ቻይናውያን ሀኪሞች ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ነው ተባለ

ቻይናውያን ዶክተሮች ሙያዊ ድጋፍ ለመስጠት ወደ ኢትዮጵያ እና ቡርኪና ፋሶ እያቀኑ ነው ተባለ።

ሀኪሞቹ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ወደ ሁለቱ አገራት እንደሚሄዱ የቻይና ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ 'ቻይና ግሎባል ቴሌቭዥን ኔትወርክ ሪፖርትስ' አሳውቋል።

ምን ያህል ሀኪሞች ወደ ኢትዮጵያ እና ቡርኪና ፋሶ እየሄዱ እንደሆነ የተባለ ነገር የለም።

ዶክተሮቹ ከሲቹዋን እና ከቲአንጂን ግዛቶች የተውጣጡ ናቸው ተብሏል።

የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር እንዳለው የህክምና ባለሙያዎቹ ወደ ሁለቱ አገራት ጉዞ የጀመሩት ሀሙስ እለት ነው።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ዛሆ ሊጃን እንደተናገሩት፤ ሀኪሞቹ ልምዳቸውን ያካፍላሉ። ወረርሽኙን በመከላከል ረገድ የቴክኒክ እገዛም ያደርጋሉ።

ናይጄሪያም 18 ቻይናውያን ሀኪሞች ድጋፍ እንዲሰጧት ወደ አገሯ የመጥራት እድቅ ይዛ ነበር። ነገር ግን ናይጄሪያውያን የህክምና ባለሙያዎች ቅሬታ አሰምተዋል።

የናይጄሪያ ሀኪሞች ማኅበር በአገሪቱ የሚገኙ ሥራ አጥ የህክምና ባለሙያዎችን ማሰማራት የተሻለ ነው ብሏል።

ቻይናውያን ዶክተሮች፤ ለናይጄሪያ ባህል እና የሥራ ባህል እንግዳ እንደሚሆኑም ማኅበሩ ተናግሯል።

በቻይናዋ ጉዋንዡ ግዛት የሚኖሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ከቤታቸው እንዲሁም ከሆቴላቸው መባበራቸው ሪፖርት መደረጉ ይታወሳል። ለዚህም ምክንያት የተባለው ኮሮናቫይረስ በአፍሪካውያኑ ዘንድ በስፋት እየተሰራጨ ነው የሚል ነው።

በቻይና የናይጄሪያ ኤምባሲ፤ ዜጎቹን ለማስወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።