አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ልኡልና አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን

እጅግ የናጠጡ የንጉሣዊያን ቤተሰቦችንና የስጋ ዘመዶቻቸውን ወደ እስር በመወርወር የሚታወቁት የሳኡዲው ልኡልና አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን አሁን ደግሞ የቀድሞው ቁልፍ የደኅንነት መኮንን የነበሩትን ዶ/ር ሳአድ አልጃብሪን ለመያዝ ዘመቻ ጀምረዋል፡።

ዶ/ር ሰአድ አልጃብሪ ለደኅንነታቸው በመስጋት ካናዳ የተጠለሉ ሰው ናቸው። ዶ/ር ሰአድ አልጀብሪ በተለይ ከእንግሊዙ የስለላ መዋቅር ኤም16 ጋር በመተባበር የሽብር ጥቃቶችን በማክሸፍ ስራቸው ይታወቃሉ። ወደ ካናዳ የሸሹት የዛሬ 3 ዓመት ሲሆን አልጋ ወራሹ ቢን ሳልማን ግን እርሳቸውን ወደ አገር ቤት ለማምጣት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም ተብሏል።

አሁን ደግሞ በርሳቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ለመፍጠር ሳኡዲ የሚገኙ ልጆቻቸው በአገሪቱ የጸጥታ ኃይል እንዳሳገቱባቸው ቤተሰባቸው ይፋ አድርጓል። የበኩር ልጃቸው ካሊድ አልጃብሪ ለቢቢሲ እንደተናገረው ኦማርና ሳራ የሚባሉትን ወንድምና እህቱን በቁጥጥር ሥር ለማዋል 50 የሳኡዲ የጸጥታው መስሪያ ቤት ባልደቦች በ20 መኪናዎች ተጭነው ወደ ቤታቸው መጥተዋል።

ካሊድ አልጃብሪ (ግራ) ታናሽ ወንድሙ ኦማር (ቀኝ) በአገሪቱ መንግሥት ታፍኖ ይገኛል ይላል።

የፎቶው ባለመብት, የአልጃብሪ ቤተሰብ ፎቶ

የምስሉ መግለጫ, ካሊድ አልጃብሪ (ግራ) ታናሽ ወንድሙ ኦማር (ቀኝ) በአገሪቱ መንግሥት ታፍኖ ይገኛል ይላል።

ሪያድ የሚገኘው የቤተሰቡ መኖርያ የደኅንነት ካሜራዎችን ምስል የያዙ የምስል ቅጂ ቋቶች ተነቃቅለው መወሰዳቸውን፣ ከፍተኛ ብርበራ መካሄዱን፣ የ20 እና የ21 ዓመት እድሜ ያላቸው ወንድም እህቱም ወዳልታወቀ ስፍራ እንደተወሰዱ አብራርቷል።

የዶ/ር ሰአድ አልጃብሪ የበኩር ልጅ ካሊድ ከአባቱ ጋር ጥገኝነት ከጠየቀበት ካናዳ በመሆን ለቢቢሲ እንደተናገረው ይህ ሁሉ እየተደረገ ያለው አባቱ ላይ ጫና በመፍጠር ወደ አገር ቤት ለማስመለስ ነው። ካሊድ ጨምሮ እንደገለጸው ወንድምና እህቱ አሁን በሕይወት ስለመኖርቸው እንኳ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይችልም።

ሳራ አልጃብሪም በመንግሥት ተይዛለች ተብሎ ይታመናል

የፎቶው ባለመብት, አልጃብሪ ቤተሰብ ፎቶ

የምስሉ መግለጫ, ሳራ አልጃብሪም በመንግሥት ተይዛለች ተብሎ ይታመናል

ቢቢሲ ስለ ጉዳዩ የሳኡዲ መንግሥትን ምላሽ ለማካተት ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካለተም።

ዶ/ር አልጃብሪ በሳኡዲ የደኅንነት መዋቅር ውስጥ ባገለገለበት ዘመን አል-ቃኢዳን ለማንበርከክ ሁነኛ ሚና የነበረው ሰው እንደሆነ ይነገራል። በተለይም ከአሜሪካ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ፣ አውስትራሊያና ኒዊዚላንድ የደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ጋር እጅና ጓንት በመሆን በርካታ ውጤት ያስመዘገበ ሰው ነበር። በፈረንጆች በ2010 እርሱ የደረሰበት መረጃ አል-ቃኢዳ በአውሮፓ ከባድ የሽብር ጥቃት ከማድረሱ በፊት እንዲከሽፍ ምክንያት ስለመሆኑም ይመሰከርለታል።

ዶ/ር ሰአድ አልጃብሪ (ፊታቸው የተከበበው) እአአ 2015 ላይ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ባቀኑበት ወቅት በወቅቱ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሯ ቴሬሳ ሜይ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር

የፎቶው ባለመብት, BANDAR AL-GALOUD

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ሰአድ አልጃብሪ (ፊታቸው የተከበበው) እአአ 2015 ላይ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ባቀኑበት ወቅት በወቅቱ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሯ ቴሬሳ ሜይ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር

በየመን ይገኝ የነበረው አል-ቃኢዳ መጠኑ ከፍ ያለ ቦምብ በእቃ መጫኛ አውሮፕላን አስርጎ ማስገባቱን፣ አውሮፕላኑም ወደ ቺካጎ እንደሚበርና ቦምቡ የሚገኘው በማተሚያ ማሽን ውስጥ እንደሆነ የተብራራ መረጃን ለእንግሊዙ የኤም 16 ያቀበለውም ዶ/ር ሰአድ አልጃብሪ እንደሆነ አንድ የዩናይትድ ኪንግደም የደህንት ባለሞያ መስክረዋል።

በማተሚያ ማሽን ተጭኖ የነበረው ቦምብ ቺካጎ ደርሶ ቢሆን ኖሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ አሜሪካዊያንን ሕይወት ይቀጥፍ ነበር ብለዋል እኚህ የደህንነት ሰው። አልጃብሪ ዝምተኛና የተረጋጋ ሰው ሲሆን በአርተፊሻል ኢንተሌጀንሲ የዶክትሬት ዲግሪውን ከኤደንበርግ ዩኒቨርስቲ አጊንቷል።

ከዚያ በኋላ ወደ ሳኡዲ በመመለስ የደኅንነት መስሪያ ቤቱን ማዘመን ችሏል። "ሳኡዲዎች ከርሱ በፊት የደህንነት ስራ ይሰሩ የነበረው ኋላ ቀር በሆነ መንገድ ሰዎችን አሰቃይቶ እንዲናዘዙ በማድረግ ነበር። እርሱ ይህን ሁኔታ ለውጦታል፤ መረጃን በኮምፒውተር በመጥለፍ ዘመናዊ ስለላን ለሳኡዲ ያስተዋወቀ ሁነኛ ሰው ነበር" ይላሉ ስማቸው ያልተገለጸ የምዕራቡ አገር የደኅንነት ሰው።

በ2015 ንጉሥ አብደላ መሞታቸውን ተከትሎ ግማሽ ወንድማቸው ሣልማን ቢን አብዱልአዚዝ ንግሥናውን ሲቆጣጠሩ ልጃቸውንና የዛሬውን አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማንን መከላከያ ሚኒስትር አድርገው ሲሾሙ ነገሮች ወዳልተፈለገ አቅጣጫ አመሩ።

መሐመድ ቢን ሳልማን በፍጹም ለዚህ ስልጣን የሚመጥን ሰው እንዳልነበረ ይነገራል። የያኔው መከላከያ ሚኒስትርና የአሁኑ አልጋ ወራሽ ሞገደኛው መሐመድ ቢን ሳልማን በድንገት ሳኡዲን በየመን ጦርነት ውስጥ እንድትዘፈቅ ግብታዊ ውሳኔ ላይ ሲደርሱ ዶ/ር አልጃብሪ ይህ መሆን እንደሌለበት፣ ጦርነት ውስጥ የሚገባው ግልጽ የመውጫ ስልት ሲኖር ብቻ መሆኑን፣ ሆኖም አገራቸው ሳኡዲ ይህ ስልት እንደሌላት ቢከራከሩም ሰሚ አላገኙም ነበር።

ሳኡዲ አሁንም ድረስ በየመን ጦርነት ውስጥ ገብታ መውጫው እንደጠፋባት ፖለቲካ አዋቂዎች ይናገራሉ።

አልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ሳልማን ለሥልጣኔ ጸር ናቸው ያሏቸውን በተለይም ለንግሥናው ይጠበቁ የነበሩትን መሐመድ ቢን ናይፍን በቁጥጥር ሥር ካደረጉ በኋላ በቀድሞ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ባልደረቦች ላይ አሰሳ ከፍተው ቆይተዋል። ዶ/ር አልጃብሪም የዚሁ ዘመቻ አንድ አካል ናቸው።

መሐመድ ቢን ሳልማን ከሳኡዲ ውጭ ሆነው መንግሥታቸውን የሚተቹ ሰዎችን አድኖ ከምድረ ገጽ በማጥፋት ስማቸው ይነሳል። በቱርክ የሳኡዲ ቆንስላ ደብዛው የጠፋው የዋሺንግተን ፖስት አምደኛ ጀማል ካሾግጂ ጉዳይ ዓለምን በከፍተኛ ሁኔታ ሲያነጋግር እንደነበር ይታወሳል። ልዑል ቢን ሳልማን ዶ/ር አልጃብሪ በምዕራቡ ያለውን ተሰሚነት ተጠቅሞ ለሥልጣኔ ስጋት ይሆንብኛል ብሎ ሊሰጋ እንደሚችልና ይህንንም ለመቀልበስ ብቸኛ መደራደሪያው ልጆቹን ማገትና አባታቸውን ወደ አገር ቤት እንዲመለስ ማባበል እንደሆነ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ይናገራሉ።